'ለተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጥሪ የማቀርበው ነገር፤ ህዝቡ በምርጫ እንዳይሳተፍ የሚከለክል መልዕክት ማስተላለፍ አይገባቸውም'

 

Ana Gomesበአውሮፓ ፓርላማ የሶሻሊስት ፓርቲ አባልና በኢትዮጵያ ግንቦት 7 ቀን 1997 ዓ.ም. ተካኺዶ በነበረው ምርጫ የአውሮፓ ምርጫ ታዛቢ ልዑካን ሊቀመንበር የነበሩት አና ጐሜዝ በቅርቡ ከዩሮ ጋዜጣ ጋር በኢትዮጵያ ስላለው የዲሞክራሲ ሁኔታ፣ ስለኦነግ (ስለየኦሮሞ ነፃነት ግንባር)፣ በቀጠናው ስላለው መረጋጋትና ”የቅርብ ወዳጃቸው ናቸው” ተብለው ስለሚጠቀሱት በዶ/ር ብርሀኑ ነጋ ስለተቋቋመው የግንቦት 7 ንቅናቄ ዙሪያ ያደረጉትን ቃለ-ምልልስ ለኢትዮጵያውያን አንባብያን በሚመች መልኩ በአማርኛ ቋንቋ ተርጉመን አቅርበነዋል።

 

እንደሚታወቀው የግንቦት 7 1997 ዓ.ም. ምርጫ ውዝግብ ተከትሎ፣ 193 የሚጠጉ ሰዎች ሞት የተነሳ የአውሮፓ ፓርላማ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ማዕቀብ እንዲደረግ ጥሪ አቅርቦ ነበረ። ፓርላማው ለምን ይህን የማዕቀብ ጥሪ ችላ አለው?

 

እንደማስበው የአውሮፓ ኮሚሽን ጥሪውን ችላ አላለም፤ በወቅቱ ለኢትዮጵያ የዕርዳታ አሰጣጥ ሁኔታ ተቀይሮ ነበር። ነገር ግን ጊዜ በሄደ ቁጥር ነገሮች እንደወትሮ ነው የተመለሱት፤ እንደውም የአውሮፓ ሕብረት ለኢትዮጵያ መንግሥት የሚደረገውን ድጋፍ የቀጠለበትና የጨመረበት ሁኔታ ነው የሚታየው። እኛ እንደምናውቀው የኢትዮጵያ መንግሥት የህዝቡን ፍላጐት የጣሰና ሙሉ በሙሉ በገዥው ፓርቲ ቁጥጥር ስር የወደቀ መንግሥት ነው። በአውሮፓ ኮሚሽን ወይም መንግሥታት ውስጥ ኢትዮጵያን በተመለከተ የአስመሳይነት ሥራ እየተሠራ ይገኛል። በአፍሪካ የዲሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶችን ለማራመድ የአውሮፓ ኮሚሽን መሠረታዊ እሴቶችና ዓላማዎች ወጥነት ይጐድላቸዋል። ይህ ድርጊት በኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ በአፍሪካ በአጠቃላይ የአውሮፓን ተዓማኒነት ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው። እኔንም በጣም የሚያሳዝነኝ ድርጊት ነው።

 

እንደተጠቀሱት የአውሮፓ አስመሳይነት (Hypocrisy) በሁሉም የዓለማችን ክፍል የሚታይ ነው። ለምሳሌ ለምዕራብ ሀገሮች ቅርበት ያላቸው እንደ ሳዑዲ ዐረቢያ በመሳሰሉ ሀገራት የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ይስተዋላል። በሌላ በኩል ምዕራባውያን በዝምባብዌ ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ ላይ ያነጣጠረ ዘመቻ እያካሄዱ ይገኛሉ። በአንፃሩ ምንም ምርጫ ያላደረጉ ወይም የምርጫ ውጤትን ያጭበረበሩና የሰው ልጆች ሕይወት ስለጠፋበት ሀገራት እምብዛም ትኩረት ሲሰጡ አይስተዋሉም ይህ አስመሳይነት አልበዛም?

