የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ሊቀመንበር የሆኑትን ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን መታሰርና የፕ/ር መስፍን ወልደማርያምን በደህንነቶች መደብደብን አስመልክቶ የአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ ፕሮፌሠር መስፍን ወልደማርያምን ቃለምልልስ አድርጎላቸው ነበር። ቃለምልልሱን አቶ ግርማ ካሳ እንደሚከተለው በጽሑፍ አቀናብሮታል።

ሠለሞን ክፍሌ፦ ጤና ይስጥልኝ ፕሮፌሠር መስፍን እንደምን ዋሉ?

ፕ/ር መስፍን፦ ጤና ስጥልኝ ሠለሞን እንደምን ዋልክ?

ሠለሞን ክፍሌ፦ እስቲ በአጭሩ ምን እንደተፈጠረ ይግለጹልን ዛሬ።

ፕ/ር መስፍን፦ ዛሬ የሆነው ጠዋት ፓስተር ዳንኤል ቢሮ ብርቱካንና እኔ ከፓስተር ዳንኤል ጋር ሆነን ስንነጋገር ቆይተን ነበር። ስንወጣ ከግቢው በሩ ላይ ቆመን እየተነጋገርን እያለ አንድ አራት የሚሆኑ መኪናዎች መጡ። ተንደረደሩና ሰዎቹ አንድ አሥር የሚሆኑ ሰዎች ናቸው። እርሷን ከበቡና ይዘው ይገፏት ጀመር። “ለምን ትገፏታላችሁ? ሕጋዊ ሥርዓት ካለ አንድ ወረቀት አንድ ሰው ይዞ መጥቶ ሊወስዳት ይችላል” ስል ጊዜ በስድብ ናዳ ወረዱብኝ። እርሷን እየገፋፋ ሲወስዱ “እረ ‘ባካችህ ይሄ ትክክል አይደለም” ስላቸው አንድ ጀግና ወያኔ ወታደር በያዘው ጠመንጃ ሰደፍ የኋሊት እዚህ ፊኛዬ ላይ መታኝ። አልወደኩም ግን ተንገዳገድኩና ጫማዬም ወለቀ። እዚህ እታች ቋንጃዬንና ባቴን እስር አድርጎ ይዞኝ በኃይል ያመኛል አሁን። ሐኪም ጋር ሄድኩና አሳየሁት። “በዚያ የሚመጣ ስር የሚያልፍ አለና ኩላሊትህን ደግሞ ነክቶት እንደሆነ ነገ ትመረመራለህ” ብሎኝ ተመለስኩኝ።

ሠለሞን ክፍሌ፦ ወ/ት ብርቱካን አሁን ወዴት እንደተወሰዱ ይታወቃል?

ፕ/ር መስፍን፦ ከመሸ በኋላ የሰማሁት ቃሊቲ ወስደዋታል ሲሉ ነው።

ሠለሞን ክፍሌ፦ ለርሳቸው በፌደራል ፖሊስ የተሰጣቸው የጊዜ ገደብና ማስጠንቀቂያ ካበቃ በኋላ ትላንት ላናግራቸው ፈልጌ ለዛሬ ቀጠሮ ሰጥተውኝ ነበር የተለያየነው። አሁን መልሼ ስደውል ይሄንን ዜና ሰናሁ። እርስዎ ጉዳዩን በሚገባ ያውቃሉ ብዬ አምናለሁ። ፕሮፌሠር መስፍን የፖሊሱ ማስጠንቀቂያ ገደብ ምንጩ ምንድን ነው ይላሉ?

