«በኢትዮጵያ ሠላማዊ ትግል አያዋጣም የሚባለው ከአሜሪካ ወይም ከአውሮፓ አይደለም» ፕሮፌሠር መስፍን ወ/ማርያም

Prof. Mesfin Woldemariyamፕሮፌሠር መስፍን ወ/ማርያም የሰባዊ መብት ታጋይ በመሆን ለረጅም ዓመታት የኢሰመጉ ፕሬዝዳንት ሆነው አገልግለዋል። ከዛም ቅንጅትን ትተው እስከወጡበት ጊዜ ድረስ በፖለቲካ ትግል ውስጥ ቆይተው የነበረ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ በአንድነት ፓርቲ ብሔራዊ ምክር ቤት አባል ናቸው። ፕሮፌሠር መስፍን ከፓርቲው ዋና ፀሐፊ አቶ አስራት ጣሴ ጋር በመሆን በአሜሪካን ሀገር በዘጠኝ ስቴቶች ለሚገኙ ደጋፊዎቻቸው ቅስቀሳ ሲያደርጉ ቆይተው ባለፈው ሣምንት ወደ ሀገር ቤት ተመልሰዋል። ፕሮፌሠር መስፍን የትጥቅ ትግልን አጠንክረው ሲቃወሙ ይደመጣሉ። ጽዮን ግርማ (የእንቢልታ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ) ስለትጥቅና ሠላማዊ ትግል ስልት ከፕሮፌሠር መስፍን ወ/ማርያም ጋር ቆይታ አድርጋለች።

 

በተለያዩ ጊዜዎች በሰጧቸው ቃለምልልሶችም ሆነ፣ ባደረጓቸው ንግግሮች የትጥቅ ትግልን ጠንከር አድርገው ይቃወማሉ ምክንያቶቹ ምንድን ናቸው?

 

የትጥቅ ትግል ማካኼድ ለኢትዮጵያ አያስፈልግም፣ የሚገባም አይደለም የምልባቸው ምክንያቶች በርካታ ናቸው። ዋና ዋና የምላቸውን ለማብራራት አንደኛ፡- የትጥቅ ትግል ለኛ ለኢትዮጵያውያን አዲስ ነገር አይደለም፣ ታሪካችን በሙሉ የሚያሳየው የትጥቅ ትግልን ነው። ራስ እገሌ ከራስ እገሌ ጋር፣ ደጃዝማች እከሌ ከደጃዝማች እከሌ ጋር፣ አንድ ንጉሥ ከሌላ ንጉሥ ወይም ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር ከሚያደርጉት ውጊያ ጀምሮ እስከ ወያኔ ትግል ድረስ ያየነው ይኼንኑ ነው። ይኼ ያረጀ አገራችንን ወደ ኋላ ያስቀረ የመገዳደል፣ የመጨራረስ፣ የማፈራረስ ታሪካችን ነው። ስለዚህ በግልጽ የምናውቀውና ያየነው ስለሆነ ምንም አይጨምርልንም፤ ይህንን የምናስብ ከሆነ ትጥቅን የምንፈልግበት ምንም ምክንያት የለንም።

 

ሁለተኛው፡- በመንፈሣዊ ሞራል አስተሳሰብ ካየነው የትጥቅ ትግል ማለት መገዳደል ማለት ነው። አንዱ አንዱን መግደል ያውም ወገንን በመግደል፣ በመገዳደል ጥሩ ውጤት እናመጣለን ብሎ ማሰብ የመንፈስ ዝቅጠትና ውድቀት ነው። በመገዳደል ጥሩ ውጤት ሊመጣ አይችልም፤ ሕይወትን ማዳበር፣ ማባዛት ነው እንጂ ሕይወትን መቅጣት መጥፎ፣ ውጤቱም መጥፎ ነው። ዛሬ የወያኔን አገዛዝ የምንቃወምበት አንደኛው ምክንያት በጉልበት፣ በኃይል፣ በጠመንጃ ሰዎችን ስለሚገዛ፣ ስለሚገድል፣ ስለሚጨፈጭፍ፣ ስለሚያስርና ስለሚደበድብ ነው። እየተቃወምን ያለነው ይኼ መጥፎ ነው እያልን ነው፤ ይህንን የምንቃወም ከሆነ ያንኑ ነገር እኛ ስናደርገው ለኛ ሲሆን ጥሩ ነው፣ ለወያኔ ሲሆን መጥፎ ነው ማለት አንችልም። መጥፎ ነገር እኛ ስናደርገውም መጥፎ ነው፤ ወያኔ ሲያደርገውም መጥፎ ነው፤ ለሁላችንም መጥፎ ነው። የሚያስከትለው የሞራልና የመንፈስ ውድቀት ነው።