 

የሰብዓዊ መብት ጥሰትን በተመለከተ የፕሬዝዳንት ቡሽ፣ የአውሮፓ መንግሥታትና ተቋማት ትልቅ ሽንፈት ነው። ምክንያቱም ሁኔታውን ስንመለከተው በዓለም አቀፍ ሕግና የሰብዓዊ መብቶችን ለማስከበር ከሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ጋር ይቃረናል። ስለዚህም ነው በጥያቄህ ውስጥ እንደጠቀስከው አይነት ምሳሌዎችና ኢትዮጵያ ውስጥ እየታዘብነው ያለው ሁኔታ ተመሳሳይ ነው። ለምሳሌ ባለፈው ጊዜ የቡድን ስምንት ስብሰባ ጃፓን በተካሄደበት ወቅት በዝምባብዌ መንግሥት ላይ ማዕቀብ ለማድረግ ጥሪ ቀርቦ ነበር። ማዕቀቡ የሙጋቤን ፈላጭ ቆራጭ መንግሥት ለማስወገድ ስለሚረዳ ተገቢ ነው። ነገር ግን በዚህ ጉባዔ ላይ ልክ እንደ የተከበረ አፍሪካዊ መሪ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አንዱ ተጋባዥ መሪ ነበሩ። መለስ ዜናዊ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊሆኑ ይችላሉ፤ ነገር ግን በምርጫው ወቅት እንዳየሁት በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ተዓማኒነት የላቸውም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዓለም ታላቅ መሪዎች ፊት ሊሸለሙ ወይም ሊቀርቡ አይገባቸውም። ምክንያቱም ፈላጭ ቆራጭ መሪ ከመሆናቸውም ባሻገር የሰው ሀገር ማለትም ሶማሊያን የወረሩ ናቸው። ስለዚህ በዓለማችን ላይ በግልፅ የሚታይ ተቃርኖ ወይም ወጥነት የሌለው አሠራር እየታየ ነው።

 

በአጠቃላይ ሲታይ በኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት ዓመታት የዲሞክራሲያዊ ሽግግር ሂደቱ እየተሻሻለ ነው ወይስ እየባሰበት ነው ይላሉ?

 

በዓለም ላይ ያለውን የዲሞክራሲያዊ ሽግግር ሥርዓት ስናይ የተለያዩ ሁኔታዎች አሉ። በኢትዮጵያ ግን በእርግጠኝነት እየተሻሻለ አይደለም ማለት ይቻላል። በአንድ በኩል የኢትዮጵያ ህዝብ ለዲሞክራሲና ለለውጥ ያለው ፍላጐት ከፍተኛ ነው። እ.ኤ.አ. በ2005 ዓ.ም. በተካሄደው ምርጫ (ምርጫ 97) በሠላማዊ ሁኔታ ነው ህዝቡ የተሳተፈው። ነገር ግን ያ ሁሉ ተስፋ በመለስ ዜናዊ ሥርዓት መና ሆኖ ቀርቷል። ስለዚህ በኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ሂደት አልተሻሻለም ማለት ይቻላል። አሁን የምናየው ሁኔታ የቡሽ አስተዳደር ማብቂያ የተቃረበበትና ከአዲሱ የአሜሪካን ፕሬዝዳንት ኦባማ አዲስ ዘመን የምናይበት ነው። አፍሪካዊ መሠረት ላልናቸው በፕሬዝዳንት ኦባማ ዘመን ዲሞክራሲና የሰብዓዊ መብት አያያዝና ጥበቃ በተመለከተ ለውጥ እንደምናይ ትልቅ ተስፋ አደርጋለሁ።

 

ከቡሽ አስተዳደር በፊት የነበሩት ባለሥልጣናት፣ የሰብዓዊ መብትና ዲሞክራሲን በተመለከተ መረጋጋት ማምጣት እንደሚችሉ ተናግረው ነበር። ታዛቢዎችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች፣ የቡሽ አስተዳደር በተፃራሪ ሲሠራ እንደነበር ይተቻሉ። በኦባማ አስተዳደር ምን ያህል ለውጥ ይመጣል ብለው ይጠብቃሉ?

