ODP

አዲሱ የኦዴፓ (የቀድሞው ኦሕዴድ አርማ)

ጥቅምት 2012

የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ባለፉት ሁለት ቀናት ሲያካሂድ በቆየው ስብሰባ አሁን የደረስንበትን የትግል ምዕራፍ እና በፓርቲው ውስጥ የሚስተዋሉ ጥንካሬዎችና ጉድለቶችን በጥልቀት በመገምገም የፓርቲው ውስጣዊ ክፍተቶችን ለመቅረፍና በቀጣይ ጊዜ የሚደረገውን ትግል ስኬታማ ለማድረግ የሚያግዙ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ስብሰባውን አጠናቋል። በዚሁ መሠረት የኦዴፒ ማዕከላዊ ኮሚቴ ባለፉት ሁለት ቀናት ስብሰባው ባካሄደው ግምገማ ላይ ተመሥርቶ ያወጣው መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል።

ኦዴፓ ሕዝብ ውስጥ ተወልዶ ያደገ የትግል ፓርቲ ነው። በትግል ጉዞው ውስጥ በሕዝቡ ጥያቄና ፍላጎት ላይ በመመሥረት ራሱን በማየትና በመገንባት ዛሬ ላይ ደርሷል። ፓርቲው ሰሞኑን ባካሄደው ስብሰባው ከከፍተኛ አመራሩ ጀምሮ በየደረጃው ባለ መዋቅር ላይ የአመለካከት አንድነት ጉድለትን ከመሰረቱ በመቅረፍ የሕዝቡን ጥያቄ በተሟላ ሁኔታ እየመለሰ መሔድ አሁን የደረስንበት የትግል ምዕራፍ የሚፈልገው መሆኑ ላይ ስምምነት ተደርሷል።

እንደ ፓርቲና እንደ መንግሥት የሚሰጥን ተልዕኮ በተቆርቋሪነትና በሕዝብ ወገንተኝነት መወጣትና በተጠያቂነት መንፈስ መንቀሳቀስን በተመለከተ ክፍተት እንዳለ ተመልክቷል። በመሆኑም ከከፍተኛ አመራሩ ጀምሮ እስከ ታች ድረስ በአመለካከትና በተግባር አንድነት እንዲሁም በተጠያቂነት መንፈስ የሕዝባችንን ጥያቄና ፍላጎት መመለስ ወሳኝ መሆኑ ላይ ከመግባባት ተደርሷል። የውስጠ ፓርቲ የአመለካከትና የተግባር አንድነትን በማጠናከር እስካሁን ምላሽ የተሰጠባቸው የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄዎችን እንደ መነሻ፣ ምላሽ ያላገኙትን ደግሞ በተለየ ሁኔታ በመመልከት በአጭር ጊዜ ውስጥ ተቆጥረው ምላሽ እንዲያገኙ እንደሚታገል አቅጣጫ አስቀምጧል።

ብዙ ብሔር ብሔረሰቦች፣ ብዙ ቋንቋና ባህሎች በሚገኙበት አገር ውስጥ የፌዴራሊዝም ሥርዓት አማራጭ የሌለው ሥርዓት ነው። ይህ ሥርዓት የብዝሃነትን ውበት በመንከባከብ የአገራችንና የሕዝባችን የጋራ ባህሎች መገንባትን የምናረጋግጥበት ወሳኝ መሣሪያ ነው። ስለሆነም የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ትክክለኛና እውነተኛ የብዝሃነት ፌዴራሊዝም ሥርዓትን በኢትዮጵያ ተግባራዊ በማድረግ የአገራችንን ሕዝቦች እኩልነትና ነፃነት ለማረጋገጥ የማያወላዳ አቋም እንዳለው በድጋሚ ያረጋግጣል።

ይሁን እንጂ ባለፉት ጊዜያት በአፈጻጸም የታዩ ተግባራት የፌዴራሊዝም ሥርዓትን የአስተዳደር ባህልና እሴትን የሚቃረኑ ብዙ ተግባራት ሲፈጸሙ ቆይተዋል። በግምገማ መድረካችን እንዳየነው ባለፉት ጊዜያት የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ሁሉንም ሕዝቦች በፍትሐዊነት እንደማያሳትፍ እውነተኛ ዴሞክራሲ በውስጡ ያልተረጋገጠ እንደሆነ ያሳያሉ።

ከዚህም ሌላ የሕዝቡ ጥቅሞችና ፍላጎቶች የመንግሥትን ሥልጣን እጃቸው ባስገቡት ጥቂቶች ሲጋጥ እንደነበረ ይታወቃል። የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ እነዚህ ድክመቶች ታርመው እውነተኛ የብዝሃነት ፌዴራሊዝም ሥርዓት መሬት እንዲይዝ የጀመረውን ትግል በማስቀጠል ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በነፃነት፣ በእኩልነት፣ በወንድማማችነትና በብልፅግና የሚኖሩባትን አገር ለመገንባት ጠንክሮ እንደሚሠራ ይገልጻል።

በሌላ በኩል ትላንት ትክክለኛው የፌዴራሊዝም ሥርዓት መሬት እንዳይይዝ ሕዝቡን የማይወክሉ ጥቂት ቡድኖች በያዙት የመንግሥት ሥልጣን ሕገመንግሥቱንና የፌዴራሊዝም ሥርዓቱን ሲጥሱ የነበሩ ቡድኖች፤ ዛሬ ራሳቸውን ለሕገመንግሥቱ የቆሙና የፌዴራሊዝም ሥርዓት ጠበቃ እንደሆኑ አድርገው በሕዝቡ ውስጥ ብዥታን ለመፍጠር የሚነዙት የውሸት ፕሮፖጋንዳ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ኦዴፓ ለማስገንዘብ ይወዳል።

