UDJ አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) ከአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) የተሰጠ መግለጫ

ሐምሌ 6 ቀን 2004 ዓ.ም. በሁላችንም ዘንድ ይጠበቅ የነበረው በእነ አንዱዓለም አራጌ ፋይል ክስ የተመሰረተባቸው ወንድሞቻችን ላይ ከ13 ዓመት እስከ እድሜ ልክ የሚደርስ የቅጣት ውሳኔ ተላልፎባቸዋል። አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ ቀደም ሲል በሰጠው መግለጫ ግልፅ እንዳደረገው አብዩ ጉዳይ በፍርድ ቤት የሚሰጠው የቅጣት ውሳኔ ክብደትና ቅለት ሳይሆን ጥፋተኛ መባልና ያለመባላቸው ላይ እንደነበር ማስታወስ ተገቢ ነው።

 

 

ፍርድ ቤቱ የሰጠው የቅጣት መጠን የሚያስተላልፈው መልዕክት ካለ የስርዓቱን ጨካኝነት እና ለስልጣኑ ስጋት ነው የሚለውን ማንኛውንም ዓይነት እንቅስቃሴ ከማፈን፤ የፍትሕ ሥርዓቱን በማንአለብኝነት በማጥቂያ መሣሪያነት ከመጠቀም ወደ ኋላ የማይል መሆኑን ነው። ኢህአዴግ ንጹሃን ዜጎችን ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ ተነስተዋል እያለ ይከስሳል። የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በማንአለብኝነት በመርገጥ ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱን እየናደ ያለው ግን እሱ ራሱ ነው።

 

የኢህአዴግ መንግሰት በሽብርተኝነት ስም ዜጎቸን ከማንኛውም ዓይነት ንቁ የፖለቲካ ተሳትፎ ለመገደብ ያለውን ቀርጠኝነት እንዲሁም በዓረብ ሀገራት የታየው ህዝባዊ እንቅስቃሴ በማነኛውም ሁኔታ እንዳይነሳ የያዘው አቅጣጫ አካል መሆኑን ፍርድ ቤቱ ከሰጠው ትንተና ተረድተናል። በአብዛኛዎቹ ተከሳሾች ላይ ለፍርድ ቤት የቀረቡት ማስረጃዎች ከፍተኛ ችሎታና ልምድ አላቸው በሚባሉ የህግ ባለሞያዎች ሲመዘኑ እስከ እድሜ ልክ የሚያስቀጡ ሊሆኑ ቀርቶ ለምክርና ለተግሳፅ እንኳን በቂ እንዳልሆኑ እናምናለን። አሉ የተባሉት ማስረጃዎችም ቀደም ሲል በገዢው ሥርዓት እንደተለፈፈው የማስረጃ ክምር ሳይሆኑ ቅንጣት ታክል እንኳን የማሰረጃነት አቅም የሌላቸውና የተሳሳቱና ናቸው። የቀረቡት ማስረጃዎች በግልዕ ያረጋገጡት ሐቅ ግን መንግሥት ህዝቡ ከብሶት በመነሳት ወደ ህዝባዊ ንቅናቄ ቢገባ ስልጣኔ አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል በሚል ከልክ ያለፈ ስጋት ላይ መሆኑንና የፈራው እንዳይደርስም ምንም ዓይነት ህገ ወጥ ተግባር ከመፈፀም ወደኋላ የማይል መሆኑን፤ ይህንንም ተፈፃሚ ለማድረግ ዜጎችን ከስጋት ሊታደጉ የሚገባቸው ተቋማት ተባባሪ መሆናቸውን ጭምር ነው።

 