 

እንደማስበው ማናቸውም ዕጩዎች በምርጫ ቢያሸንፉም በዓለም ዙሪያ ከፍተኛ ቀውስ ያስከተለው የቡሽ አስተዳደር ያከትማል። በኔ በእምነት የፕሬዝዳንት ኦባማን ስብዕናና የአፍሪካዊና እስያዊ ወይም ኢንዶኔዥያ ተቋዳሽ መሆናቸው ዩናይትድ ስቴትስ አመራር በኩል አፋጣኝ ለውጥ ማምጣት እንዳለበት እንዲገነዘቡ ይረዳቸዋል። ይህ ደግሞ የዲሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶች መሠረታዊ እሴቶችና ብሎም ፍትህ በዓለማችን ይበልጥ እንዲሠፍን ይረዳል። በዚህ ዓለም ዲሞክራሲያዊ ያልሆነ አሠራር ማየት አንሻም፣ ከመረጋጋት የተሻለ ብዬ የማምነው ዲሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶች ሲከበሩ ነው።

 

በብዙ ፎረሞች ተቃዋሚ የኢትዮጵያ ፓርቲዎች፣ በገዥው ፓርቲ ላይ ጫና ለማሳደር አንድ መሆን ወይም መተባበር እንዳለባቸው ሲናገሩ ይደመጣሉ። እውነታው ግን በተቃራኒ ነው። ኅብረት፣ ኦፌዲን እና ሌሎችም ተቃዋሚ ፓርቲዎች በፓርላማ ይገኛሉ። በሌላ በኩል ፓርላማ ያልገቡ የቅንጅት አመራር አባላት አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ መሥርተዋል። የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) በምርጫ አልተሳተፉም። አሁንም ቢሆን የቀድሞ ቅንጅትና አንድነት ፓርቲ አመራር አባላት በተለየዩ ፓርቲዎች በመቧደን እየተከፋፈሉ ይገኛሉ። ለምሣሌ አንዳኛው በኢንጂንየር ኃይሉ ሻውል አመራር ስር ሲሆን፣ ሌላኛው በአቶ አየለ ጫሚሶ ስር ይገኛል። በሌላ በኩል እንደ ኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጪ ግንባር ያሉ አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ከኤርትራ መንግሥት ጋር በመሥራት ላይ ይገኛሉ። እርስዎ እነዚህን ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች አንድ ለማድረግ ወይም ለማዋሃድ ምን እያደረጉ ይገኛሉ?

 

