የሕወሓት መግለጫ

ሕወሓት በውሕደቱ ስብሰባ ላይ አልገኝም አለ

ለኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞከራሲያዊ (ኢሕአዴግ) ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት (አዲስ አበባ)

ጉዳዩ፦ የኢሕአዴግ ምክር ቤት የስብሰባ ጥሪን ይመለከታል

እንደሚታወቀው የኢሕአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ኅዳር 6 ቀን 2012 ዓ.ም. የውሕደት ጥናት ውጤት ላይ ለመወያየት በሚል ባካሔደው ስብሰባ አጀንዳውን ስቶ በሕግ ባልተሠጠው ሥልጣን ላይ የኢሕአዴግ እኅትና አጋር ድርጅቶች እንዲዋሓዱ በአብላጫ ድምፅ ወስኗል።

የተላለፈውን ውሣኔ ተከትሎ ውሕደትን የሚመለከት አጀንዳ ላይ እንዲወስን የኢሕአዴግ ምክር ቤት ለኅዳር 11 ቀን 2012 ዓ.ም. ለስብሰባ ተጠርቷል። የደረሰንን የስብሰባ ጥሪ መሠረት በማድረግ በሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ በተደረገው ውይይት፤ የኢሕአዴግ ምክር ