Abay Tsehaye

አቶ አባይ ፀሐዬ

ወርቅና ሐቅ እያደረ ይጠራል

ትዴት (የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር)

ሕወሓት በመላው ኢትዮጵያ እየተደረገበት ባለው ትግልና ጫና ተገዶ፣ እንደዚሁም በኢህአዴግ ራሱ ውስጥ ባሉት ፓርቲዎች መካከልም በተፈጠረው ፉክክርና ፍትጊያ የተነሣ ምስጢር አድርጎ ደብቆት የነበረውን ሐሰትና ማወናበድን አንድ ባንድ እያለ እያጋለጠው ይገኛል። ይህ ሁኔታ እዚህ ላይ የሚቆም አይደለም፣ ሕዝቡ መብቱን ለማስከበር ቆርጦ ተነስተዋልና።

ቀደም ብሎ የማጥራት ዘመቻ በሚል አስመሳይ እንቅስቃሴ፣ የማስተዳደር ድክመት እንዳለው፣ የዴሞክራሲ ሂደቱን እንዲጠብማድረጉን፣ ሙስና መንገሱን፣ የሐሰት ሪፖርቶችን በማቅረብ የሌለ ዕድገት እንደተመዘገበ ያሰራጭ እንደነበረ አምኗል። ከዚህ አልፎም ከሕግ ውጭ የታሠሩ ፖለቲካዊ እሥረኞች የሉም፣ የሉኝምም እያለ ከቆዬ በኋላ አሁን እየፈታኋቸው ያሉት የተቃዋሚ ድርጅቶች አባላት በፈጸሙት ወንጀል ነበር እንጅ በፖለቲካ አመለካከታቸው እንዳልነበረ ገልጿል። ያ የፖለቲካ እሥረኞች የሉንም፣ በፖለቲካ ልዩነት ሰዉን አናሥርም ይል የነበረው እንቶ ፈንቶ የፈጠራ ወሬ ውሃ የማይቋጥር እንደሆነ ሕዝቡ አሳምሮ ያውቀዋል።

ይህ ወንጀል፣ በራሱ ላይ እየተፈፀመበት ያለው ሕዝባችን ቀርቶ እነኛ ጥቅማቸውን እንዲያስጠብቅላቸው በድጎማ የሚንከባከቡት ምዕራባውያን ጭምር የነቁበት፣ ፀሐይ የሞቀው ገሃድ ሓቅ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ባጠቃላይ፣ በተለይም በትግራይ ውስጥ ዜጎች ምሬታቸውን በመግለጻቸው ምክንያት እንደሚታሠሩ መደበቅ የማይቻል መራራ ሓቅ ነው። ለዚህም ጥሩ አብነት ሊሆን የሚችለው በእግሪ ሓሪባ አርሶ አደሮች ላይ ያደረሰውን ግፍ ያስታውሷል። ለእንደነዚህ ዓይነቶቹ ለተገለጹት ሓቆች ቀደም ሲል የሥርዓቱ ተቃዋሚ ኃይሎች ከነርሱ መካከልም ትዴት(ታንድ) በተደጋጋሚ ድርጊቱን በመቃወም ቅሬታቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል። ሆኖም ግን ይህንን በማለታቸው ብዙዎች ታስረዋል፣ ተገርፈዋል፣ ተገድለዋል ተሰድደዋል። በመሆኑም የፖለቲካ እሥረኞች የሉንም ብሎ ማለት ራስን ከማቄል የዘለለ ትርጉም ስለሌለው፣ በሌላ ደረቅ ወንጀል ካልተሳተፉት በቀር ሁሉም እሥረኞች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ በነፃ ተፈትተው በተገቢው ሁኔታ ሊካሱ ይገባል።

ከዚህ ለየት ባለ ሁኔታ ደግሞ ሰሞኑን አቶ አባይ ጸሃዬ በሰጡት መግለጫ፣ ተቃዋሚዎች ለሠላሳ ዓመታት ያህል የትግራይ ሕዝብ ተጠቃሚ ሳይሆን እያለ እንደተጠቀመ አድርገው በመቁጠር ዘመቻ ሲያካሂዱ፣ ሳንጋፈጣቸው በመቆዬታችን በኢህአዴግ ውስጥ ያሉት ፓርቲዎችም ጭምር ይህን አመለካከት እንዳላቸውና ጠባብ ብሔራዊ ስሜት ማደጉን፣ ወጣቶቻችንንም ስለ ኢትዮጵያዊነትና አንድነት ዕውቀት እንደሌላቸው፣ ወዘተ... እያሉ ዘርዝረው አቅርበዋል።

