“ጎሰኝነትን ተዋጉ፤ ለሰብዓዊነት ቁሙ!” ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ

በሎንዶኑ የ2012 ኦሎምፒክ ተሳታፊ የሆኑ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች

ውድ የኢትዮጵያችን ልጆች አገራቸውን፣ ህዝባችውንና መላውን አፍሪካን በመወከል ላለፉት ሃምሳ ስድስት ዓመታት በኦሊምፒክ አደባባይ ያስመዘገቡት ወርቃማ ገድል የውርደታችን ማገገሚያና የበጎ መልካችን ማሳያ በመሆኑ ከቶውንም ከልባችን ሊሰረዝ የሚችል አይሆንም። በተለይም በአምባገነኖች በትር ተገፍተው አገራቸውን በመልቀቅ በስደት ለሚኖሩ የኢትዮጵያ ልጆች የኦሊምፒክ ተዋናይ ስፖርተኞቻችን የሃፍረታቸው ሁሉ ማርከሻና ኩራታቸው ሆነው ኖረዋል።

 

ኢትዮጵያና ኦሊምፒክ ላፍታም ሊነጣጠሉ የማይችሉበት በርካታ ምክንያቶች አሉ። ከሺዎች ዓመታት ታሪክና ከህዝብ ፍላጎት ጋር ግብግብ የገጠሙት የህወሃት/ኢህአዴግ መሪዎች እንደሚሉት ሳይሆን ድፍን ዓለም የሚስማማበት በወርቅ የተለበጠ ታሪክ ያስመዘገበው ሻምበል አበበ ቢቂላ በሮም ኦሊምፒክ በባዶ እግሩ ድል ሲጎናጸፍ ጸሃፍት ድሉን ጣሊያን በስርቆት ከወሰደው ታሪካዊው የአክሱም ሃውልት ጋር አያይዘውት ነበር። የአድዋ ድል ገድልም በድጋሚ መታደሱን የከተቡ ነበሩ።

 

ዛሬ በሎንደን ኦሊምፒክ ዋዜማ ስለ ኦሊምፒክ አምባሳደሮቻችን ስንናገር፣ አጃቢ ሆነው በልዑካንነት አብረው ስለሚዘምቱት የህወሃት/ኢህአዴግ ካድሬዎችና ስፖርቱንም በፖለቲካ ጠፍር ተብትበው “ከዓባይ ግድብ” ጋር በማያያዝ ድርጅታዊ ቁማር ስለሚቆምሩት እንዳልሆነ አበክረን ለማስታወቅ እንወዳለን፤ ምክንያቱም የህወሃት/ኢህአዴግ አመራሮችም ሆኑ ተከታዮች በየትኛውም መስፈርት ስለ ኦሊምፒክና ኦሊምፒዝም ባህር ጠለቅ ዓላማዎችና የተሳትፎው አስፈላጊነት ለመናገር ብቃት ስለሌላቸው ነው።

 

ኦሊምፒክ፣ ኦሊምፒዝም የዘርና የዘር መድሎዎ፣ የሃይማኖት፣ የፖለቲካ፣ የጾታ፣ ወዘተ ልዩነቶችን ወደጎን የሚያደርግ፣ መከፋፈልን የሚጠላ፣ የአንድነትና የሰላም ማጠናከሪያ መድረክ መሆኑ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ እውነት ነው። የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ /አኢጋን/ የሰው ልጆች ሁሉ ያለ አንዳች ልዩነት እኩል መሆን እንዳለባቸው አጉልቶ የሚያሳየው “ከጎሰኝነት ይልቅ ሰብዓዊነት” ከሚለው መርሁ በመነሳት ይህን የመልካም ምኞት መልዕክት ሲያውጅ የቆመለትና የተመሰረተበት ዓላማው ስለሚፈቅድለትና ስለሚያስገድደው በመሆኑ በሎንደን የኢትዮጵያችንን ክብር ከፍ ለማድረግ ለተሰለፋችሁ ሁሉ ታላቅ ድል እንመኛለን።

 

በሌላው ጎኑ የህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ ስፖርቱን መነገጃና የፖለቲካ መድረክ በማድረጉ ለተገፋችሁ፤ በተለያዩ አጋጣሚዎች አገራችሁን መወከል እየቻላችሁ በአድልዎ ምሬት አገራችሁን ለቃችሁ ለተሰደዳችሁ፣ ፈልጋችሁ ሳይሆን “አታስፈልጉም” ተብላችሁ ለሌላ አገር ህዝብና ሠንደቅ ዓላማ ለመሰለፍ የተገደዳችሁ ውድ የኢትዮጵያ ልጆች እናንተም ክብር የሚሰጣችሁ ኢትዮጵያውያን መሆናችሁን በዚህ አጋጣሚ ልንገልጽላችሁ እንወዳለን።

 

