አባይ ሚዲያ AbbayMedia.comከአባይ ሚዲያ ዋና አዘጋጅ፣

ውድ ኢትዮጵያዊያን፣

ለሁለት ዓመት ያህል አገልግሎቱን አቋርጦ የነበረው አባይ ሚዲያ ወደ አገልግሎት መመልሱን ስናበስራችሁ በታላቅ ደስታ ነው። አባይ ሚዲያ ከአገልግሎት ውጭ ለሁለት ዓመታት ያህል እንዲቆይ ያደረገውን ምክንያት ለእናንተ የሚዲያው ታደሚዎች ማቅረቡ አስፈላጊ ሆኖ ስላገኘነው እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

 

 

አባይ ሚዲያ በ2007 ዓ.ም ስራ ሲጀምር ድረ ገጹን ያቋቋምነው አካላት፣ ሀገራችንና ህዝቧን የሚመለከቱ ማናቸውም መረጃዎችና ትምህርታዊ ጽሁፎች ለሀገራችን መጠነ ሰፊ ችግር መፍትሄ ለመፈለግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ያላቸውን ከፍተኛ አስተዋጽዖ በመገንዘብ ነው። በተለይ ደግሞ በየግዜው የሚወጡ መረጃዎችንና ጽሁፎችን ወደ ኋላ ሄደው ለመመርመር ለሚፈልጉ ሁሉ በቀላሉ ሊያገኟቸው አድርጎ በአርካይቭ መልክ ማስቀመጡ ያለው ጥቅም በመረዳት ነው።

 

አባይ ሚዲያን አቋቁመን ሁለት ዓመት ያህል አገልግሎት መስጠት ላይ እያለን፣ ወደ ኢትዮጵያ ይገባል ተብሎ ተስፋ ሲደረግበት የነበረው በድሲ ከተማ ተመስርቶ የነበረው ኢቲኤን (ETN) በመባል የሚታወቀው የቴሌቭዥን ጣቢያ ሲዘጋ፣ ወደ ኢትዮጵያ በቀጥታ የሚተላለፍ የነጻ ቴሌቪዥን ጣቢያ የማቋቋም አስፈላጊነት ይበልጥ ጎልቶ መታየት ጀመረ።

 

በቀጥታ ወደ ኢትዮጵያ የሚተላለፍ የነጻ ቴሌቪዥን አገልግሎት በሀገራችንና ለህዝቧ እንደ አንድ የመረጃ ምንጭ በመሆን ሊያደርግ የሚችለውን እርዳታ የአባይ ሚዲያ ዋና አዘጋጅ በመገንዘብ፣ በውጭ የምንገኝ ኢትዮያዊያን እውቀታችንና ገንዘባችንን ከአስተባበርን ልንተገብረው እንችላለን የሚል እምነት ስላደረበት፣ በዚህ ከአምባገነን አዙሪት ውስጥ ሊያወጣን በሚችል ጥረት ላይ ሙሉ ለሙሉ ትኩረት ለመስጠት ወሰነ።

 

የአባይ ሚዲያ ዋና አዘጋጅ ከሌሎች ሁለት ኢትዮጵያዊያን ጋር በመሆን ከስድስት ወር የጥናት ወቅት በኋላ በእርግጥም እኛ ኢትዮጵያዊያን የራሳችንን የቴሌቪዥን ጣቢያ አቋቁመን ስራ መጀመር እንችላለን የሚል ድምዳሜ ላይ ተደረሰ። የቴሌቪዥኑን አገልግሎት የማስጀመሩ ዝግጅት በአባይ ሚዲያ ዋና አዘጋጅ አስተባባሪነት ተጨማሪ የስምንት ወር ግዜ ፈጀ። በዚህ ስምንት ወር ግዜ ውስጥ የአባይ ሚዲያ ዋና አዘጋጅ ለዚህ ታሪካዊ ቴሌቪዥን አገልግሎት ኢሳት የሚለውን ስም በማውጣትም ሆነ አርማውን ዲዛይን በማድረጉ ከፍተኛ ኩራት ይሰማዋል።

