ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ

ቀደም ባሉት ዘመናት ወደ ውጭ ሀገር በተለያየ ምክንያት የተጓዙ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ወደ ሀገራቸው የሚመለሱበትን፤ የእናት ሀገራቸውን ምድር የሚረግጡበትን ቀናት ይቆጥሩና ይናፍቁ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን በዋናነት ወደ ውጪ ሀገር የሚሄዱት ለትምህርት ሲሆን የዚያን ዘመን ወጣት ትምህርቱን ጨርሶ በመመለስ የሀገሩን እና የሕዝቡን ውለታ ለመክፈል የነበረው ጉጉት ከፍተኛ ነበር፡፡ ተምሮ በውጪ ሀገር መቅረት ሀገርን እንደመክዳት የሚያስቆጥር በመሆኑ በኢትዮጵያውያን ህሊና ስደት ተቀባይነት አልነበረውም፡፡


ዛሬ ዛሬ ሁኔታዎች ሁሉ ተለዋውጠው የኢትዮጵያ ህዝብ እጣ ፋንታ ፍልሰትና ስደት ሆኗል፡፡ ስደት የማያባራ የኢትዮጵያውን የሕይወት ገጽታ ሆኗል፡፡ የገጠሩም የከተማውም ሰው ወደ ውጭ ሀገር ይሰደዳል፡፡ ወጣቶች ይሰደዳሉ፡፡ እህቶቻችን ይሰደዳሉ፡፡ ሕፃናት ጭምር በጉዲፈቻ ስም ይሰደዳሉ፡፡ሕጋዊበተባለውም ሆነ በሕገ-ወጥ መንግድ ሕዝባችን ወደ ውጭ ሀገር ይነጉዳል፡፡ በዚህ የተነሳም በወሊድ ምጣኔ ሳይሆን በሰደት ምክንያት አምራች የሆነው የህዝብ ቁጥር ሊቀንስባቸው ከሚችሉ ሀገሮች ኢትዮጵያ አንዷ ሆናለች፡፡


ለዚህ ሁሉ ማለቂያ የሌለው ስደት መንስኤው በደርግ ተጀምሮ በኢህዴግ መንግስት ተጠናክሮ የቀጠለው አምባገነናዊ አገዛዝ የፈጠረው አስከፊ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ፖሊሲ ውድቀት መሆኑ አይካድም፡፡ ዜጎች በሀገራችን ከተንሠራፋው ድህነትና ሥራ አጥነት በማምለጥ ሠርቶ ለማግኘትና የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ህይወት ለመለወጥ ስደትን ቢሹም ከኢኮኖሚያዊ ፍላጎት በስተጀርባ አምባገነናዊ የፖለቲካ ሥርዓቱ የወለዳቸው ችግሮቹ ለስደቱ መንስኤነት ዋነኛውን ሚና ይጫወታሉ፡፡


የሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነት አለመረጋገጥ፣ ለሕዝብ ፍላጎት ተገዢና ተጠያቂ መንግሥት አለመኖር፣ የሕግ የበላይነት አለመከበር፣ የፍትሕ፣ የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ እጦት፣ በዜጎች ላይ በቀበሌ ካድሬዎች የሚደርስ አፈናና ወከባ፣ ከመሬትና ከንብረት መፈናቀል እንዲሁም የኢህአዴግ የተሳሳተ የትምህርት ፖሊሲ ውጤት ለዜጎቻችን ስደትና ወጥቶ ላለመመለስ ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው፡፡


ባለንበት የግሎባላይዜሽን ዘመን የሰው ልጅ በተለያየ ምክንያት ከሀገር ወደ ሀገር በስፋት ይንቀሳቀሳል፡፡ ከሀገሩም ወጥቶ በተለያዩ ሀገሮች ኑሮውን መስርቶ ይኖራል፡፡ የየሀገሩ መንግሥታት በሌላ ሀገር የሚኖሩ ዜጎቻቸውን መብት ለማስከበር የሚከተሉት ፖሊሲና የሚወስዱት ዲፕሎማሲያዊ ርምጃ ዜጎቻቸውን የሚያኮራና የሚያስከብር ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በተቃራኒው የኛ ሀገር መንግሥት ግን በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የሚፈልጋቸው ለኢንቨስትመንት ለሚያውሉት ገንዘባቸው ካልሆነ በስተቀር በሰው ሀገር ለሚደርስባቸው ውርደትና አስከፊ ሰቆቃ መድህን ሲሆናቸው አይታይም፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት በሊባኖስ በአሠሪዋ ስቃይ የደረሰባትና ራሷን ያጠፋችው የዓለም ደቻሳ ሁኔታ የኢትዮጵያውያንን አንገት ያስደፋ ሲሆን መንግሥት ለዜጎቹ ህልውናና ክብር ደንታ ቢስ መሆኑን በገሀድ አስመስክሯል፡፡


