TPLF

ሕወሓት

ጥቅምት 4 ቀን 2012

የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ከመስከረም 26 እስከ ጥቅምት 2/ 2012 ዓ/ም ድረስ ለተከታታይ 7 ቀናት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ በ2011 ዓ/ም ተይዘው የነበሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር እቅዶች፤ ድርጅታዊና ፖለቲካዊ ስራዎች በተለይ ደግሞ በአዲሱ የፖለቲካ መድረክ የትግራይ ሕዝብ ህልውና፣ ደህንነትና ዋስትና ለማስጠበቅ የተካሄደ ሁለንተናዊ የመመከት ትግል እና ይህንን መሰረት በማድረግ የተሰሩ ስራዎች በዝርዝር ገምግሟል። በዚህ ልዩ የትግል ምዕራፍ የታዩ ጥንካሬዎችንና ጉድለቶችን በመገምገም ሊወሰድ የሚችል ትምህርት በመለየት በዚህ ዓመት ሊሰሩ የሚገባቸው ልማታዊና ፖለቲካዊ እቅዶችንም አጽድቋል።

በተጨማሪም አሁን ያለው ተጨባጭ አገራዊ ሁኔታዎችንና ዕድገቶችን በመገምገም በቀጣይ ለሚኖረው ትግል መሰረት ያደረገ የመመከትና ደህንነትን የማረጋገጥ አቅጣጫዎችንና እቅዶችን በዝርዝር ተወያይቶ በዚህ ዓመት ሊኖር የሚችለውን ሁለንተናዊ ትግል ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችሉ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ስብሰባውን አጠናቋል።

ባለፈው ዓመት ተይዘው የነበሩ የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የሰላም እቅዶችን በቀጣይነት ለማስፋትና ለማጎልበት የሚያስችል ዘርፈብዙ ጥረት እየተካሄደ ቆይቷል። ከጀመርነው የፀረ- ድህነት ትግል ለአፍታም ሳንዘናጋ፣ በዋነኛው አጀንዳችን ላይ ለመረባረብ የሚያስችል አቅጣጫ ይዘን ሰፊ ርብርብ ስናደርግ ቆይተናል። በሕዝባችን የተደራጀ ትግልና እንቅስቃሴ ከትክክለኛ መንገዳችን ሳንወጣ በልማት እቅዶቻችን ላይ ከፍተኛ ትኩረት በማድረግ ስንሰራ ቆይተናል።

የሁሉም ዘመቻዎቻችንና ርብርቦቻችን ትኩረት የሕዝባችን ደህንነትና ህልውና ከማስጠበቅ አንፃር እየቃኘንና ቅድሚያ ሰጥተን፣ የሁሉም ነገር ማጠንጠኛ ልማትና የሕዝባችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ መሆኑን በማመን ሁሉም ነገር ትተው ከነ አካቴው ወደ ጥፋት በገቡና ይባስ ብለው እኛንም ጎትተው ከመንገዳችን ሊያስወጡን በሚጥሩ ሀይሎች ሳንደናገር ስራችንን ማእከል አድርገን ከፍተኛ ርብርብ ስናደርግ ቆይተናል።

ልማታዊ ዲሞክራሲያዊው መስመራችንን ጨብጠን የሕዝባችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተለይ ደግሞ የወጣቶችንና የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማስፋት የሚያግዙ ተግባሮች በትግራይ እንዲከናወኑ ስናደርግ ቆይተናል።

ሕዝባችን በየጊዜው የሚያነሳቸውን የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው። በመልካም አስተዳደር መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት የቆዩ ችግሮች ፈትተን የሕዝባችን ፍላጎቶች ለመመለስ የቀበሌን መዋቅር ለማስተካከል የተጀመረው የሪፎርም ስራ ተስፋ በሚሰጥ ደረጃ ወደ ተግባር ገብቷል። ስፋትና ጥልቀት ባለው ሁኔታ ሲደረግ የነበረው የወረዳ ሪፎርም ጥናትም ሕዝባችን ልማትና ውጤታማ አገልግሎት እንዲያገኝ በሚያስችል መልኩ በዚህ ዓመት በከፍተኛ ትኩረት ለመፈፀም እንስቃሴ እየተደረገ ቆይቷል። ይህ በቀጣይ ለሚኖሩን ስራዎች እንደ አንድ ትልቅ መነሻ ሆኖ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ያግዛል።

