ከ”የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ” የተሰጠ መግለጫ

የካቲት 2፣ 2005 (Feb 9, 2013)

ባለፉት ጥቂት ቀናት የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት በቁጥጥሩ ሥር የሚገኙትን የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን አገልግሎቶችን በመጠቀም፣ በእስር ላይ የሚገኙ የሙስሊሙ ማህበረሰብ መሪዎችን የሚወነጅል ሠፊ ቅስቀሳ በማካሄድ ላይ ይገኛል።

 

ይህ “ጅሃዳዊ ሐረካት” በሚል ርዕስ በተደጋጋሚ በመሰራጨት ላይ ያለው ፊልም፣ የሙስሊሙ ማህበረተሰብ የሀይማኖቱን አስተዳደር በተመለከተ ወክለው እንዲናገሩለት የመረጣቸው መሪዎቹ በእስር ላይ እያሉና ጉዳያቸውም በፍርድ ቤት ተብየው እየታየ እያለ፣ እነዚህን በህዝብ የተመረጡ መሪዎች “እሰላማዊ መንግሥት ለመፍጠርና ሁከት ለማካሄድ የሚፈልጉ አሽባሪዎች” እንደሆኑ በማሰመስል በጥፋተኛነት የሚወነጅል ነው።

 

ምንም እንኳን ይህ ፕሮግራም እንዳይተላለፍ በራሱ በህወሓት/ኢህአዴግ ቀጥተኛ ቁጥጥር ሥር ያለው ፍርድ ቤት የእገዳ ትእዛዝ ቢሰጥም፣ የህወሓት/ኢህአዴግ መንግሥት በተለመደው ትዕቢትና አይን አውጣ ባህሪው፣ የፍርድ ቤቱን ትእዛዝ በመሻር፣ ሕዝብን በሕዝብ ላይ ለማነሳሳት ያነጣጠረውን፣ ክፋፋዩንና ሀላፊነት የጎደለውን የሀሰት ፕሮፓጋንዳውን ማሰራጨቱን ቀጥሎበታል።

 

ያለፉት ሀያ ዓመታት ታሪክ የሚያሳየው፣ ገዥው ህወሓት/ኢህአዴግ ስለመብት መከበር የቆሙትን ሁሉ በየተራ ለማንበርከክ በፈጠራ ክሰ መወንጀል፣ ማሰርና ማሳደድ ብሎም መግደል ዋነኛ ስልቶቹ ሆነው መቆየታቸውን ነው። ይህንን የጥፋት አካሄድ ህጋዊ ለማስመሰልም ሰፊ የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ሥራ መስራቱ የተለመደ ነው። አሁንም በሙስሊሙ ማህበረሰብ መሪዎች ላይ የሚካሄደው ቅስቀሳ የተለመደው ቅጥፈት፣ መሰሪና ከፋፋይ ፕሮፓጋንዳ አካል ነው። የሙስሊሙን ማህበረሰብ ሕጋዊ ጥያቄ ባግባቡ ከመመመለስ ይልቅ፣ አገዛዙ አሁንም የሚያደርገው ሃላፊነት በጎደለው መልክ፣ በሕዝብ መካከል ውዥንብርንና ሽብርን በመፍጠር ረገጣውን ለመቀጠል መሯራጥ ብቻ ሆኗል።

 

የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ (ሸንጎ )፣ ህወሓት/ኢህአዴግ ይህን በቀጣይነት የሚያደርገውን ሃላፊነት የጎደለው ብጥብጥ የመፍጠር ጥረትና መሰረታዊ የመብት ረገጣ በጥብቅ ያወግዛል። ሙሰሊሙ ማህበረሰብም ለእምነት ነጻነቱ መከበር ለሚያደርገው ሰላማዊ ትግል ያለውን ድጋፍ በድጋሚ ያረጋግጣል።

 

ህወሓት/ኢህአዴግ፣ ዓመታትን ባሰቆጠረው ግፍና የመብት ረገጣው፣ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በስነልቦና ሽብር አፍኖ፣ አንዱን የህብረተሰብ ክፍል በሌላው ላይ እንዲነሳ በማድረግ፣ የከፋፍለህ ግዛ መንገዱን በማጠናከር፣ የአምባገነን የስልጣን ዘመኑን ለማራዘም እየጣረ መሆኑ ግልጥ ነው። ዛሬ በሀገራችን ውሰጥ፣ በህወሓት/ኢህአዴግ መብቱ ያልተረገጠ፣ የጥቃቱ ስለባ ያልሆነ የህብረተሰብ ክፍልን ማግኘት አይቻልም። ይህን መጠን የለሽ ረገጣ ለማስቆምና ዴሞክራሲያዊና ስብዓዊ መብቶችን ለማስከበር የሚቻለው ደግሞ ሁሉም ዜጋ፣ በግልም ሆነ በጋራ፣ ለመብቱ መከበር "እምቢ አልገዛም" ብሎ ሲነሳ ብቻ ነው። ሰለሆነም፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከሙሰሊሙ ህብረተሰብ ጎን እንዲቆም፣ እንዲሁም ሌሎች የመብት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ በጋራ ትግሉን እንዲያፋፍም ጥሪያችንን እናሰተላልፋለን።

 

በውጭ ሀገር የሚገኘው ኢትዮጵያዊም፣ የህወሓት/ኢህአዴግን ከፋፋይ ሴራና ቀጣይ የመብት ረገጣ በጋራ በመሆን በሰላማዊ ሰልፍና መስል በሆኑ እንቅስቃሴዎች እንዲያጋልጥ ጥሪ እናቀርባለን።

ህወሓት/ኢህአዴግ ሕዝብን ለመከፋፈልና ለማጋጨት የሚያደርገው ጥረት ይከሽፋል!

የሁሉም ኢትዮጵያዊ መብት ይከበር!

የተባበረ ሕዝብ አይበገርም!

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!