በሌላም በኩል ዜጎቹ በሕገ-ወጥ ደላሎች አማካይነት በሁሉም የጎረቤት አገሮች በኩል ወደ ተለያዩ ሀገራት በመሰደድ መጉላላትና አደጋ ሲደርስባቸው የኢህአዴግ መንግሥት የሕገ-ወጥ ደላሎች ቁጥር መጨመሩን በሚዲያው ከሚነግረን በቀር ጉዳዬ ብሎ ችግሩን ከምንጩ ለመቅረፍ የሚወስደው እርምጃ ባለመኖሩ መንግሥታዊ ኃላፊነቱን መወጣት ያቃተው መሆኑ በግልፅ ታይቶአል፡፡


በኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ በየሀገሩ የሚደርሰው ሰቆቃ አዲስ ባይሆንም ሰሞኑን በማዕከላዊ ታንዛኒያ በጫካ ውስጥ ተጥለው የተገኙ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ እጅግ በጣም አሳዛኝና አስደንጋጭ ነው፡፡ እነዚህ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከሀገራቸው ከወጡ በኋላ በማላዊ አቆራርጠው ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመግባት ሲሉ በኮንቴይነር ተጭነው በታንዛኒያ በኩል ሲጓዙ አየር አጥተው በመታፈናቸው 43 ሕይወታቸው ሲያልፍ በርካቶቹ ለጉዳት ተዳርገዋል፡፡ ይህ ድርጊት የኢህአዴግ መንግሥት በካድሬያዊ የአፈና አገዛዙ ከቀዬአቸው እያፈናቀለ በሰው ሀገር ለስቃይ የሚዳርጋቸው ዜጎች ስፍር ቁጥር የሌለው መሆኑን ማሳያ ነው፡፡


መንግስት ይህ አልበቃ ብሎት በሞኖፖል በሚቆጣጠረው ኢቲቪ በሟቾች ቀብር ስነሰርዓት አስታኮ በሀገሪቱ ስለአለው ልማት፣ ልማቱን ተከትሎ ስለአለው ፍሰሃና ደስታ ፕሮፓጋንዳ በመንዛት ዜጎችን ለስደት የሚያበቃቸውን ዋናኛ መንስዔ ለመደበቅ ሲዋትት፤በተጎጂዎችም ላይ ሲያላግጥ ማየት አሳፈሪ ክስተት ሆኖ አግኝተነዋል፡፡


አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ወዳጅ ዘመዶች መጽናናትን ይመኛል፡፡ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ የሚሆነው የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እውን እስኪሆን ድረስም ትግሉን ከህዝቡ ጋር አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡


ከሁሉም በላይ ለዜጎች መፈናቀል፣ ፍልሰትና ስደት መንስኤ የሆኑ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ችግሮች እንዲወገዱ መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማክበርና ለማስከበር እንዲሁም መልካም አስተዳደርንና ፍትሕን ለማረጋገጥ የሚያስችል እርምጃ በአፋጣኝ እንዲወሰድ ፓርቲያችን በአጽንኦት ይጠይቃል፡፡


በመጨረሻም ሕዝባችን መንግሥት ለዜጎች ሰብአዊና ደሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ትኩረት ሰጥቶ እንዲንቀሳቀስና የሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነትን እንዲያረጋግጥ አስፈላጊውን ጫና እንዲያደርግ ጥሪያችንን እናሰተላልፋለን፡፡


አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)
ሐምሌ 4 ቀን 2ዐዐ4 .
አዲስ አበባ

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!