ይሁን እንጂ በልማት ስራዎቻችን በሚፈለገው መጠንና ስፋት በሚጠበቀው መጠን ውጤት ያላስመዘገብንባቸው ሁኔታዎች አሉ። በዋናነት በመልካም አስተዳደር ጉዳይ አሁንም ችግሮቻችን ሰፋፊ መሆናቸውን አይተናል። እየተጠራቀሙ በመጡ ችግሮች ሳቢያና በማስፈፀም አቅማችን ጉድለት ምክንያት ያልፈታናቸው የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዳሉ እንገነዘባለን። በተለይም በወጣቶችና ሴቶች ተጠቃሚነት ላይ አሁንም ሰፊ ችግር እንዳለ፣ በገጠርም በከተማም እየታየ ያለው የመሬት አስተዳደር ችግር፣ አገልግሎት በመስጠት ዙርያ ያለው ችግርና መንገላታት፣ ለልማት ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ዙርያ ያሉ መዘግየቶችና እንቅፋቶች እንዲሁም ሌሎች ተዛማጅ ችግሮች የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ በዝርዝር የተመለከታቸው ጉዳዮች ናቸው።

በመሆኑም እነዚህ ችግሮች በዚሁ ዓመት “በጊዜ የለም” መንፈስ እንዲፈቱ ከፍተኛ ጥረትና ርብርብ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተመለክተናል። የልማት ስራችን የሁሉም ቋጠሮ መሆኑን በመገንዘብ፣ ለዘላቂ ህልውናችንና ደሕንነታችን መረጋገጥ ባለው ትርጉም ተገንዝበን በላቀ ቁርጠኝነትና ወኔ ልንዘምትና ልንገሰግስ ይገባል። ከዚህ የልማት እንቅስቃሴ የወጣቶችንና የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የላቀ ርብርብ ይደረጋል ብቻ ሳይሆን የእንቅስቃሴው አስኳል ይሆናል።

ከዚህም አልፎ በእያንዳንዱ አከባቢ ያለው ፀጋ ግምት ውስጥ ያስገባ የልማት አደረጃጀትና ስምሪት እንዲደረግ እና በዚሁ ላይ የሚመሰረት በገጠርም ይሁን በከተማ ወደ አዲስ የልማት እንቅስቃሴ የሚያስገቡ አቅጣጫዎችንም የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ለይቷል። የተጀመረው የቀበሌና የወረዳ ሪፎርም ስራ ተጠናክሮ ወደ ተግባር እንዲገባና በመልካም አስተዳደር መሰረታዊ ለውጥ እንዲያመጣ እንቅስቃሴ እንዲደረግ የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አቅጣጫዎችን ለይቶ አስቀምጧል።

የተከበርክ የትግራይ ሕዝብ፤

ባለፈው ዓመት በአንድ በኩል ፀረ ድህነት ትግል በማካሄድ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የትምክህት ኃይሎችን በመመከት ላይ ቆይተናል። የትግራይ ሕዝብንና ሕወሓትን ለማንበርከክ ከሁሉም አቅጣጫዎች ሲያጋጥመን የቆየው ፈተና ቀላል አልነበረም። እንደፈለግነው እንዳንሆን ማለፊያ የከለከሉን እና የጎን ውጋት እየሆኑብን ያሉት “የትግራይ ሕዝብና ሕወሓት ናቸው” ብለው ማለቂያ የሌለው ሴራና በደል ለመፈፀም ያልሞከሩት ፀረ-ሕዝብ ተግባር አልነበረም።