ኢትዮጵያውያን የዲሞክራሲ ሥርዓት ለመተግበር የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ከልቤ እደግፋለሁ። ነገር ግን እኔ የውጭ ዜጋ ነኝ። ማንም ሰው ኢትዮጵያውያን የሚፈልጉትን ለውጥ ከውጭ ሆኖ ማምጣት አይችልም ይህ ለኢትዮጵያውያን የተተወ ሥራ ነው፤ ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉ ሰዎች የአውሮፓ መንግሥታት በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጫና እንዲያሳድሩ ግፊት ሊያደርጉ ይችላሉ፤ ያም ሆነ ይህ የተወሰነ ኃላፊነት ነው። ዋናው ኃላፊነት የወደቀው በኢትዮጵያውያን ላይ ነው። የኔ አጋርነት በኢትዮጵያ ውስጥ ለዲሞክራሲ ሥርዓት ከሚታገሉ ኃይሎች ጋር ነው። አሁን ያለው በማንም ያልተወከለና የተናቀ ሥርዓት ህዝቡ ላይ እያደረገ ያለው ጭቆና ዋናው ምክንያት፤ የኢትዮጵያ ህዝብ በተለያየ ምክንያት በመከፋፈሉ ነው፤ ይህ አሳዛኝ ሁኔታ ነው በጣም አሳዛኝ። ኢትዮጵያውያን በርዕዮተ ዓለም፣ በፖለቲካና በብሔረሰብ ያላቸውን ልዩነት አቻችለው፣ በአንድነት ለዲሞክራሲ ሥርዓት ከተባበሩ የመለስን አስተዳደር በመጣል፣ በምትኩ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት ይችላሉ። እንደ ከዚህ ቀደም የአማራን የበላይነትና አብዛኛው የኢትዮጵያን ህዝብ የሚይዙት የኦሮሞን ህዝብ ሥጋት እየነጣጠልን የምንሰብክ ከሆነ የመለስ ፈላጭ ቆራጭ ሥርዓት እንዲቀጥል የሚያደርግ ጥሩ አማራጭ ነው። ስለዚህ ነው እኔ ኢትዮጵያውያን በዲሞክራሲ፣ መልካም አስተዳደር፣ ፍትህና ለሰብዓዊ መብቶች ክብርና ኢኮኖሚ ዙሪያ ባሉ አጀንዳዎች፣ በአንድነት እንዲቆሙ ጥሪ የማቀርበው። ስለሆነም እኔ በምንም ዓይነት ኢትዮጵያዊያን በራሳቸው የሚሠሩትን ሥራ መተካት አልችልም።

 

ከግንቦት 7 ቀን 1997 ዓ.ም. ምርጫ በፊት ኢሪን ለተባለ የተባበሩት መንግሥታት የዜና ምንጭ በሰጡት ቃለምልልስ/ ሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች የደጋፊዎቻቸውን ስሜትና ምኞት በማርገብ፣ የምርጫውን ውጤት እንደ እውነት እንደሚቀበሉ ተስፋ አድርገው ነበር። ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ገዥው ፓርቲ እርስዎ በወቅቱ ተስፋ አድርገው የነበረውን ተግባራዊ ያደረጉ ይመስልዎታል?

 

ደኅና! ከምርጫው በፊትና በኋላም እንደታየው የኢትዮጵያ ህዝብ በምርጫው በመሳተፍ ለዲሞክራሲ ያለውን ፍላጐትና ዝግጁነት አሳይቷል። በዚያ ወቅት አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ገዥው ፓርቲ የምርጫውን ሂደት ሊያዛባው እንደሚችል ያላቸውን ሥጋት ከመጀመሪያው ጀምሮ ሲነግሩኝ ነበር። በተወሰነ ደረጃ በወቅቱ ልክ ነበሩ። የአዲስ አበባ ምርጫ ውጤት እንደታወቀ ገዥው ፓርቲ የምርጫውን ውጤት በመላ ሀገሪቱ ማዛባት ጀመረ። መንግሥት የምርጫውን ውጤት ማጭበርበር ተከትሎ ለዲሞክራሲ የነበረው ተስፋ መና ሆነ። እኔ እንደማስበው ሥርዓቱ የህዝቡን ፍላጐት መቀልበሱ ለራሱ መጥፎ ነው፤ የአዲስ አበባ ምርጫ ውጤት የመላ ሀገሪቱ ምርጫ ውጤት ነፀብራቅ ነው። እርግጥ አንዳንድ ቦታ የውጤት ልዩነት ቢኖርም ማለቴ ነው። ስለዚህ ነው አሁንም ቢሆን ለተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጥሪ የማቀርበው ነገር፤ ህዝቡ በምርጫ እንዳይሳተፍ የሚከለክል መልዕክት ማስተላለፍ አይገባቸውም፣ ህዝቡ ለመምረጥ መጥቷል። ስለዚህ መለስ ህዝቡ ለዲሞክራሲ ዝግጁ አይደለም ብሎ መናገር አይችልም። የኢትዮጵያ ህዝብ ለዲሞክራሲ ያለውን ዝግጁነት በምርጫ ወቅት በብዛት በመገኘትና በመምረጥ አስመስክሯል።