በ1956 ሜልቦርን ኦሊምፒክ የተጀመረው የጀግኖቻችን ተሳትፎ በሮም ኦሊምፒክ አበበ ቢቂላ በባዶ እግሩ አለምን ሁሉ በማስደመም የወርቅ ቅብ መቀባት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የሚጠሉንም ሆነ የሚወዱን፣ የሚገፉንም ሆነ የሚነቅፉን፣ የሚበታትኑንም ሆኑ የሚሰበስቡን … ሁሉም ባንድነት ከተቀመጡበት ተነስተው ለኢትዮጵያችን ዘምረዋል፤ ለሰንደቋ ሰግደዋል። ትንሽ ትልቅ ሳይባል የአፍሪካ ኩራት፣ የጥቁር ህዝቦች ሃብት፣ የነጠርን ጥቁሮች እንደሆን አምነው ተቀብለዋል። አበበ ቢቂላ፣ ማሞ ወልዴ፣ ማርሽ ቀያሪው ምሩጽ ይፍጠር፣ የሚነፍሰው መሃመድ ከድር፣ ዮሃንስ መሃመድ፣ የረጅም ጊዜ የማራቶን ባለቤት በላይነህ ዴንሳሞ፣ የጽናት ተምሳሌት ሃይሌ ገ/ስላሴ፣ ተስፈንጣሪዋ ደራርቱ ቱሉ፣ ጌጤ ዋሚ፣ አሰፋ መዝገቡ፣ ከ32 ዓመት በኋላ የማራቶንን ድል አገሩ የመለሰው የሲዲኒ ኦሊምፒክ ጀግና ገዛሃኝ አበራ፣ የሴቶች ማራቶን ባለድል ፋጡማ ሮባ፣ እንደ አቡ ሸማኔ የሚምዘገዘገው ቀነኒሳ በቀለ፣ በአብሪ ኮከብ የምትመሰለው ጥሩነሽ ዲባባ፣ የደፋር ልጅ ደፋር መሰረት፣ በቤጂንግ ኦሊምፒክ እንዳትሳተፍ የማይረሳ ወንጀል የተፈጸመባት ብርሃኔ አደሬ፣ ሚሊዮን ወልዴ፣ መሰለች መልካሙ፣ … በነዚህ ሁሉ ድል ኢትዮጵያ ነግሳለች፣ ተዘምሮላታል፣ ተወድሳለች፣ ቅኔ ተደርድሮላታል። ታሪክ በከበረው ኦሊምፒክ ተሳትፎዋ አንቱ ብሎ ተቀብሏታል።

 

አትሌቶችችን ከድካም ይልቅ የአገር ፍቅራቸው እየነደደ እንደዋላ እየተምዘገዘጉ በጨዋነት የሰላሙን ጦርነት በድል ሲወጡ ተምሳሌቱ ጎሰኝነት፣ ጠባብነት፣ አረመኔነት፣ የአገር ክህደት፣ አምባገነንነት ወዘተ ለማንጸባረቅ አይደለም። ዓላማቸውና ውስጣቸውን እየደቃ እንደ እሳተ ጎሞራ የሚያንተገትጋቸው የወገናቸው አደራ፣ የአንድነታቸው ምስጢር፣ ከጥንት ሲወርድ ሲወረድ የመጣው የቅድመ አያቶቻቸው የአሸናፊነት ታሪክ ስለሚያነቦገቡጋቸው እንጂ፤ ይህም ብቻ አይደለም ህወሃት/ኢህአዴግ ሸርሽሮ ሊጥለው ሌት ተቀን ጉልበቱንና ገንዘቡን ቢከሰክስም አልሆንልህ ያለውን የኢትዮጵያዊነትና የኢትዮጵያ ዘላለማዊነትና ለማሳየት ነው። ደራርቱ ቱሉ “ዓለም ሁሉ መዝሙራችንን እንዲዘምርና ሠንደቅ ዓላማችን ሲውለበለብ እንዲያይ ከማድረግ በላይ ምንም የሚያኮራ ነገር የለም” ስትል ተናግራ ነበር።

 

በውድድር ወቅት በተለይም የመጨረሻ ዙር አብሳሪ የሆነው ምልክት ከተሰጠ በኋላ እናቶች የምጥ ያህል ጭንቀት ውስጥ በመግባት ሲጸልዩና ሲሳሉ፣ ወንዶችም በጭንቀት ሲወጠሩ፣ ህዝብ ዓይኑን ድል ላይ ሲያተኩር፣ በምናቡም ከድል በኋላ የምትውለበለበውን ሰንደቅ ሲያለም፣ ድል ሲናፈቅ … የአትሌቶቻችንም የመጨረሻ ምኞት የ“እኔ ላሸንፍ” ሳይሆን አሸናፊውን አጅቦ ሠንደቅ የማውለብለብና የሕዝብን ኩራት ከፍ ማድረግ ሲሆን … ከድል በኋላ ሕዝብ ሲደሰት … ኢትዮጵያ እንደገና ስሟ በዓለምአቀፍ መድረክ ላይ ሲወሳ … በአሁኑ ጊዜ ያለንበት ወቅት በመጨረሻው ዙር ላይ እንደምንገኝ ያመላክታል። ወቅቱ ከምንጊዜውም በላይ የ“እኔ ላሸንፍ” እሽቅድምድም የሚታይበት ሳይሆን የአገር መጻዒ ዕድል የሚቀድምበት ሊሆን ይገባል እንላለን።