ይሁን እንጂ ምኞታቸውና ዓላማቸው ስለተገነዘብን በትክክለኛ መንገድ ያደረግነው ፍትሃዊ ትግልና የመመከት ተግባር የጠላቶቻችን ምኞትና ህልም አምክነን ወደፊት እየተራመድን እንገኛለን። በሕዝባችን ፅኑ አንድነትና ስምረት፣ በበሳል ንቃትና ምክንያታዊ ትግል፣ በማይነጥፍ ወኔ የተሳካ የመመከት ተግባር ስናከናውን ቆይተናል። ይህ ከትግራይ ሕዝብ ጥረትና ትግስት ውጭ እንደማይሳካ እሙን ነበር። ያለፈው የሩቅና የቅርብ ታሪክህ እንደሚያሳየው ከትግልህና ከጥረትህ ውጭ መብትህንና ጥቅምህን ለማስከበር ፍቃድ የሚሰጥህ አካል አልነበረም፤ አሁንም አይኖርም።

ሁሉ ጊዜ ለፍትህና ለእኩልነት እንደቆምክ፣ ትክክለኛ መስመርህንና ዓላማህን ይዘህ በፅናት እየታገልክ፣ በሁሉም የትግል ምዕራፎች ያጋጠሙህ መሰናክሎችንና እንቅፋቶችን እየጠራረግክ በመጓዝ ላይ ትገኛለህ። ወደፊትም ብቸኛው መንገድህ ይህና ይህ ብቻ ነው። በዚህ እልህ አስጨራሽ የትግል ምዕራፍ ያካሄድከው ወደር የለሽ የመመከት ተግባር በአጠቃላይ የትግራይ ሕዝብ፤ በተለይም ደግሞ የትግራይ ወጣቶች፣ ምሁራንና ሴቶች ለፈፀማችሁትና እየፈፀማችሁ ላላችሁት ገድል የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ የተሰማውን ክብርና ኩራት በዚህ አጋጣሚ ሊገልጽላችሁ ይወዳል።

የተከበርክ የትግራይ ሕዝብ

አሁንም ቢሆን ሁኔታዎች እየከበዱና እየባሱ በመምጣታቸው ደህንነትህንና ህልውናህን ለማስጠበቅ የምታደርገው ትግል ይበልጥ አጠናክረህ ልትቀጥልበት ይገባል። ሁሉም ሕዝብ ሊገነዘበው የሚገባ ሃቅ ሊገጥመን የሚችለው ፈተና እና ፈተናውን ለመሻገር የሚጠይቀን ትግልና ጥረት እጅግ እየከበደ ሊመጣ ይችላል። ወደፊት መራመድ ሲያቅታቸው፣ በራሳቸው ድክመትና ፀረ-ሕዝብ ተግባራቸው ፈተና ሲበዛባቸው ወደ ሌላ ወገን እየለጠፉ እያደናገሩ ዕድሚያቸውን ለማራዘም ጥረት ማድረጋቸው አይቀርም። አንድነትህንና ፅናትህን ለማደፍረስ በውስጣችን የሚታዩ ችግሮችን እንደ ዕድል ለመጠቀም እየሰሩ ይገኛሉ። አልፎ አልፎ የሚታየውን ከባቢያዊነትም ይሁን በሃይማኖት ስም በመካከልህ ልዩነት ለመፍጠር ያላሳለሰ ተግባር እየፈጸሙ ይገኛሉ። ይህን ለማስጽፈፀም ታስቦ የሚላከው ባንዳ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም። ይህ እንደሚሆን ተገንዝበህ እንደወትሮህ አንድነትህን አጠናክረህ፣ በአንድ ላይ ሆነህ ለላቀ ትግል ተዘጋጅ። የምንጊዜም ዋስትናህና የድል አድራጊነት ምስጢር አንድነትህ፣ መስመርህና ፅናትህ ነው። የትግራይ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ባለሃብቶችና ምሁራን አሁንም እንደቀድሞ በአንድነት ፀንታችሁ ሊኖረን ለሚችለው ትግል በላቀ ደረጃ ልትዘጋጁ ይገባል።

መላው የድርጅቱ ኣባላትና አመራሮችም የላቀ ፅናትና ተነሳሽነት የሚጠይቀውን ትግል ሕዝባችንን ይዘን ወደ ዘላቂ ድል ለመገስገስ መሪ ሚናችሁን ልትፈፅሙ ይገባል። ከዚህ ባለፈ የትግራይ ሕዝብ ህልውናና ደህንነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ትግል የነበረውን የትግል አቅሞች ሁሉ ለማንቀሳቀስ ይሰራል። በትግራይ ውስጥ ካሉ ፖለቲካዊ ድርጅቶችና ሲቪክ ማህበራትም በጋራ ለመስራት ሕወሓት የተለየ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ሊያረጋግጥላችሁ ይወዳል።

የተከበርክ የትግራይ ሕዝብ፤

የሕወሓት ማእላዊ ኮሚቴ በስፋት ካያቸው መሰረታዊ ጉዳዮች አንዱ በአገራችን እየታየ ያለው ፈጣን አደጋና ወዲፊትም ሊኖረው የሚችል አጠቃላይ ሁኔታ የሚመለከት ነው። በአሁኑ ወቅት በአገራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ ችግሮች እየተበራከቱ፣ ጥፋት በጥፋት ላይ እየተደራረበ፣ የጥፋቱ ስፋትና መጠን በየቀኑ እየጨመረ ወደ ከፋ አገር የመበተን ደረጀ እየደረሰ ነው። አደጋው ወደ ከፋ ደረጃ እንዲሄድ እያደረገ ያለው አንዱ ምክንያት የፓርቲ ውሕደት ለመፈፀም እየተደረገ ያለው የችኮላ እንቅስቃሴ ነው። የፓርቲ ውሕደት ጥያቄ በኢህአዴግ ውስጥ በተለያየ ጊዚያት እየተነሳ የቆየና ይህንን ለማድረግ ደግሞ ሊሟሉ የሚገባቸው መሰረታዊ ጉዳዮች እንዲታዩና በጥናት ላይ በመመስረት እንዲመለሱ መግባባት ላይ የተደረሰበት ጉዳይ ነው። ሕወሓትም ቢሆን በመሰረተ ሃሳብ ደረጃ የተለየ እምነት አልነበረውም። ሆኖም ግን ይህን ለማድረግ በሁሉም መሰረታዊ የመስመር ጥያቄዎች፣ ፕሮግራም፣ ስትራቴጂ ወደ አንድ የሚያስተሳስር አመለካካተና እምነት በሁሉም እህት ድርጅቶች ሲፈጠር ብቻ ነው መተግበር የሚችለው። አንድ ሊያደርግ የሚችል የጋራ የአመለካከትና የተግባር አንድነት በሌለበት ወቅት አንድ ድርጅት እንደ ድርጅት መጠን ህልውና ሊኖረው አይችልም። ከውሕደት በፊት የሚያዋኀድ አመለካከትና እምነት መለየት አለብን። ኢህአዴግንና አገርን እየበተኑ ካሉት የተገዙ ደባል አመለካከቶች የሚለይ መስመር እና አጥር በጠራ መልኩ ሳይለይና ሳይቀመጥ ውሕደትን ማሰብ አይቻልም። በደፈረሰ አመለካከትና በአንድነት ሊሰምሩ በማይችሉ እሳትንና ጭድ አስተሳሰቦችን በተሸከመ ኢህአዴግ አይደለም ውሕደት ቀርቶ በግምባርነት ለመቀጠል የማይችል የተበተነ ድርጅት ነው አሁን ያለው። እንደዚህ ያለ የተበተነ ድርጅት ወደ አንድ ፓርቲ ውሕደት ይመጣል ብሎ ማሰብ በራሱ ድርጅቱን ከመበተን አልፎ አገርን የሚበትን ተግባር ነው ሊሆን የሚችለው።

