የኢትዮጵያውያን ተጋሩ የውይይት መድረክ

በቅርቡ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያን ሕዝብ ጥቅምና ክብር አሳልፎ የሰጠውን የአልጀርስ ስምምነትና የድምበር ኮሚሽኑን ፍርደ-ገምድል ውሳኔ ሙሉ በሙሉ ተቀብሎ እንደሚተገብረው አሳውቋል። ኢትዮጵያ ከድል መንጋጋ ሽንፈትን መንጭቃ አወጣች እንደተባለው ከበርካታ መሥዋእትነት በኋላ ለምን ወደ ድርድር ተሂዶ መራራ ዲፕሎማሲያዊ ሽንፈት ማምጣት እንዳስፈለገ በውል ባይታወቅም፣ ከዚያም በኋላ የአልጀርስ ስምምነት ውድቅ ለማድረግ የሚያስችል በቂ ፖለቲካዊ፣ ታሪካዊና ሕጋዊ ምክንያቶች እያሉ ለምን በአጣዳፊና ግብታዊ በሆነ መንገድ ውሳኔውን ተቀብለናል ማለት እንዳስፈለገ ግልጽ አይደለም።

መላው ኢትዮጵያውያን ከጠረፍ እስከ ጠረፍ ወድ ሕወታቸውንና አካላቸውን ገብረው ያመጡትን ድል የኢትዮጵያን ሕዝብ ፍላጎትና ጥቅም ግምት ውስጥ ባላስገባና እኔ አውቅልሀለሁ በሚል እብሪት የተወሰነውን ውሳኔ የአገራችንን ዘላቂ ሰላምና የግዛት አንድነት የሚጎዳ ስለሆነ በጽኑ እንቃወማለን።

ሕወሓት ላለፉት 27 ዓመታት በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደረውን የኢሮብ ብሔረሰብ ለማጥፋት በርካታ ሴራዎችን ሲሸርብና ሲተገብር መቆየቱ የሚታወቅ ነው።የኢሮብ ሕዝብ ያንን ተቋቁሞ መዝለቅ ቢችልም፤ ዛሬ ግን የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ተግባራዊ ማድረግ ማለት በጭቆና ስር ያለውን ሕዝብ ለሁለት በመክፈል ሕልውናቸው እንዲዳከም፤ ብሎም ሙሉ በሙሉ እንዲጠፋ የሚያደርግ የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ ስለሆነ ውሳኔውን አጥብቀን እንቃወማለን።

በስምምነቱ ተግባራዊ መደረግ በቀጥታና በከፋ ሁኔታ ተጠቂ የሆነው በድንበር አካባቢ ያለው ሕዝብ ማለትም የኢሮብን ጨምሮ የባድመ፣ የግሎመከዳ (ዛላንበሳና አካባቢው) እና የዓፋር ሕዝብ ድምፃችን ይሰማ እያለ ባለበት ሁኔታ ድምፁ ሳይሰማና እሱን ችላ ብሎ ውሳኔውን ተግባራዊ ማድረግ፤ ሰላም ሳይሆን መቃቃርና ግጭት እንደሚያሰከትል መታወቅ አለበት። በኢትጵያም በኤርትራም በኩል ያሉ የደንበር አካባቢ ሕዝቦች አሁንም ዕድል ስጡንና ተወያይተን እንፍታው በሚሉበት ሰዓት ለሕዝቦች ተገቢውን ዕድል ሳይሰጥ የሚደረግ የፖለቲከኞች ውሳኔ ተቀባይነት አይኖረውም።

በአጠቃላይ የአልጀርስ ስምምነትና የደንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ እንዳለ መቀበልና መተግበር ፍትሕን የማያመጣ፣ ርትዕን ያላገናዘበ፣ የሕዝብና የአገር ጥቅም የማያስጠብቅ፤ ብሎም ለሰላም ፋይዳ የሌለው ነው። ስለሆነም፤

ለኢትዮጵያ ሕዝብ

በልጆችህ መሥዋእትነት የተገኘው ድል አሳልፎ የሚሰጥና ሉዓላዊነትህን የሚዳፈር ውሳኔ ተግባራዊ ለማድረግ የኢትዮጵያ መንግሥት እየተሰናዳ ስለሆነ፤ በተደራጀና በተቀናጀ ሁኔታ እንድትቃወመው ጥሪ እናደርጋለን። አባቶቻችን ባደረጉት ታላቅ ተጋድሎና መሥዋእትነት ታፍራና ተከበራ የቆየችን አገር በክህደትና በሸፍጥ በተመሰረተ የአልጀርስ ስምምነት ስትቆራረስ ማየት በታሪክም ተወቃሸ የሚያደርግ ስለሆነ በጽናት እንድትቃወመው ጥሪ እናቀርባለን።

ለትግራይ ሕዝብ

የኢትየጵያ ሉአላዊ ግዛቶች ለኤርትራ አሳልፎ ለመስጠት በኢትዮጵያ መንግሥት የተወሰነውን ውሳኔ በመቃወም በአንዳንድ የትግራይ አካባቢዎች እየተደረገ ያለው ሰላማዊ ሰልፍና የተቃውሞ ድምፅ የሚደገፍና የሚበረታታ ነው። ሕወሓት በመለስ ዜናዊ መሪነት በክህደት የፈረሙትን ስምምነትና የተቀበሉትን ውሳኔ መተግበር ማለት ለትግራይ ሕዝብ በኢትዮጵያዊነቱ ላይ ያጠላ አደገኛ ጥላና ለቀጣይ የሕወሓት ጭቆናና ዐፈና አመቺ ሁኔታ የሚፈጥር ነው። ስለዚህ ፀረ-ሕወሓት ተቃወሞው በድምበር ኮሚሸኑ ውሳኔ ላይ ብቻ ሳይገደብ በአጠቃላይ ለፍትሕና ለዴሞክራሲ ወደ ሚደረገው ትግል በማስፋፋት ጫንቃህ ላይ እንደ መዥገር የተጣበቁትን የመለስ ተከታዮችን ላንዴና ለመጨረሻ ግዜ እንድታስወግድ በዚህ አጋጣሚ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

ለዶ/ር ዐቢይ አሕመድ

በእስካሁኑ ሂደት ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ክብር እየሠሩ ያሉትን ትልቅ ሥራ በአክብሮት የምናየው ነው። የአልጀርስ ስምምነትና የድምበር ኮሚሽኑን ውሳኔ በተመለከተ ግን እርሶ የሚመሩት ፓርቲ ኢሕአዴግ እንዳለ ለመተግበር የወሰነው ውሳኔ የኢትዮጵያን ክብርና የግዛት ሉዓላዊነት የማያስጠብቅ እንዲሁም፤ የተመኙትን ሰላም የማያመጣ ነው።ስለዚህ እርሶ የሚመሩት ድርጅት ውሳኔውን እንዲቀይር የተቻለዎትን በማድረግ ከታሪካዊ ስህተት እንዲድኑ ጥሪ እናቀርባለን።

ኢትዮጵያ በልጆችዋ አንድነት ጸንታ ለዘላልም ትኑር!

15 June 2018

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!