አስር ወር የፈጀው ፖሊስ፣ዓቃቢ ህግ፣ፍርድ ቤት እንዲሁም በመንግሰት በሞኖፖል የተያዘው ሚዲያ በመተጋገዝ በጋራ ሲያከናውኑት የነበረው የተቀነባበረ የኢፍትሐዊነት ድራማ የመጀመሪያው ምዕራፍ በፍርደገምድል የጥፋተኝነት ውሳኔና ጭካኔ በተመላበት የቅጣት ፍርድ ተጠናቋል። ይህ ማለት ግን የድራማው ደራሲ፤ አዘጋጅና መሪ የሆነው መንግሰት ዕቅዱ በአሰበው መንገድ ተሳክቶለታል ማለት አይደለም። ይልቁንም ለስርዓቱ ኢ-ዲሞክራሲያዊነት ማረጋገጫ በመስጠትና እውነተኛ ባህሪውን በማጋለጥ ውጤቱ ከዕቅዱ ውጭ ሆኖበታል። አንድነት ይህንን ሲል ያለምንም ማስረጃ አይደለም። ከነአንዱዓለም እስር በኋላ በርካታ ወጣቶች ከምንጊዜም በላይ ፓርቲያችንን በመቀላቀል ላይ ሲሆኑ፤ ቀደም ሲል የነበሩትም አባላት በከፍተኛ ተነሳሸነት ትግሉን ተያይዘውታል። ወጣቱም ሆነ ሕዝቡ በአጠቃላይ ሰላማዊ ትግል ፍሬ እያፈራ መሆኑን ከምንጊዜውም በላይ የተረዳንበት ወቅት ላይ ደርሰናል ብለን እናምናለን።

 

የኢህአዴግ መንግሥት የሰላማዊ ትግል መሰረት የሆኑትን በነፃነት የመደራጅትና ሃሳብን ያለምንም ገደብ የመግለፅ መብቶችን በማፈንና ገደብ በመጣል የሚያደርገው ጫና ቁርጠኛ የሰላማዊ ታጋዮችን ለበለጠ ትግል ሲያነሳሳ በአንፃሩ ደግሞ በአጥር ላይ የነበሩትን ዜጎች ወደ ሌሎች አማራጭ የትግል ስልቶች እየገፋቸው መሆኑን ማጤን ይገባዋል። ኢህአዴግ ይህን በማድረግ የሚያተርፈው ነገር ቢኖር ለልማት ሊውል ይችል የነበረውን ጉልበት፤ ጊዜና ሀብት ለአላሰፈላጊ ግብ ግብ አንዲያውል መገደዱና፤ ሀገራችን የምትሻውን ዲሞክራሲ በማራቅ የትንሳኤውን ጊዜ ማራዘም ብቻ ነው። የኢትዮጵያ ትንሣኤ ይዘገያል እንጂ ሀገራችን ዲሞክራሲ የሰፈነባትና ሰብዓዊ መብቶች የሚከበሩባት ሀገር እንደምትሆን ምንም ጥርጥር የለንም።

 

ይህንን ተሰፋችንን የሚያለመልመው ደግሞ በእስር ላይ የሚገኙ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን በፍርድ ሂደቱ እሰከ መጨረሻ የውሳኔ ዕለት ያሳዩት የመንፈስ ጥንካሬ ከእስር ቤት ውጭ ለምንገኝ አባላት ለቀጣይ ትግላችን ከፍተኛ ግብዓት እንደሚሆን፤ ማንኛውም ዓይነት እስርና እንግልትም የሰላማዊ ትግሉን አቅጣጫ እንደማያስቀይረው ለወዳጅም ለጠላትም ይፋ ያደረጉ መሆናቸው ነው። የአንድነት አባላትም በእነዚህ ጀግኖች የመንፈስ ጥንካሬ ይበልጥ ተበራትተው በመሥራት ፓርቲያችውን እንዲያጠናክሩ እያሳሰበ፤አንድነትም ጠንካራ አባላቱን ይዞ ከሌሎች ኣጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበርና በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡ አማራጭ መብቶችን ሁሉ አሟጥጦ በመጠቀም የሕዝቡን ዘርፈ ብዙ ሠላማዊ ትግል ወደ ፊት ለማራመድ አጋዥ ኃይል በመሆን የበኩሉን እስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ለሐቀኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ለማረጋገጥ ይወዳል።

 

ሀገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በብዙ ችግሮች ተወጥራ ትገኛለች። ከእነዚህ ችግሮች አንዱ የወጣቱ ሥራ አጥነት ነው። ወጣቶች ሥራ በማጣቸው ሥራ ፍለጋ ከአገር ውጭ አየተሰደዱና በየበረሃው እየወደቁ የአውሬ ሲሳይ ይሆናሉ። ባሕር ውስጥ ሰጥመው ያልቃሉ። በኮንተይነር ውስጥ ታፍገው ሲጓዙ አየር በማጣታቸው ህይወታቸው ያልፋል። በየደረሱበት የስደት አገርም መብታቸውን የሚያስከብርላቸውና ደህንነታቸውን የሚያስጠብቅላቸው መንግሥታዊ ወገን በማጣታቸው ለዘርፈ ብዙ መከራ ተጋልጠው እስከመሞት ይደርሳሉ። በየትምህርት ተቋማት ለዓመታት የሠለጠኑ ወጣቶች የመጨረሻ ዕድላቸው በኮብልሰቶን ሥራ መሰማራት ሆኗል።

 

ዛሬ በሀገራችን ሕገመንግሥቱን ተማምኖ ሠላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማድረግ የማይቻል ሆኗል። የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ሕልም ሆኖ ቀርትዋል። ሙስና የሥርዓቱ ዓይነተኛ ባህሪ ሆኗል። በመንግሥት ጣልቃ ገብነት ምክንያት የሃይማኖት ተቋማት ሕገ መንግሥቱ በሚሰጣቸው መብቶችና ዕምነታችው በሚፈቅድላችው መሠረት መንቀሳቀስ አልቻሉም። በአጭሩ ይህ ሥርዓት ሕዝቡ የእኔ ነው የማይለውና በላዩ ላይ በጉልበት የተጫነ ሥርዓት ሆኗል። ስለዚህ የኢትዮጵያ ሕዝብ በተደራጀም ሆነ በአልተደራጀ መልኩ የእሱ ያልሆነውንና በኃይል የተጫነውን ሥርዓት በሠላማዊና ሕጋዊ ትግል ወደሚገባው የታሪክ ሥፍራ ለመላክ ጠንክሮ መታገል አለበት። ሐቀኛና በሠላማዊና ሕጋዊ መንገድ የምንታገል ተቃዋሚ ኃይሎችም ይህን የሕዝብ ዓላማ ለማሳካት ተባብረን እንድንሠራ አንድነት ጥሪውን ያቀርባል።

 

በውጭው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ደጋፊዎቻችን ገዢው ሥርዓት የደገሰላቸውን መራራ የግፍ ፅዋ የሚጎነጩ ታጋዮች የሚያሳዩትን ጠንካራ የትግል መንፈስ ስንቅ በማድረገግ ሰላማዊ ትግላችንን ከምን ጊዜም በላይ አጠናክረን እንድንቀጥል ለትግሉ የሚያሰፈልገውን ዘርፈ ብዙ ድጋፋቸውን በከፍተኛ ደረጃ ያሳድጋሉ ብለን እናምናለን። በተለይ የታሳሪ ወንድሞቻችን ቤተሰቦችና ልጆቻቸው በግፈኛ ውሳኔ ምክንያት ችግር ላይ እንዳይወድቁ ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርጉልን በዚሁ አጋጣሚ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

 

ዓለምአቀፍ ህብረተሰብም፤ በተለይ ኃያላን መንግሥታትና ለጋሽ ተቋማት ለሥርዓቱ የሚሰጡት ድጋፍ በሕግ ሽፋን ለሕዝብ መጨቆኛና ማጥቂያ እየዋለ መሆኑን ተገንዝበው ሁኔታው እንዲለወጥ ከሕዝቡ ጎን በመቆም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉና ራሳቸውንም ከህሊና ወቀሳ እንዲያድኑ አበክረን እንጠይቃለን።

 

የታጋዮች እስር ለሰላማዊ ትግል አራማጆች የሰላማዊ ትግል ፍሬ ማፍራት ምልክት ሲሆን ለጨቋኞች ደግሞ የፍርሃታቸውን ጥግ የሚያሳይ ብቻ ነው የሚሆነው። በእስርና እንግልት ሠላማዊ ትግል እንደማይቀለበስ አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ በተለይም ለገዢው ፓርቲ ማረጋገጥ ይወዳል።

 

አንድነት ለለዲሞክረሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)

ሐምሌ 8 ቀን 2004 ዓ.ም.

አዲስ አበባ

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!