ከዚህም አልፎ በቅርቡ ከግንባሩ እምነትና መተዳደሪያ ደንብ ውጭ የፓርቲ ውሕደት ለመፈፀም እየተደረገ ያለው ሩጫ ችግሩ እንዲባባስ የሚያደርግ ፀረ-ዲሞክራሲያዊ አካሄድ እየሰፋ መምጣቱን የሚያሳይ ነው። የቅርፅ ውሕደት ብቻ ሳይሆን በይዘትና በያዘው ፕሮግራሙ በመሰረቱ የተለወጠ አዲስ ፓርቲ ለመመስረት ነው ጥረት እየተደረገ ያለው። ይህ ሲሆን የኢትዮጵያ ሕዝቦች ኢህአዴግ ለያዘው ፕሮግራም መሰረት አድርገው የሰጡት አገርን የመምራት ሥልጣን ያከትማል ማለት ነው። አገርን ለመምራት ኃላፊነት ያልተሰጠው አዲስ ፓርቲ እንዲመሰረት ነው እየተደረገ ያለው። እንዲህ ያለ አዲስ ፓርቲ በአገራችን ፖለቲካዊ ድርጅቶች የምዝገባ ህግ ያላለፈ፣ በሕዝቦች ፈቃደኝነት በሥልጣን ላይ ለመቆየትም ሆነ ሥልጣን ለመያዝ ለመወዳደር የማይችል ሕገ-ወጥ ድርጅት ነው የሚሆነው።

በመሆኑም በውሕደት ስም በፍጹም ፀረ-ዴሞክራሲያዊ መንገድ አዲስ አሃዳዊ ድርጅት ሊመሰረት አይገባም። በሁሉም መለኪያዎች አንድ ፓርቲ ለመሆን የሚያስችል መነሻና ምክንያት በሌለበት ኢህአዴግን አፍርሶ ሌላ ፓርቲ ለማቋቋም ማሰብ አገርን የሚበትን ተግባር ነው። ስለዚህ ኢህአዴግ እንደ ግንባር ተደራጅቶ ችግሮችን በትግል እየፈታ አገር ሊመራ ይገባል። ከጊዜ አንፃርም ይህ ሊቆይ የሚገባው ጉዳይ ነው። አጋር ድርጅቶችም በውሕደት ስም እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ህልውናችሁን የሚያጠፋ መሆኑን ልትገነዘቡ ይገባል። ይሁን እንጂ አጋር ድርጅቶች ወደ ኢህአዴግ በሙሉ አባልነት ገብታችሁ በጋራ ትግልና ጥረት አገርን የሚያድን ተግባር ሊትፈፅሙ እንደሚገባ ሕወሓት በፅናት ያምናል። ከዚህ ውጭ ሕወሓት በእንደዚህ ያለ አገርን የሚበትን ተግባር ውስጥ ገብቶ ሊንቦጫረቅ እንደማይፈልግ ሊታወቅ ይገባል። መላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በውሕደት ስም ኢህአዴግን ለማፍረስ የሚደረገው እንቅስቃሴ ኃላፊነት በተሞላበት ተገቢውን ትግል እንድታደርጉ ሕወሓት ጥሪውን ያቀርብላችኋል።

የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች

ሕገ-መንግሥታችንና ህብረ ብሔራዊ ፌደራላዊ ሥርዓታችን የሚሸረሽሩና የሚጥሱ ተግባራት በየቀኑ ማየት የተለመደ ተግባር ሆኗል። በዚሁ ወቅት የትምክህት ሐይሎች በአመለካከትና በተግባራዊ እንቅስቃሴ ጉልበት ፈጥረው አገር የሚያምሱበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በብዙ የአገራችን አከባቢዎች የሰላም እጦት እየተስፋፋ፣ በዚሁም ምክንያት ከጊዜ ወደ ጊዜ መንግሥት የማይቆጣጠራቸው አከባቢዎች እየተበራከቱ ይገኛሉ። ለመብቱና ለማንነቱ ለታገለ ሕዝብ በርካታ ግፍና በደል የሚፈፀምበት፣ ዜጎች በእርጋታ የማይኖሩበት፣ በማንነታቸው ምክንያት በዜጎች ላይ ግፍ የሚፈፀምበት፣ ለህይወታቸውና ንብረታቸው ዋስትና ያጡበት፣ በዚች አገር ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ህውከትና መፈናቀል የተበራከተበት፣ መንግሥት የዜጎች ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ እየተቸገረ የመጣበት፣ ከዚህ አልፎም የአገሪቱ የመከላከያ ከፍተኛ አመራሮች እና የአማራ ክልል አመራሮች እስከመግደል ተግባር የተፈፀመበት፣ ሌላ ቀርቶ የነዚህ ምርጥ ጀነራሎችና መሪዎች ግድያ እንኳን በአግባቡ በማጣራት ለሕዝብ ግልፅ ለማድረግ በማይቻልበት፣ የህግ በላይነት እየተጣሰ፣ የዜጎች ህይወት መጥፋትና መፈናቀል ማዳን የማይችል መንግሥትና ሥርዓት ወደ መሆን ተሸጋግረዋል ማለት ብቻ ሳይሆን ይህንን ለማስቆምና ለመግታትም ዋና ተግባሩ ያላደረገና ቁርጠኝነትም የሌለው ሆኗል።