 

አንዳንድ ታዛቢዎች በኢትዮጵያ የግል ፕሬስ አደጋ ውስጥ እንዳለ ይናገራሉ። ለዚህም የሚቀርበው ምክንያት የሕትመት ዋጋ መናር ነው። በዚህም ምክንያት በገዥው ፓርቲ አባላት የፋይናንስ ድጋፍ የማይደረግላቸው የፕሬስ ውጤቶች እየተዘጉ ይገኛሉ። ከዚህም በተጨማሪ የ2005 ምርጫን (ምርጫ 97ን) ተከትሎ ብዙ ጋዜጠኞች ላይ እንግልት ደርሷል። በቅርቡም አዲስ የፕሬስ ሕግ በፓርላማ ፀድቋል። ይህ ሕግ መንግሥት የሕትመት ውጤቶችን ከስርጭት በፊት እንዲያግድ ይፈቅድለታል። ታዛቢዎች ይህ እርምጃ መንግሥት ፕሬስን ለማፈን አዲስ ዓይነት እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ ይናገራሉ። የአውሮፓ ሕብረት በኢትዮጵያ የግሉን ፕሬስ ለመደገፍ የተለየ ዕቅድ ካለው ቢነግሩን?

 

በኢትዮጵያ ብዙም የግል ፕሬስ ውጤቶችን አናይም። ለዚህም ምክንያቱ መንግሥት የሚያሳድረው ጫና ነው። ይህን በተለያየ ደረጃ ከፋፍዬ ልነግርህ እችላለሁ። ከምርጫው በኋላ መንግሥት ባጠቃላይ የግል ፕሬስ አልፈቀደም። እኔ እስከ ማውቀው ድረስ መንግሥት ፕሬስን ለማፈን ውስብስብ አማራጮችን ይወስድ ነበር። ህዝቡ በኢንተርኔት መረጃ እንዳያገኝ በተለያዩ መንግሥታት ይደገፍ ነበር፤ እንደተነገረኝ መንግሥት የኮሚኒኬሽን ግንኙነቶችን ለማቆም የቻይናውያን ድጋፍ ተደርጐለታል። ስለዚህ ጥያቄው ለዲሞክራሲ ካለው ጠቀሜታ አንፃር ወሳኝ ነው። በኔ እምነት ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ለማስፋፋት በአውሮፓ የሚደረጉ የገንዘብ ድጋፎች የግልና ነፃ ፕሬስን ማካተት ይገባዋል። ይህ ድጋፍ ሊደረግላቸው የሚገቡ በሀገር ውስጥና ውጪ ላሉ የግል ፕሬስና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች ነው።

 

የሬዲዮ ሥርጭት ምናልባት ውጤታማ ነው ብዬ አምናለሁ። ምክንያቱም የራዲዮ ሥርጭት አድማሱ ሠፊ ነው። የራዲዮ ፕሮግራም የትም ሆነህ በአማርኛም ሆነ በሌላ ቋንቋ ልታስተላልፍ ትችላለህ። ይህ የገዥው ፓርቲ መረጃን ለማፈን ወይም ለማዛባት የሚያደርገውን ጥረት ያከሽፈዋል። ይህ ለአውሮፓ ሕብረትም ሆነ በአውሮፓ ፓርላማ በኩል ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ዲሞክራሲን ለመገንባት ከተፈለገ ነፃ የሆነ የመረጃ ፍሰትን መደገፍ ይገባል።

 

የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ፍጥጫ እንደቀጠለ ይገኛል፣ መፍትሔው ምንድነው ብለው ያስባሉ?