በመጀመሪያ ደረጃ የትግራይ ሕዝብ ሳይጠቀም እንደተጠቀመ አስመስሎ በቴሌቪዥንና በሁሉ የሕዝብ መገናኛ መሳሪያዎች በሰፊው ሲያስተጋባና ሲያራግበው የነበረው የሕወሓት አመራር እንደነበር በግልጽ ሊታወቅ ይገባል። ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ ባንድ ወቅት በኢፌዲሪ ፌዴራል ፓርላማ ቀርበው ባሰሙት ንግግር “የትግራይ ገበሬዎች መቶ ፐርሰንት ሞዴል አርሶ አደሮች ሆነዋል” ብለው ሪፖርት ሲያቀርቡ እነ አቶ አባይ ጸሐዬና ሌሎቹ የሕወሓት አመራርና አባላቶቹ የት ነበሩ? የሚል ጥያቄ ልናቀርብ እንገደዳለን። ቀጥሎም ሕወሓት በባለዋናነት የሚገዛት ትግራይ ገዥዎቿ ሲያቀርቡት በነበረው የዕድገት ሪፖርቶች በመነሣት፣ ትግራይን በዓይኑ ያላያት ኢትዮጵያዊ ወገን ትግራይ ከፍተኛ ዕድገት ላይ ደረሰች፣ ተመነደገች ብሎ ቢናገር ምን ያስገርማል? እንደ ማስረጃ አድርጎ ያቀረበው እኮ ሕወሓት ራሱ ባቀረበው ሪፖርት ላይ ተመርኩዞ ነው። ትናንት እመሬት ላይ የሌለ የውሸት ሪፖርት እያቀረባችሁ ነው ስንላችሁ፣ የትግራይ ዕድገትን የማያስወድዳቸው መናፍቆች ስትሉን አልነበረንም! መቐለ ከተማ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ዕጥረት አለው ሲባል እኮ ነው የትግራይ የውሃ አቅርቦት 82% ደርሷል እያላችሁ የሐሰት ሪፖርት ስታቀርቡልን የነበራችሁት። ቅንነት ባጠገባችሁም ሲያልፍ አይነካካችሁም እንጅ ቢኖራችሁ ኖሮማ፣ አሁን የምትሉትን ልክ እንደኛው ስትሰሙት ከቆዬ እና የትግራይ ሕዝብም ያልበላነውን እንደበላን አድርጋችሁ አታስቆጥሩን ብሎ ሲነግራችሁ ለምንድነው ዉሸቱን ያልታገላችሁት? ባንድ በኩል ሕወሓት የሌሉ ጠላቶችን እንዳሉ አስመስሎ እየፈበረከ የትግራይ ሕዝብ በስጋት የተነሳ እጉያችሁ ሥር እንዲወሸቅና ከጎናችሁ እንዲሰለፍ ስትሉ፣ ይካሄድ የነበረውን የስም ማጥፋት ዘመቻን በደስታ ስትቀበሉት የቆያችሁት እንዲያዉም በውሸት የትግራይ ሕዝብ በወያኔያችን አድጎ ብዙ ነገር አግኝቷል እያላችሁ የመምቻ ዱላ ስታቀርቡ ቆይታችኋል። በሌላ በኩል ደግሞ በተቃዋሚዎችም ላይ ከልክ ያለፈ ንቀት ስለነበራችሁ ነው።

ጠባብነቱስ ቢሆን እንዲነግስ ያደረገው ራሱ ሕወሓት/ኢህአዴግ አይደለም ወይ! ሕዝቦች ድሮም ቢሆን ለዘመናት እዚያው አብረው ነበር ሲኖሩ የነበሩት፤ ይሁንና ግን አሁን እየታዬ ያለው የጎሳ ጥላቻ እንዳሁኑ ገንኖ የወጣበት ጊዜ ታይቶ አይታወቅም። በመሆኑም በብሔሮችና ብሔረሰቦች መካከል እየታየ ያለውን ቅራኔና ጥላቻ እንዲባባስና እንዲያድግ ያደረገው ሕወሓት/ኢህአዴግ ሲያካሂደው በነበረውና እያስቀጠለው ባለው የተዛባ ፖሊሲ የተነሳ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።