የሕዝብ መሰረታዊ ጥያቄዎችን ወደ ጎን በመተው ሌላ ጉዳይ ላይ በማትኮር የአገሪቱ ኢኮኖሚ እየተዳከመ ወደ ከፍተኛ ድቀትና ማሽቆልቆል እየገባ ነው። የአገሪቱ ልማት የሚመራውና የሚደግፈው አጥቶ፣ ልማታዊ አቅሞች እየመከነ፣ ስራ አጥነት እየተባባሰ፣ የሕዝብ ኑሮ ውድነት ከጊዜ ወደ ጊዜ ሰማይ የሚሰቀልበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በዚህ ምክንያትም ችግር በችግር ችግር እየተመሰቃቀለና እየተደራረበ በመሄድ ላይ ይገኛል። የሕዝባችን ዋስትና የሆነው ሕገ-መንግሥታችንና ህብረ ብሔራዊ ፌዴራል ሥርዓታችን በማፍረስ አሃዳዊ ሥርዓትን መልሶ ለመትከል እየሰራ ያለውና በዋናነት ይህንን አደጋና ጥፋት እየፈጠረና እየመራ የሚገኘው ትምክህተኛው ሀይልና በዙርያው የተሰባሰበ ፀረ ሕዝብ ሐይል ነው።

በውስጣቸው ያለውን ድክመትና ፀረ-ሕዝብ ተግባር ከመፍታትና ከማጥራት ይልቅ የሁሉም ችግር “ሶስተኛ ወገን አለው” የሚል የቆየ ዘፈን ሲደጋግሙ እየታየ ነው። ለአማራ ሕዝብ የማይመለከተውና ያልተገባ ምስል እያስያዙና “ትምክህተኛ ተብለሃል!” እያሉ በዚህ ተሸፋፍነው በሕዝቦች መካከል የቆየውን ዝምድናና ወንደማማችነት ለማደፍረስ እየጣሩ ይገኛሉ። የአማራ ሕዝብ ትምክህተኞችን ታግሎ በእኩልነት የሚኖርባት አዲሲቷ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እንድትመሰረት የማይተካ ሚና የተጫወተ ሕዝብ ነው። የትግራይና የአማራ ሕዝቦች በጋራ ትግላቸው ትምክህተኛውን አሸንፈዋል። ለወደፊትም ቢሆን እነዚህ ሕዝብ ለሕዝብ አጋጭተው እንዲባላ በማድረግ መኖር የሚፈልጉና ኃላፊነታቸውን ትተው ለጥፋት የተሰማሩ ሓይሎች በተደራጀ መንገድ ሊታገላቸው ይገባል።

መላው የአገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችም ህብረ-ብሔራዊ ፌዴራላዊ ሥርዓታችንን ለማዳን በሚደረገው ወሳኝ ትግል ከማንኛውም ጊዜ በላይ አገራችንን ለማዳን ሊረባረብ ይገባል።ሕብረ ብሔራዊ ፌዴራላዊ ሓይሎች የጀመራችሁትን ትግልና ሰፊ ትብብር መድረኮች አማራጭ የሌለው መሆኑን ተገንዝባችሁ ትግላችሁን አጠናክራችሁ ልትቀጥሉበት ይገባል። ሕወሓትም የተጀመረውን ትግል ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ ሊያረጋግጥላችሁ ይወዳል።