 

ሦስተኛ፡- ፈረንጆች (The Logic of Force) የሚሉት ነገር አላቸው። በጉልበት መተማመን ሌላ በጉልበት የሚተማመን ይፈጥራል፣ ይራባል። ያ ደግሞ ሌላ በጉልበት የሚተማመን ይፈጥራል፤ አዕምሮ ውስጥ ሌላ ነገር አይገባም። አንድን ሰው ድራሹን አጥፋው ሲሉ ከነአስተሳሰቡ ይመስላቸዋል ሃሳቡ ድራሹ አይጠፋም፤ ሰውየውን ነው ድራሹን የሚያጠፉት፤ በእንደዚህ ዓይነት የሃሳብና የማኅበረሰብ ዕድገት ሊመጣ አይችልም። አዕምሮን በጡንቻ በመለወጥ፣ ማሰብን አስተኝቶ በጉልበትና በጠመንጃ ብቻ ለመነጋገር መሞከር ትክክል አይደለም፣ ተገቢም አይደለም፤ እኔ ሕገ አራዊት ወደምለው የእንስሳ ምድብ ውስጥ መግባት ነው።

 

አራተኛው፡- የፖለቲካ ትግል የምናካኺደው፤ ይኼ በኢትዮጵያ በፍፁም አዲስ ነገር ነው። የፖለቲካ ትግል ማለት ደግሞ ይህንን ሕገ አራዊት በማኅበረሰብ ሕግ፣ በሕገ መንግሥት ሕግ መለወጥ ነው። ሰዎች በመደባደብ ፈንታ ይከራከራሉ፣ ይወያያሉ፣ ህዝቡ በድምፁ ፈራጅና ዳኛ ይሆናል፤ ፖለቲካ የሚባለው ይኼ ነው። ከድብድብና ከጠመንጃ ነፃ ሆኖ በሙሉ ልብ ለመነጋገር፣ ለመከራከር፣ የተለያዩ ተቃራኒ ሃሳቦችን በነፃነት ለመወያየት የሚደረግ ነው። እኛ የምንፈልገውና ዲሞክራሲ፣ ዲሞክራሲ እያልን የምንጮኸው ይህንኑ ለማምጣት ነው። ሰው ሁሉ በነፃነት፣ በሙሉ ልብ ሃሳቡን የሚገልጽበት፣ እንደልቡ የሚሰበሰብበት ሥርዓት ለመፍጠር፣ ጠመንጃ ቦታ የለውምና መቅረት አለበት።

 

እርሶ ያሏቸውን በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገኙ መብቶች እንዲኖሩ ለማድረግ፣ ሠላማዊ ትግሉ አላዋጣም የሚሉ አሉ። ግንቦት 7 የተባለውና በዶ/ር ብርሃኑ የሚመራው ንቅናቄ የትጥቅ ትግሉንም እንደሚመርጥ አስታውቋል። እርስዎ ከትጥቅ ትግሉ በአንፃራዊ መልክ ያለው የሠላማዊ ትግል በምን መልኩ ያዋጣል ይላሉ?

 