የኢሕአዴግ ውስጣዊ ሪፎርም የፓርቲውን የትግል አካሄድ፤ የሕብረተሰቡን ጥያቄና ፍላጎት መሠረት ያደረገ ነው። ይህም በሐዋሳ ከተማ በተደረገው የፓርቲው 11ኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ በምሁራን ተጠንቶ እንዲቀርብና ውሳኔ እንዲያገኝ አቅጣጫ የተሰጠበት ነው። የሕዝቡ ጥያቄና የፓርቲው ውስጣዊ ውሳኔዎች በጥቅሉ ሲታይ ፓርቲው በአደረጃጀቱ ፣ በዴሞክራሲዊነቱና፣ በአሳታፊነቱ ራሱን እንዲያይ የተሻለ እድል የፈጠረ ነው።

የተደረገው ጥናትም የኢሕአዴግ አመሠራረት ዴሞክራሲያዊና አቃፊ ያልሆነ፣ የአገር ግንባታ አቅምን የሚሸረሽር፣ ገሚሱን የአገሪቱ ሕዝቦች ወደ ጎን በመተው በጥቂት ቡድኖች የሚወሰን መሆኑ ተለይቷል።

የኢሕአዴግ አወቃቀር ሲመራበት የነበረው አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሕዝብን ውሳኔ ሰጪነት የሚገድብ ስለሆነ፤ ለደረስንበት የትግል መድረክ የሚመጥን አይደለም። ባለፉት ጊዜያት የነበረውን የዝርፊያ መዋቅር፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት፣ ፀረ ዴሞክራሲያዊ ድርጊቶች ሲፈፀሙበት የነበረውን መዋቅር በማፈራረስ፤ ዴሞክራሲና ነፃነት የሰፈነባትና የበለፀገች አገር ለመገንባት በኢሕአዴግ አወቃቀር ላይ ሪፎርም ማድረግ ወሳኝ ጉዳይ መኾኑን ኦዴፓ ያምናል።

በብዙ ጉድለቶች የታጠረው የኢሕአዴግ አወቃቀር የኦሮሞንና የአገራችን ሕዝቦችን ጥያቄና ፍላጎት ለመመለስ ያልተመቻቸ መሆኑን የኦዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ተንትኖ ተግባብቶበታል።

በዚሁ መሠረት ኢሕአዴግን በማደስ፤ በዘመነ አሠራርና ሥርዓት የሚመራ ፓርቲ በመፍጠር፤ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ፅንሰ ሐሳብን በመደመር ፅንሰ ሐሳብ ለመተካት ውይይት እየተደረገ መሆኑ ይታወቃል።

የመደመር ፅንሰ ሐሳብ ያለፉትን ስኬቶች ይበልጥ በማጎልበት የሚታዩትን ጉድለቶች ከመሠረቱ በመፍታት የአዲሱን ትውልድ መብትና ጥቅም የሚያረጋግጥ መሆኑን ኦዴፓ ያምናል።

በዚሁ መሠረት የኢሕአዴግ ሪፎርም ጉዳይ እውነተኛ የፌደራሊዝም ሥርዓት ዴሞክራሲዊ ብሔርተኝነትና አገራዊ አንድነት ሚዛኑን ጠብቆ ብዝሃነት የሰፈነባትና የበለፀገች አገር በመገንባት የሕዝብን ጥቅምና ፍላጎት ለማስጠበቅ የተመረጠ ዘዴ መሆኑን በማመን ለስኬታማነቱ ለመሥራት ወስኗል።

በመጨረሻም የደረስንበት የትግል ምዕራፍ የተወሳሰበ ቢሆንም የፓርቲውን ውስጣዊ ድክመት በመቅረፍ ሰፊውን ሕዝብ ከጎኑ በማሰለፍ ከፊት ለፊቱ የሚጠብቀውን ፈተና በማሸነፍ አዲስ ታሪክ እንዲመዘገብ ለማድረግ የጀመረው ትግል ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ኦዴፓ ይገልጻል።

በኦዴፓ ሲወሰኑ የነበሩ ውሳኔዎችና ሲቀመጡ የነበሩ አቅጣጫዎች ሕዝባችንን ድል እያጎናፀፉ ለዚህ ምዕራፍ አድርሰውናል። አሁን የተቀመጡ አቅጣጫዎችም ሕዝባችን በመሥዋዕትነት የተጎናፀፋቸውን ድሎች ጠብቆ እንዲያቆያቸውና ተጨማሪ ድሎችን የሚያጎናፅፉት መሆኑን ተረድቶ ለአፈጻጸማቸው በጋራ መረባረብ ይጠበቅበታል። ትውልድ አያሌ መሥዋዕትነት የከፈለበት የሕዝባችን ጥያቄዎች በሙሉ ምላሽ እንዲያገኙ ከምንጊዜውም በበለጠ የሚታገል መሆኑን ኦዴፓ በድጋሚ ያረጋግጣል።

ተባብረን ከሠራን የማንፈታው ችግር አይኖርም !!

ጥቅምት 2012
የኦዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