 

ለብዙ ኢትዮጵያውያን ሕመም ቢሆንም ኢትዮጵያ በባድመ ላይ የተሰጠውን ብይን መቀበል ይገባታል። ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ያላትን ግንኙነት በተመለከተ ሌሎች አማራጮች ማየት ይገባል። ይህ በኢትዮጵያና በኤርትራ መንግሥታት የሚወሰን ጉዳይ ነው። እኔ እንደማውቀው የኤርትራ መንግሥት ጨቋኝ ሥርዓት እንደሆነ ነው። የኤርትራ መንግሥት የጦርነት አባዜን እየተከተለ ይገኛል። በቀጠናው በብዙ ችግሮች እጁን እያስገባ ይገኛል። የኢትዮጵያ መንግሥት አርቢትሬሽኑን አለመቀበሉ የሚያበሳጭ ነው። ከዚህም በተጨማሪ የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ የአሜሪካንን መንግሥት በግንባር ቀደምትነት ጨምሮ በኢትዮጵያ ላይ ጫና አለማሳደራቸው እንዲሁ የሚያበሳጭ ጉዳይ ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያ የድንበር ውሳኔውን አለማክበሯ የጦርነቱ ሁኔታ በሁለቱ ሀገሮች እንዲቀጥል ዋነኛው ምክንያት ነው ብዬ አምናለሁ።

 

የኤርትራ መንግሥት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ በኤርትራና በጅቡቲ መካከል ያለውን ችግር ማጋነኑ፣ ድርጅቱ ኢትዮጵያ የባድመን ግዛት መቆጣጠሯን ማስቆም አለመቻሉን ለመሸፈን የሚያደርገው ጥረት ኤርትራን ለማሳጣት ነው ይላል።

 

እኔ ማለት የምችለው ኢትዮጵያ በመጀመሪያ ደረጃ የድንበሩን ውሳኔ መቀበል አለባት። የኤርትራን መንግሥት በአፍሪካ ቀንድ እያካሄደ ያለው ትርምስ በምንም ዓይነት ይቅርታ ሊደረግለት አይገባም። በመጀመሪያ ደረጃ የኤርትራ መንግሥት ልክ እንደ መለስ ሥርዓት ህዝቡን የሚጨቁን ሥርዓት ስለሆነ የሚደገፍ አይደለም። የኤርትራው መሪ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ውጥረት ህዝቡን ለመጨቆን ይጠቀምበታል። የኤርትራ መንግሥት በቀጠናው የሚታወቀው በአፍራሽ መልኩ እያካሄደ ባለው እንቅስቃሴ ነው። የኤርትራ መንግሥት በሱዳን፣ በሶማሊያና በተለያዩ በቀጠናው በሚገኙ ሀገሮች ጣልቃ እየገባ ይገኛል። እንዲሁም በሀገር ውስጥና በውጭ እያደረሰ ባለው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት መጠየቅ ይገባዋል።

 

አሁን አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ብሎ ራሱን የሰየመው የቀድሞ የቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞራክሲ ፓርቲ የመጪውን እ.ኤ.አ. 2010 (2002 ዓ.ም.) ምርጫ መሳተፍ የለበትም ይላሉ?

 

የመለስ ሥርዓት ሥልጣን ላይ እስካለ ድረስ በኢትዮጵያ ለሚደረግ ምርጫ እምነት የለኝም። የ2005 ምርጫ እንደሚያስተምረን የመለስ ዜናዊ ሥልጣን ላይ ለመቆየት የምርጫን ሂደት ለማዛባት ወደ ኋላ አላለም። አሁንም ቢሆን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ያካሂዳል የሚል እምነት የለኝም። እንደኔ እምነት የሽግግር መንግሥት ብቻ ነው በኢትዮጵያ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ሊያካሂድ የሚችለው።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!