ግንቦት 7 ይህንን ይል አይል አላውቅም፤ ብቻ ማን ይበለው ማን፣ የትኛውም ፓርቲ ይበለው፣ የሠላማዊ ትግል አላዋጣም የሚባለው ልክ አይደለም፤ በ1997 ዓ.ም. በትንሹ ተጀምሮ ታይቷል። ሚያዝያ 30 የምን ውጤት ነው፣ የሠላማዊ ትግል ውጤት አይደለም? ከዚያ በላይ ድል አለ? ከዚያ በላይ የህዝብን ስሜትና አንድነት የሚያሳይ ጉልህ የሆነ ማስረጃ አለ? የግንቦት 7 ምርጫ ምንድነው፣ የሠላማዊ ትግል ውጤት አይደለምን? በኢትዮጵያ ያ ሁሉ ህዝብ፣ ቀኑንና ለሊቱን ሙሉ ቁሞ ለመምረጥ የተዘጋጀው፣ በሠላማዊ ትግል ውጤት እኮ ነው። ይኼንን የሚዘነጉ ወይ ደግሞ ሆን ብለው ለመርሳት የሚፈልጉ ሰዎች ካልሆኑ በስተቀር የሠላማዊ ትግል ውጤቱማ በጉልህ ታይቷል። በርግጥ የሠላማዊ ትግል ውጤት በጡንቻ፣ በመሣሪያ ኃይል መቀልበሱ ታይቷል።

 

ከዛም ወዲህ ሠላማዊ የትግሉን መድረክ የሚያጠቡ ነገሮች በነፃው ፕሬስ በኩል፣ በፖለቲካውም በኩል ታይተዋል፣ እየታዩም ናቸው። አንዳንድ የሚደረጉ ነገሮች አሉ ለምሳሌ ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ያየሁት፣ የጋዜጣውን ዋና አዘጋጅ ከአዲስ አበባ ጎንደር ወስዶ ማስር (በርግጥ የአማረ ጠበቃ አይደለሁም) ለኔ ትክክል አይደለም። በተናገረው፣ በፃፈው ከሆነ እዚሁ ይያዛል፣ ይታሠራል እንጂ ከሚኖርበት ቦታ ተወስዶ ሌላ ቦታ መታሰሩ ግልጽ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው። እንደዚህ፣ እንደዚህ ዓይነት ነገሮች ትክክል አይደሉም፤ የምንዋጋው ይኼንኑ ነው። ነገር ግን እንደዚህ እየተደረገ ነው ብለን የሠላማዊ ትግሉ አይሠራም ለማለት አንችልም፤ የሠላማዊ ትግሉ አስፈላጊ የሆነው እነዚህ ነገሮች ስላሉ ነው። እነዚህ ነገሮች መፈፀማቸው የሠላማዊ ትግሉ አልሠራም የሚያሰኙ ሳይሆኑ ሠላማዊ ትግሉ ያጋጠመውን ጋሬጣ የሚያሳዩ ናቸው። እነዚህ ነገሮች ባይኖሩ ትግል መጀመሪያውኑ ለምን ያስፈልጋል።

 

እነዚህ ነገሮች ስላሉ ነው ትግሉ የሚያስፈልገው። በሠላማዊ ትግሉ መሞት፣ መታሰር፣ መደብደብ አለ፤ ሌላም ሌላም ነገር ይኖራል፤ ግን እምነቱ ያለው ሰው በፅናት በሠላማዊ ትግል በሕጋዊ መንገድ ለመታገል ቆርጦ ከተነሳ ጊዜ ይፈጅ ይሆናል እንጂ ሠላማዊ ትግሉ አልሠራም የምንልበት ምንም ምክንያት የለም። ሁላችንም በግልጽ ማወቅ ያለብን ሠላማዊና የትጥቅ ትግል ዓላማዎች በጣም የተለያዩ መሆናቸው ነው። የሠላማዊ ትግል ዓላማ የኢትዮጵያን ህዝብ የሥልጣን ባለቤት እስኪሆን ድረስ እንዲታገል ማድረግ ነው፤ የትጥቅ ትግሉ ግን አንድ ቡድን ፈጥሮ፣ ጠመንጃ አስይዞ፣ በጠመንጃ ታግሎ፣ የሚገድለውን ገድሎ፣ ወንበሩን ለመያዝ ነው፣ ወያኔ በዛ መንገድ ነው ሥልጣን የያዘው። እኛ የምንፈልገው የኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ የሥልጣን ባለቤት የሚሆንበትና ሥልጣን የመውጫው ዘዴ ያለ ጠመንጃ እንዲሆን ነው።

 

በሠላማዊ ትግል ህዝብን የሥልጣን ባለቤት ለማድረግ መንቀሳቀሻ ቀዳዳ ያስፈልጋል፤ ለምሳሌ ነፃ የሆኑ የመገናኛ ብዙኀንና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች (መያዶች) ናቸው። አሁን ባለው የኢትዮጵያ ሁኔታ እነዚህ ነፃነቶች የሉም የሚል መደምደሚያ ላይ የደረሱ አሉ። በዚህ ሁኔታ ሠላማዊ ትግሉ ዋጋ ይኖረዋል?