ሕዝባዊ አንድነትን አጠናክሮ ስምምነቱን በማጠናከር ፈንታ ልዩነቶቹ ላይ በማተኮር እርስ በርሱ እንዲጠላላና እንዲጠራጠር አደረጋችሁ። በኦሮሞ ክልል አርሲ፣ አኖሌ ውስጥ የአማራ ወታደር የኦሮሞ ሴትን ጡት ሲቆርጥ የሚያሳይ ሐውልት ሲሠራ፣ እየሳቃችሁና እየተደሰታችሁ ዝም ነበር ያላችሁት፣ ምክንያቱም በኦሮሞና አማራ ሕዝቦች መካከል ቅራኔ እንዲያድግ በመፈለግ ነው። ከደቡብ ኢትዮጵያ በርካታ የአማራ ብሔር ተወላጆች ሲፈናቀሉስ፣ ትክክል አይደላችሁም ብሎ ጥፋቱ እንዲቆም በማድረግ ፈንታ፣ ባካባቢው ያላግባብ የሠፈሩ ሰዎች የአካባቢውን የደን ልማት በማውደማቸው ነው የተባረሩት እየተባለ በኢህአዴግ የመገናኛ ብዙኃን ሲስተጋባ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። ከቦታው ተፈናቅሎ በየመንገዱ ለተጣለው ሰው እንኳን ዕርዳታ አልተደረገለትም፣ ሕወሓት/ኢህአዴግ ለነዚህ ዜጎች ያሳዬው ምንም ዓይነት ሰብዓዊ ርኅራሄ አልነበረም። መንግሥት ምንም ሊያደርግላቸው ባለመቻሉም የተነሳ ነው በመኢአድ ጽ/ቤት እንዲጠለሉ የተገደዱት። ይህም ኢ-ሰብአዊ ተግባር ነበር ያ የተፈናቀለው ሕዝብና ቀሪው ወገን ይህ መንግሥት አይወክለኝም እንዲል ያበቃው።

ሕገ መንግሥቱ ልዩነቶችን የሚያሰፋ እንጂ አንድነትን የሚያጠናክር አልሆነም። ሙሉ የኢትዮጵያ ሥልጣን ይዛችሁም ሁሉንም የኢትዮጵያ ሕዝቦችን በእኩል ዓይን ማየትና ማገልገል ይቅርና አሁንም ድረስ አማራ ጠላት ነው ትላላችሁ። ይህ አባባላችሁ እንኳንና ከአንድ ፖለቲካዊ ሥልጣን የጨበጠ ኃላፊነት የተሸከመ አካል ይቅርና ከተራ ሰውም ልትጠብቀው የምትችል አመለካከት አይደለም።

ይህ አሁን እየተባለ ያለው ነገር ሁሉ እንዳይመጣ ከሚል ገና ከጧቱ ብዙ አዋቂዎች፣ ተቃዋሚ ድርጅቶች እኛም እንደ ትዴት (ታንድ) እና እንደግለሰብም ስናስጠነቅቅና ስናሳስብ ቆይተናል። ለአቶ አባይና ለሕወሓት መሪዎች የምንጠይቃቸው ለምንድነው ምክሮቹን ልትሰሙ ያልፈለጋችሁት? በአንጻሩ ግን ለምንድነው ይህንን ምክር ለለገሱላችሁ፣ ፀረ ሕዝብ፣ ያማራ ቡችላ፣ ቆሻሾች ወዘተ ... እያላችሁ ስም ስታጠፉና ስታሳድዱ የነበራችሁት? እንላቸዋለን።