ፕ/ር መስፍን፦ እርሷ የሰጠችው መልስ የተናገረችው ነገር ምንም ስህተት የለበትም። በእውነት ለእውነት መመስክር የሚችሉ ሰዎች ደግሞ ቢኖሩ ፕሮፌሠር ኤፍሬምም ፓስተር ዳንኤልም ሌሎችም አሉ። እርሷ በሽምግልናው በኩል ተኬዶ ይቅርታ ጠየቅን ነው ያለችው። በሕጋዊ ሥርዓት ግን ሌላ አይነት መንገድ ነው ያለው። አንደኛ መጀመሪያ ውሳኔ መስጠት አለበት። ፍርድ መፈረድ አለበት። ይቅርታ ለመጠየቅ። እና ይሄ የተጀመረው ገና ገና ውሳኔ ብይንም ሳይሰጥ ነው። ፍርድ ከተፈረደ በኋላ እስረኞቹ ምንድን ነው የሚያደርጉት ቃሊቲ እንዳየነው? ፎርም አለ። ይቅርታ መጠየቅ ሲፈልጉ ፎርም ይሰጣቸዋል። የይቀርታ ኮሚቴ እስር ቤት ውስጥ አለ። ፍሮም ይሰጣቸዋል። አንድ አሥር ገጽ ይሆናል። ያንን ይሞላሉ። ያንን ሞልተው ይመልሳሉ። ሲመልሱ ለየቀበሌው ከጎረቤቶች ከሰዎች ከሚያወቋቸው ሰዎች አጣርቶ አስተያየት ሰብስቦ እንደገና መልስ ለእስር ቤቱ ይላካል። እስር ቤቱ ያንን ካየ በኋላ ወደ ይቅርታ ቦርድ የሚልከውን ይልካል። የሚያስቀረውን ያስቀራል። ይኼ ነው በይቅርታ ኮሚሽኑ የሚሄደው። እርሷ በሽምግልናው ነው የሄድነውና ይቅርታ የጠየቅነው ነው ያለችው።

ይሄ ትክክል ነው። ማንም የሚክደው ነገር አይደለም። እዚህ ነው እንግዲህ “ይሄንን አንቺ በሕጋዊ መንገድ ይቅርታ አልጠየኩም ብለሻል።” ያሉት። በሕጋዊው ሁለቱም ሕጋዊ ሆኗል ለነገሩ። ይሄም ሕጋዊ ነው። በይቅርታ ኮሚሽን በኩል ሄደ። ፕሬዝዳንቱ ጋር ደርሶ ነው ይቅርታው ተሰጠ የተባለው። እና ሕጉ ነጋሪት ጋዜጣ የሚያዘውን ሕጋዊ ሥርዓት አልተከተለም። የኛ በሌላ በኩል ነው የሄደው ነው እርሷ የምትለው። ደግሞ ሕጉን በሚገባ ታውቀዋለች።

ሠለሞን ክፍሌ፦ አዎ የሕግ ባለሞያ በመሆናቸው ያውቃሉ!

ፕ/ር መስፍን፦ የሕግ ባለሞያ ነች። ምንም ይቅርታ መጠየቋን አልካደችም። ችግሩ እንደው ዝም ብሎ “አያ ጅቦ ሳታመኻኝ ብላኝ” የሚለው አይነት ነገር ነው። ያም ከሆነ ሥርዓት ባለው መንገድ ሰዎቹ አሉ። እነዚያ ሰዎች ፕሮፌሠር ኤፍሬም አለ። ፓስተር ዳንኤል አለ። አትሌት የታወቀው ኃይሌ አለ። እነዚህ ሁሉ ያውቃሉ። የሆነውን ነገር የተደረገውን ነገር። እና ምንም የሚያስቸግር ነገር አልነበረም። እንደዚህ የሚያደርስ የሚያቃቅር ዱላም ጋር የሚያደርስ ነገር የለም። ግን እንግዲህ ፖሊስ ሆኗል ሁሉን ነገር የሚያደርገውና እየገባን በመሆኑ ይመስለኛል እዚህ ጋር የደረሱት።

ሠለሞን ክፍሌ፦ ፕሮፌሠር መስፍን ለሰጡኝ ማብራሪያ አመሰግናለሁ። እንዳሉት ሽማግሌዎቹንም ፈልገን ለማነጋገርና ማብራሪያ እንዲሰጡን ለማድረግ እንሞክራለን። እንደገና ለሰጡን ማብራሪያ አመሰግናለሁ። ደህና ያምሹ!

ፕ/ር መስፍን፦ እግዚአብሔር ይስጥልኝ!

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!