 

ከድል በኋላ አትሌቶቻችን በአሸናፊ ሰገነት ላይ ሆነው በልባቸው ውስጥ ያለችውን አገራቸውን እየተመለከቱ የሃሴት እንባ ሲያፈሱ አገራቸውን የሚወዱ ሁሉ የማያውቁት ስሜት እያራዳቸው፣ እየወረራቸው በደስታ የሚያነቡት ለአገራቸው ካላቸው ክብርና ለአገራቸው ያላቸው ፍቅር ወሰን ስለሌለው በመሆኑ ይህ የኖረው ስሜት ለናፈቃቸው ሁሉ የሎንደን ኦሊምፒክ መቃረቡ ታላቅ ደስታን ይሰጣቸዋል።

 

ውድ አትሌቶቻችን፣ የምትወክሉት ህዝብ ሁሉ ከጎናችሁ ነው። በስደት አገራቸውን ለቀው የሚኖሩ በጉጉት ይጠብቋችኋል። የጋራ ንቅናቄያችን ለናንተ አንድ መልዕክት አለው። እውነተኛውን ተልዕኮ በፖለቲካው ቀለም በመቀባት የህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ እንዳይቆምርባችሁ ተጠንቀቁ። የህዝብ ሃብት ናችሁና ሁሌም ህዝባዊነታችሁን እንደቀደሙት ባለታሪኮች ጠብቁ። በቢሊዮን የሚቆጠር ህዝብና ዓለም ሁሉ የሚመለከተውን አንድነታችሁን በስልጣን አውጁ። ከጎሰኝነት ይልቅ ሰብዓዊነት ይነግስ ዘንድ የተመረጣችሁ የሰላም አምባሳደሮች ናችሁና ይህንኑ አንጸባርቁ። በቅርብ ርቀት የምናያት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ምስረታ ዋዜማ ላይ ናችሁና ድላችሁና ብስራታችሁ ሁሉ ልዩ ትርጉም እንዳለው ይሰማችሁ።

 

የህዝብን አመኔታና ክብር ወደ ጎን በመተው በተንጠፈጠፈ የትራፊ ዘመን የፖለቲካ ቁማር ይበልጥብናል በሚል አትሌቶቻችንን የምታዥጎረጉሩ ከአሳፋሪው ተግባራችሁ በመለየት ሚዛናችሁን እንድታስተካክሉ እንመክራለን። በዘመን ሁሉ ሲታወስ የሚኖረውን ታላቅ ገድላችሁን እንደምናምንቴ በመጣል ፎቅና መሬት እያያችሁ ለምትገኙ የሚደበቅ ነገር የለምና ከወዲሁ ለክብራችሁና ዋጋ እንድትሰጡ አበክረን እናሳስባችኋለን።

 

በየትኛውም መድረክ የምንገኝ የኢትዮጵያ ልጆች አትሌቶቻችን በርካታ የፖለቲካ ተጽዕኖ እንዳለባቸው በመረዳት፣ ከተጽዕኖ ነጻ ሆነው አስተያየት መስጠት እንደማይችሉ በመገንዘብ፣ ምንም እንኳ ነጻ ሆነው ሲሮጡ ቢታዩም እነሱም ነጻ ሊወጡ የሚገባቸው ወገኖቻችን እንደሆኑ በመረዳት፣ ውጤታቸው ምንም ሆነ ምን በኦሊምፒክ መንደር ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ፍቅር ልንሰጣቸውና ልናወድሳቸው ይገባል።

 

የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ በሎንደን ኦሊምፒክ ለሚሳተፉ ውድ የኢትዮጵያችን ልጆች ድልን ይመኛል። ከድሉም ጋር ተያይዞ የሚዜሙ አዳዲስ መዝሙሮችና የድል ብስራቶች ድሉ ላይ ብቻ የሚያተኩሩና የሕዝብ ሐብት ሆነው የሚቀሩ እንጂ የፖለቲካ አመለካከት ማስተጋቢያ እንዳይሆኑ ልብ ለሚሉ የዘርፉ ባለሙያዎች ያሳስባል።

 

ድል ለጥቁር ሕዝብ አምባሳደሮች!!!

ሐምሌ 15፣ 2004 ዓ.ም.

ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!