በዚህ አጋጣሚ ሕገ-መንግሥት፣ ሰላምና የሕዝቦችና የአገርን ደሕንነት በመጠበቅ የላቀ ኃላፊነት ያለብህ የአገር መከላከያ ሰራዊት፤ አገራችን እያጋጠማት ያለውን አደጋ በሚገባ ተገንዝበህ ከጥፋት ለማዳን እያደረገው ያለው ርብርብ፣ ለዚች ልዩ ታሪክና ክብር ያላት አገር ሉኣላዊነቷንና ሰላሟን በመጠበቅ ረገድ ዛሬም እንደወትሮ በላቀ ደረጃ ሕዝባዊ ኃላፊነትህን ተቋማዊ እንድትህን አጠናክረህ በምታደርገው ሁለንተናዊ እንቅስቃሴም የትግራይ ሕዝብና ሕወሓት ከጎንህ ሆነው አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚፈፅሙ ልናረጋግጥ እንወዳለን።

በሕገ- መንግሥቱ መሰረት ስድስተኛው አገር አቀፍና ክልላዊ ምርጫ በያዝነው ዓመት የግድ መካሄድ ያለበት ነው። በመሆኑም ሕወሓትና የትግራይ ሕዝብ ምርጫው በወቅቱ እንዲካሄድ በተደጋጋሚ አቋማቸውን እየገለፁ ቆይተዋል። ይሁን እንጂ ምርጫው ለማካሄድ የሚያስችል ምንም ዓይነት ዝግጅት እየተደረገ አይደለም። “በቂ ዝግጅት አላደረግንም” ተብሎ ምርጫውን ለማራዘም የሚደረገው ጥረት ፈፅሞ ተቀባይነት ሊኖሮው አይችልም። በአገራችን ያሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ነፃ የመወዳደር ዕድል አግኝተው ሕዝብ በነፃ ፍላጎቱ የሚመርጠውን መንግሥት ወደ ሥልጣን እንዲመጣ በሕዝብ ፍጹም ፈቃድ በሥልጣን ላይ እንዲቆይ የሚያደርግ ሕገ-መንግሥታዊ መብት በጥብቅ መከበር አለበት። ይህ በማይሆንበት ወቅት መላው የአገራችን ሕዝቦች መብታችሁንና ሕገ-መንግሥታዊ ሥልጣናችሁን አደጋ ላይ እየጣለ መሆኑን አውቃችሁ የላቀ ትግል ልታደርጉ በሚጠይቅ አስገዳጅ ጊዜ ላይ እንገኛለን።

የተከበርክ የኤርትራ ሕዝብ

የትግራይና የኤርትራ ሕዝብ ለጋራ መብትና ጥቅም በጋራ የታገሉ ወንድማማች ሕዝቦች ናቸው። የነበረውና አሁንም ያለው ዝምድናና መደጋገፍ ወደ ዘላቂ አስተማማኝ ደረጃ ለማድረስ ባለፈው ዓመት የተጀመረው የሰላም ጭላንጭል በዚህ ዓመትም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። በጋራ ለዘላቂ ሰላም ተደጋግፈን ልንሰራ ይገባል። የጀመርነው አዲስ እፎይታና ሰላም ዋስትና ያለው እንዲሆንም የሁለቱም ሕዝቦች ትስስርና ግንኙነት እንዲጠናከር መስራት አለብን። የትግራይ ሕዝብና ሕወሓትም ይህንን ለማጠናከር ከነሱ የሚፈለገውን ሁሉ እንደሚፈፅሙ ደጋግመን ልናረጋግጥልህ እንወዳለን።

የማንሻገረው ፈተና አይኖርም
ዘልዓለማዊ ክብርና ሞገስ ለስማእቶቻችን!
የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ
ጥቅምት 4 ቀን 2012 ዓ.ም.
መቐለ

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