 

ነፃነት የለም ካልን የምንታገለው ለነፃነት ነው፤ መብቶች ተገድበዋል ካልን እነዛ የተገደቡ መብቶች እንዲለቀቁ ነው። እነዚያ መብቶች በሕግ የተቀመጡ ናቸው። በሕግ በኩል ምንም ችግር የለበትም። ሕገ መንግሥቱ ማናቸውንም ዓይነት የሰብዓዊ፣ የፖለቲካና የኢኮኖሚ መብቶች ይፈቅዳል፤ እነዛን በሕግ የተሰጡንን መብቶች በተግባር ለማሳየት እንቢ ከሚለው ጋር በግድ መታገል፤ በሕግና በሠላም ያንን እናግኝ ማለት ነው።

 

ለምሳሌ በውጭ ሀገር ሆነው የሠላማዊ ትግል አብቅቶለታል፣ የሠላማዊ ትግል መድረኩ ጠቧል የሚሉ ሰዎች 15 ሺህ ኪሎ ሜትር ርቀው፣ አንድ ትልቅ መንግሥት የሙጥኝ ብለው ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ጋዜጦች ሃሳባቸውን ይገልፃሉ። ይኼ እነሱ የሚሉትን እና የሚያደርጉትን የሚቃረን ነው። በ15 ሺህ ኪሎ ሜትር ርቀት በኢትዮጵያ ውስጥ ሃሳባቸውን መግለጽ ከቻሉ ትንሽ ቀዳዳ አለ ማለት ነው። ያንን ቀዳዳ በሠላማዊና በሕጋዊ መንገድ ማስፋት ይቻላል። ዞሮ ዞሮ እኔ ለነፃነቴ የተፈለገውን ዓይነት መሥዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ልሆን እችላለሁ። አንዳንድ ጊዜ ዜጋ ነኝ አይደለሁም ብዬ ግራ የሚገባኝ ጊዜ አለ። ለምሳሌ ትናንትና ለመኖሪያ ቤቴ ለምጠቀመው ውሃ 960 ብር ክፈል አሉኝ፤ እኔ ለቤንዚን እንኳን እንደዚህ ዓይነት ገንዘብ አላወጣም የለኝምም። ውሃ ምን ያህል ቢወደድ ነው ወይስ ሆን ተብሎ ውሃም፤ መብራትም፣ ኢንተርኔትም የማጥቂያ መሣሪያ እየሆነ ነው? ይኼን ሁሉ ኢፍትሃዊነት በምንችለውና በሕጋዊ መንገድ በአንድነት መታገል አለብን። ሁላችንም ጋር እስኪደርስ ድረስ መጠበቅ የለብንም።

 

አንዳንዴም ደግሞ በራሳችን እስኪደርስ መጠበቅ ሊኖርብን ይችላል። ለምሳሌ አማረ አረጋዊ እስከ ዛሬ ሰዎች ሲታሰሩ ያስብ ከነበረው፣ ዛሬ ጎንደር በሚገኘው እስር ቤት ቁጭ ብሎ የሚያስበው የተለየ ነገር ይሆናል፣ ይኼ ደግሞ መጥፎ ነው። እስኪደርስብን መጠበቅ የለብንም፤ ሳይደርስብን ሊደርስብን ይችላል ብለን፣ ያንዱ መብት ሲነካ የሌላውም እንደተነካበት ሊሰማን ያስፈልጋል። ሠላማዊና ሕጋዊ ትግሉ የሚሰምረው ሁሉም ሰው መብቶች ተጓደሉባቸው ብሎ ለሚያምንባቸው ሰዎች ሲታገልና ሃሳቡን ሲገልጽ ነው። እንዲህ መተሳሰብ እስካልቻልን ድረስ ግፍና በደል በያንዳንዳችን ላይ እስኪደርስ ድረስ ከጠበቅን፤ ይኼ የሠላማዊ ትግሉ ድካም ሳይሆን የመብት ግንዛቤ ድካም ነው። ሰዎች ስለ መብታቸው፣ ስለነፃነታቸው፣ ስለ ዜግነታቸው በደንብ ካወቁ ለመብቶቻቸው ይታገላሉ። በሠላማዊና ሕጋዊ መንገድ ሕጉን እየጠቀሱ መታገል አለባቸው። በርግጥ ከቅድመ አያቱና፣ ከአያቱ ጀምሮ በአገዛዝ የኖረ ህዝብ፣ ትንሽ ባለሥልጣን ሁሉ ሲደበድበው አሜን ብሎ የማሰብ ባህሉ ግንዛቤ እስኪያገኝ ድረስ ነው እንጂ ሠላማዊ ትግሉ በሁለትና በሦስት ሰዎች የሚሆን ነገር አይደለም። ሠላማዊ ትግሉ አይሆንም የሚባለው ከአሜሪካ ወይም ከአውሮፓ አይደለም። ሠላማዊ ትግሉ ይሠራል አይሠራም ብሎ መፈተን የሚቻለው መድረኩ እዚሁ (ሀገር ውስጥ) ነው።