 

ከዚህ በመቀጠል የአባይ ሚዲያ ዋና አዘጋጅ ከሌሎች ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ጋር በመሆን ለሶስት ወራት ያህል ወደ አምስተርዳም ከተማ በመሄድ የኢሳትን የመስራች ስቲዲዮ ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት በበላይነት በማስተባበር የመጀመሪያውን ዝግጅት በኤፕሪል 8 2010 ዓ.ም በቀጥታ ወደ ኢትዮጵያ እንዲተላለፍ አድርጓል።

 

የአባይ ሚዲያ ዋና አዘጋጅ ከሳስት ወር የአምስተርዳም ቆይታው በኋላ ወደ ለንደን በመመለስ በለንደን የኢሳት ስትዲዮን አቋቁሟል። የዲሲው የኢሳት ስቱዲዮ በአካባቢው በሚገኙ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ጥረት ሊመሰረት ችሏል።

 

የአባይ ሚዲያ ዋና አዘጋጅ ከሌሎች ሀገር ወዳድ የቦርድ ዓባሎች፣ የአስተዳደር ሰዎች፣ ጋዜጠኞች፣ አቅራቢያኖችና የቴክኒክ ባለሞያተኞች ከሁሉም በላይ ደግሞ በመላው ዓለም ከሚገኙ ደጋፊ ኢትዮጵያዊያን ጋር በመሆን፣ ቀን ከለሊት በመስራት የኢሳት ቀጣይነትና ውጤታማነት ለማረጋገጥ ያደረገው ጥረት ነው፣ የአባይ ሚዲያን ድረ ገጽ ከአገልግሎት ውጭ ሆኖ ለሁለት ዓመት እንዲቆይ ያደረገው።

 

የአባይ ሚዲያ ዋና አዘጋጅ በወያኔ አንባገነን ስርዓት በሀገራቸው የነጻ ጋዜጠኛነታቸውን ሙያ እንዳይተገብሩ የተገደዱትን የሚዲያ ባለሙያዎች እድል ሊሰጥ የሚችል ሁኔታ ለማመቻቸት የነበረውን ራዕይ ከአሳካ በኋላ፣ በ2007 ዓ.ም ጀምሮት ወደ ነበረው አባይ ሚዲያን “የኢትዮጵያ የመረጃ ባንክ” ወደ ማድረግ ተልዕኮ ተመልሷል።

 

አባይ ሚዲያ ወደ ሥራ ሲመለስ በርካታ ዘመናዊ አገልግሎቶችን በማካተት ነው። የአይፎንና የአይፓድ ተጠቃሚዎችን በአመቺ ሁኔታ አባይ ሚዲያን እንዲገለገሉ የተመቻቸ ዲዛይን ያዘጋጀን በመሆኑ ዘመናዊ መገናኛዎትን በመጠቀም እንዲጎበኙን እንጋብዞታለን።

 

አባይ ሚዲያ በየዕለቱ በአማርኛና በእንግሊዘኛ የሚወጡ ጽሁፎችን፣ ጠቃሚ ዜናዎችን፣ የተለያዩ ጦማሮችን የስዕልና የድምጽ ስራዎችንና በየግዜው የሚካሄዱ ክንውኖችን በሚመለከት የሚያስፈልገውን መረጃ ለእናንተ ለማድረስ ዝግጅቱን አጠናቋል።

 

ይህም በመሆኑ ኢትዮጵያን በሚመልከት ድረ ገጾችን ሲያስቡ ከምርጫዎ አንዱ፣ አባይ ሚዲያን እንዲያደርጉ በመጋበዝ፣ እርሶም ለሌሎች የአባይ ሚዲያን ወደ አገልግሎት መመለስ ዜና እንዲያደርሱልን በአክብሮት እንጠይቃለን ።

የአባይ ሚዲያ ዋና አዘጋጅ፣

ግሩም ይልማ፣

http://abbaymedia.com/

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!