አሁን ውጥረት ውስጥ ሲገቡ አቶ አባይና መሰሎቹ በኢህአዴጎች ውስጥ የነበሩ መሳሳቦችን ምስጢር ማውጣት ጀምረዋል። ለምንድነው ቀደም ብላችሁ ይደረግ የነበረውን ክርክርና ሙግት ሕዝብ እንዲያውቀው ይፋ ያላደረጋችሁት? የዚህም ምክንያት በሕወሓት ኋላ ቀር ምስጢራዊ አሠራር የተነሣ ነው። የዘረፋችሁትና ያጠፋችሁት እንዳይታወቅባችሁ ለማድረግ የምታደርጉት አካሄድም ነው ብለን እናምናለን። ታዲያ ለዚህ ሁሉ ተጠያቂው ራሱ ሕወሓት ነው፣ ምክንያቱም ሕወሓት መጀመሪያ ላይ ወሳኝ ተራ ስለነበራት በውነት ልትሠራ ብትፈልግ ኖሮ፣ ልታስተካክለውና ትክክለኛ መስመር ልታስይዘው ትችል ስለነበር ነው። የዚህ ሁሉ ድክመትና ምክንያቶች መሠረቱ የሕወሓት አመራር ነው። ሌላው ቀርቶ አሁን በሚደረገው የማጥራትና ተሓድሶ ዘመቻ ሳይቀር እንኳን የኋሊት እየሳበና እየጎተተ ያለው የሕወሓት አመራር ነው። የፖለቲካ እሥረኞች ይፈቱ፣ የፖለቲካ ምኅዳሩ ይስፋ ተብሎ የኦሮሞና የአማራ ክልሎች ተግባራዊ የማድረግ ሥራ በሚያደረጉበት ሁኔታ ላይ፣ በትግራይ ግን የፖለቲካ እሥረኞችን መፍታት አልጀመሩም። ተቃዋሚዎችንም ሲጋብዙ አልታዩም። ይህንን የለውጥ ሥራ ተግባራዊ እንዳታደርጉ ምንድነው የከለከላችሁ? ባጠቃላይ ሲታይ የሕወሓት አመራር ከሚገባው በላይ እንደዛገና ከማስወገድ በቀር ልንጠግነው የሚቻል አለመሆኑን ነው።

ሌላው እዚህ ላይ ሳንጠቅስ ልናልፈው የማይገባ ነጥብ ቢኖር አቶ አባይ አንቀጽ 39ኝን ተጠቅሞ መገንጠል መብት እንደሆነ ከገለጸ በኋላ፣ መገንጠል በሃገሪቱ ላይ ስለሚያስከትለው ውድመት ያሳስባል። የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) የመገንጣጠል ጠንቅ ከኢትዮጵያ አልፎም ለመላው የአፍሪካ ቀንድ ተጽእኖ ከማሳደሩ በላይም አደገኛና የተመሰቃቀለ ውጤት እንደሚኖረው በመገንዘብ አስቀድሞ ፍትሕንና ርትዕን ግቡ ያደረገ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት እንጂ አንቀጽ 39 መፍትሄ እንደማይሆን አስቀድሞና ደጋግሞ ሲግለጸው የነበረ ጽኑ አቋሙ ስለሆነ እዚህ ላይ ደግመን ዝርዝር ውስጥ መግባቱ አስፈላጊ ሆኖ አይታየንም። ይሁን እንጂ ሕወሓት/ኢህ አዴግ ከዚህ ከሚያጋጥመው ችግር ትምህርት ወስዶ ከሆነና እነኛ አቶ አባይ ያቀረባቸው ስጋቶችን ከምር የሚቀበል ከሆነና ለመፍትሄነቱም ከተጋ፣ የተጠቀሰዉን አንቀጽ ጨምሮ ህገ መንግሥታዊ ክለሳ ማካሄድ ለምን ዳገት ሆነበት? እነኛ አቶ አባይ በትክክል የገለጻቸው አሉታዊ ውጤቶች ለሕወሓት/ኢህአዴግ ግልጽ የሆኑለት ከሆነ፣ መገንጠል እንደ አማራጭ ተደርጎ በሕወሓት መሪዎችና ተላላኪዎቻቸው እየተደጋገመ የሚነሳውና የሚበረታታው ያለው ለምንድነው?

እንደ ትግራይ ሕዝብ ያለን አማራጭ ከመላው ኢትዮጵያውያን ሕዝቦች ጋር ሆነን ሕወሓትን በማስወገድ የሚጠቅመንን ድርጅት መደገፍ ወይንም ማቋቋም ነው። ምክንያቱም ትግራይ ከሕወሓት አመራር ሌላ ወልዳ እንደመከነች ካልተቆጠረ በስተቀር ከሕወሓት ጋር ተጣብቃችሁ ኑሩ ተብሎ ሕዝባችን ሊገደድ አይገባም፣ አይሆንምም። ስለዚህ ይህን ራሱን በስብሻለሁ ብሎ ያመነ አመራር ራሱን ከገለጽበት የተሻለ አባባል ስለማይኖር፣ ያለፈ የትግል ታሪኮቹን አቅቦ ለተተኪው ወጣት ትውልድ ኃላፊነቱን በሠላማዊና የሠለጠነ መንገድ እንዲያስረክብ አበክረን ማሳሰብ እንፈልጋለን።

ት.ዴ.ት.

25.02.2018

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!