 

ከላይ እንደጠቀሱልን ኢትዮጵያ ውስጥ ሕጎቹ አሉ እንዲፈፀሙ መታገል ነው ብለዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ሕጎችም እየተሻሻሉ ነው በሚል እየተቀየሩ ናቸው። ለምሳሌ የፕሬስ ሕግ፣ የመያዶች፣ የባንኮች፣ ... ይኼ ሁኔታ ሠላማዊ ትግሉን አያስቸግረውም?

 

ሕገመንግሥቱ፣ ”ከዚህ ሕገመንግሥት ተቃራኒ የሆነ ሕግ ሊወጣ አይችልም” ይላል። ከሕገ መንግሥቱ ተቃራኒ የሆነ ሕግ ቢወጣ፣ ሕግ ነው ብለን ልንቀበለው አንችልም፤ ከሠላማዊ ትግሉም አንዱ ይኼ ነው። ይኼ ሕግ ሕገመንግሥቱን ይቃረናል። ስለዚህ ለኛ ሕግ አይደለም አንቀበለውም። አንቀበለውም ብለንስ ምን እናደርጋለን? ሠላማዊ ትግሉ ይኼንን ጥያቄ ነው መመለስ ያለበት።

 

ውጪ የሚገኙ አብዛኞቹ ኢትዮጵያዊያን የትጥቅ ትግሉን እንደሚደገፉ ይነገራል፤ እርስዎ ደግሞ በቅርቡ ወደ አሜሪካ ኼደው ነበር፤ ጉዳዩን እንዴት አዩት?

 

ይኼ አዲስ ነገር አይደለም ባለፉት 15 ዓመታት ውስጥ አይቼዋለሁ። ለትጥቅ ትግል ብዙ ፉከራና ሽለላ ሲደረግ ነበር። ነገር ግን አንዳቸውም ወደ ሱዳን ጠረፍ የደረሱ አይመስለኝም። አንዳንዶቹም ትተውት ሠላማዊ ሥራቸውን እየሠሩ ነው። ለኔ እንደሚመስለኝ አንዳንዶቹ በቁጭት፣ በስሜትና በንዴት ወደዛ ኼደው ሊሆን ይችላል፤ አንዳንዴም ደግሞ ፉከራ ባህላችን ነው መፎከር፣ መሸለል እንፈልጋለን፣ በዛ ምክንያት ሊሆን ይችላል። እንደውም የገንዘብ መዋጮ በሚጠየቅበት ጊዜ ለሠላማዊ ትግል ከሚዋጣው ገንዘብ፣ ለትጥቅ ትግሉ በሚዋጣበት ጊዜ ይበልጥ የሰው እጅ የሚፈታ ይመስለኛል። ይኼ ግን ፊት ነው አሁን ሁሉንም አዩት አልሠራም። አሁን ያለው ሽለላ ብዙውን ሰው አያደናግረውም፤ ከዚህ በፊት አይቶታል ሰምቶታል፣ ምንም አዲስ የመጣለት ነገር የለምና።

 

