ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተሠጠ መግለጫ

ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት

የተከበራችሁ የአገሬ ሕዝቦች!

ሰሞኑን በተከሠተው እጅግ አሳዛኝ ግጭት በዜጎቻችንና በንብረታቸው ላይ በደረሰው ሁሉ ማዘኔን አስቀድሜ ለመግለጥ እወዳለሁ።

ያጋጠመን ፈተና ኢትዮጵያውያን ካልተባበርንና አንድ ኾነን ካልቆምን መንገዳችን ምን ያህል አስቸጋሪና አስፈሪ ሊሆን እንደሚችል ማሳያ ነው። ችግሩ የብሔርና የሃይማኖት መልክ እንዲኖረው ለማድረግ ተሞክሯል። በዚህም የተነሣ ወገኖቻችን በአሰቃቂ ሁኔታ መሥዋዕት ኾነዋል።

የጸሎት ቤቶች ተቃጥለዋል። የንግድ ድርጅቶችና የመኖሪያ ቤቶች ወድመዋል። የተፈናቀሉ ወገኖች በተለያዩ ቦታዎች ተጠልለዋል። መተላለፊያ ያጡ ዜጎችም በየከተሞቹ ከርመዋል። እንኳንስ ለማየት ለመስማት የሚዘገንን እኩይ ተግባር በወገናችን ላይ ተፈጽሟል።

በልብ ሰባሪው ክሥተት ብናዝንም ኢትዮጵያውያን ዛሬም ታላቅ ሕዝቦች፣ አስተዋዮችና አመዛዛኞች መሆናቸውንም አይተናል። ቤተ ክርስቲያን እንዳይቃጠል የሚከላከሉ ሙስሊሞች፣ መስጅድ እንዳይቃጠል ዘብ የሚቆሙ ክርስቲያኖች አሉን። ከእነርሱ ብሔር ውጭ ለኾነው ወገናቸው ሲሉ መሥዋዕትነት የከፈሉ ኢትዮጵያውያን አሉን። ሰላምና ደኅንነትን ለማውረድ ሌት ተቀን የሚደክሙ ሽማግሌዎች አሉን። ቤት ንብረታቸውን ላጡ መጠለያ የሚሆኑ፣ መንገድ ለተዘጋባቸው ማደሪያ የሚያዘጋጁ ብዙ ወገኖች አሉን። የፈተናው ዓላማ ተስፋ እንድንቆርጥና መንገዳችንን እንድንቀይር መኾኑን ተረድተው፣ ዛሬ በሆነው ነገር ሳይደናገጡ፣ ነገን አሻግረው የሚመለከቱ ዜጎች አሉን። ለሕግና ለኅሊና የሚቆሙ የመከላከያና የፖሊስ አባላት አሉን።

ይህ ሁሉ ለምን እንደመጣብን እናውቃለን። ከዚህ የበለጠ ፈተና ቢያጋጥመንም እንኳን የጀመርነውን ጉዞ አናቋርጥም። አረሙን እየነቀልን፣ ስንዴውን እየተንከባከብን እንሄዳለን እንጂ፤ ለአረሙ ስንል ስንዴውን አንተወውም። በመንገዳችን የሚያጋጥመንን ዕንቅፋት እያነሣን መንገዳችንን እንቀጥላለን እንጂ ወደ ቀኝም ወደ ግራም ወለም ዘለም አንልም። ፈታኞቻችን ያልተገነዘቡት ነገር ቢኖር የተከፈለውን መሥዋዕትነት ሁሉ ከፍለን የኢትዮጵያና የሕዝቦቿን ብልጽግና የምናረጋግጥ መሆናችንን ነው።

የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥና አጥፊዎች በሕግ ፊት ቀርበው ተገቢው ሁሉ እንዲያገኙ ያለማወላወል እንሠራለን። በተፈጠረው አሳዛኝ ክሥተት የተጎዱት እንዲያገግሙ፤ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉት እንዲመለሱ፣ ንብረታቸው የጠፋባቸው እንደገና እንዲቋቋሙ ከሕዝባችን ጋር ሆነን በጽናት እንሠራለን። ይህንን ለማሳካትም የሃይማኖት ተቋማት፣ የሲቪክ ማኅበራትና መላው ሕዝብ ከጎናችን እንዲቆም ጥሪ እናደርጋለን።

እርስ በርሳችን ከተከፋፈልንና ከተጋጨን አሸናፊዎቹ ሌሎች ናቸው። ማናችንም አናሸንፍም። ጠላቶቻችን ምን እንድንኾን እንደሚፈልጉ በጥቂቱ አይተነዋል።

ከዚህ የከፋ እንዳይገጥመን መንግሥትና ሕዝብ የሚጠበቅባቸውን ማድረግ አለባቸው። መንግሥት ከመንግሥት የሚጠበቀውን ሁሉ ያደርጋል። ሕዝቡም ባለመለያየት፣ ለአጥፊዎች አጀንዳ ባለመመቻቸት፣ አንዱ ለሌላው ጋሻና መከታ በመኾን፤ ወንጀለኞችን አሳልፎ ለሕግ በመሥጠት፣ የተጎዱ ወገኖቹን በመርዳት ታላቅነቱን ሊያስመሰክር ይገባል።

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራ፣ ተከብራና በልጽጋ ለዘላለም ትኑር!

ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!

ጥቅምት 15 ቀን 2012 ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