በርግጥ አሁንም ውዥንብር አለ፣ ሠላማዊ ትግሉንም፣ የትጥቅ ትግሉንም እንደግፋለን የሚሉ አሉ። የትጥቅ ትግሉን እንዴት እንደሚደግፉት አላውቅም፤ አንድም ከዛ ተነስቶ ወደ ሱዳን ጠረፍ ለመምጣት የሚፈልግ የለም። ገና እዚህ ሀገር የሚመለመሉ ሰዎች ተመልምለው፣ እነሱን ለማገዶ ለማቅረብ ካልሆነ በቀር ሌላ ምንም የሚያደርጉት ነገር የለም። በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ወጣቱ ቂል አይደለም። ዝም ብሎ ኼዶ ማገዶ ለመሆን አይፈልግም። ውስጥም ያሉት ቢሆኑ ባለፉት 15 እና 16 ዓመታት የሚያዋጣና የማያዋጣውን አይተዋል። ንዴት ሲመጣ መፎከርና መሸለል ይቀናን ይሆናል። ባህላችን ነውና ከዛ ውጭ ምንም ነገር ሊሆን የሚችል አይመስለኝም።

 

አብዛኞዎቹ በስደት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በፖለቲካው ጉዳይ ደመ ሞቃት ናቸው ይባላል?

 

ደመ ሞቃት የመሆን ነገር አይደለም፣ ሁኔታዎች በጣም የተለዩ ናቸው። ውጭ ሀገር ሲኮን ነፃነት የኖረ አይነት ስሜት ይሰማል። ለምሳሌ አሜሪካን ሀገር ስለ ትጥቅ ትግል ማውራት፣ መለፍለፍ የፈለጉትን ያህል መናገር ይቻላል፤ ነገር ግን ወደ ትጥቅ ትግል ለመሄድ አንድ እርምጃ ቢታሰብ ችግር ይመጣል፣ በተግባር የሚፈቀድ አይደለምና። ሁልጊዜም ነፃነት በኃላፊነት የተከበበ ነው፣ ኃላፊነት የሌለበት ነፃነት ስድነት ነው። ተነሱ፣ ተዋጉ፣ ... የሚባሉት ሰዎች እነማናቸው? እነማንናቸው የሚሞቱት? እነማናቸው የሚገደሉት? ይኼ ትልቅ ኃላፊነትን የሚጠይቅ ነው። ሩቅ ሆኖ በሰው ሕይወት ላይ መፍረድ ተገቢ አይደለም። በራስም ሕይወት ላይ ቢሆን እንደዚህ ዓይነት ፍርድ መስጠት ተገቢ አይደለም። እዚህ ነፃነት የለም፣ ያለችው ነፃነት በጠመንጃ ተይዛለች፤ በዚያች በታፈነች ነፃነት ውስጥ ነው የምንነጋገረው። በተቻለን መጠን ልናሰፋው እንሞክራለን እነሱ ደግሞ በጠመንጃ፣ በጥይት ሊያፍኑትና ሊያጠቡት ይፈልጋሉ። እነርሱ በሰው ላይ የሚደርሰውን አያዩትም፣ አይሰሙትም፣ አይሰማቸውም ሩቅ ናቸው። እኔ በራሴ ላይ ባይደርስብኝ በሌሎች ላይ ሲደርስ ሳየው ይሰማኛል እና እጠነቀቃለሁ። በኔ ላይ እንዲሆን የማልፈልገውን በሌሎች ላይ እንዲሆን አልፈልግም።

 

እዚህ እየተያየን፣ እየተነጋገርን የሚሆነውን ነገር እያየን ነው የምንኼደው፤ እነሱ ከዚህ ውጭ ርቀት ላይ ናቸው። ንዴትና ቂም አለባቸው፣ አንዳንዶቹ በቀል ይፈልጋሉ። ሩቅ በመሆናቸው ያለምንም ገደብ፣ የፈለጉትን ነገር መናገር ይችላሉ። ነገር ግን ለሀገራቸው የሚያስቡ በወገኖቻቸው ላይ አደጋና ችግር እንዲደርስ መፈለግ ያለባቸው አይመስለኝም። ራሳቸውን ከአደጋ ከልለው፣ ሩቅ ሆነው ሌሎችን ”በርቱ ነፃነት ለማግኘት የሚያዋጣው ይኼ ብቻ ነው!” ማለት ምን ማለት ነው?

 

እነሱ አንድ ትልቅ መንግሥት የሙጥኝ ብለው፣ እኔ የሙጥኝ ያልኩት አንድ መንግሥት ሳይኖር ተነስ ታጠቅ ብለው የሚመክሩኝ የፍቅር ነው ወይስ የጠብ? ይኼንን ወጣቱ ማሰብ መቻል አለበት። የሚያዋጣው ማሰብ ነው። መማር እያቃተን ነው እንጂ የአፄ ኃ/ሥላሴ መንግሥትና የደርግ መንግሥት ሲወድቁ አስፈፃሚዎቻቸውም አብረው ወድቀዋል። በሠላማዊ መንገድ ለነፃነትና ለመብቶች የሚታገሉ ሰዎች፣ በደህንነት ውስጥ ላሉት ፖሊሶችም፣ ለዓቃቤ ሕግም፣ ለዳኞችም፣ ለትልልቆቹም ባለሥልጣኖች ነፃነት ነው የሚታገሉት። ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች ሁሉ ነፃ አይደሉም። ግፍን ማካኼድ ነፃነት አይደለም፣ ከሕግ ውጭ መሥራት ነፃነት አይደለም። የሥልጣን ብልግና ነው። ትግላችን የሁሉም ኢትዮጵያዊ መብት ተከብሮ፣ በሠላም የምንኖርበት ሀገር ለመመሥረት ነው።

 

የግንቦት 7 ንቅናቄ ጫካ ገብተው ከሚታገሉ ቡድኖች ጋር በመቀላቀል ሊሠራ እንደሚችል መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከእነዚህ ቡድኖች ጋር መሥራቱ ውጤት ያስገኛል ብለው ያምናሉ?

 

እነዚህ ኃይሎች ላለፉት 15 እና 16 ዓመታት ምን አደረጉ? ምን ውጤት አስገኙ? በዚህ ጊዜ ውስጥ የሠላማዊ ትግል ውጤት ከዛ በላይ ውጤት አላስገኘም? ሚያዝያ 30ና የምርጫው ቀን ግንቦት 7 የታየው የሠላማዊ ትግል ውጤት የበለጠ አይደለም? እነሱ ምን አሳዩ? እርግጥ ጊዜ ይፈጃል ሻዕቢያ 30 ዓመት ፈጀብን ይላል። ወያኔ 15 ዓመት ፈጀብኝ ይላል፣ ያ የተለየ ዘመን ነው።

 

አሁን ዘመኑም የዓለምም ሁኔታ የተለየ ነው። ይኼ ይቻል ይሆን፣ አይቻል ይሆን አላውቅም። ግን አንድ የማይካድ ነገር አለ፤ ከሠላማዊ ትግል በቀር ሌላ ምንም የሚያዋጣ ነገር የለም የምንል ሰዎች እና ለዚህ የምንታገል ሰዎች እየተዳከምን በሄድን መጠን፣ የትጥቅ ትግሉን የሚፈልጉ ሰዎች ደግሞ እየተጠናከሩ ይኼዳሉ። የዓለም ሁኔታ ተለዋዋጭነትና የአካባቢያችን ተለዋዋጭነት ተደምሮ ምን ሊያስከትል እንደሚችል አናውቅም። ሌላው ቀርቶ ሶማሊያ በመውረር የፈጠርነው ጦስ ምን እንደሚያስከትል አናውቅም። ስለዚህ እንደው ማሰብ ችለን አዕምሮአችን እና መንፈሣችን ከስሜታችን በልጠው በመተማመን፣ መወያየትና አንድ መፍትሔ ለመፍጠር ካልቻልን እየተበላሸ ሊሄድ እንደሚችል ጥርጣሬ አለኝ። ያዋጣም አያዋጣም አንድ ሰው በንዴት የሚወስነው ነገር፣ ነገ ከነገ ወዲያ ነፃነቱ በጠበበ መጠን ለትጥቅ ትግል አመቺ ሁኔታ ይፈጠራል። ይኼ ምንጊዜም ቢሆን ይጠቅማል ማለት አይደለም።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!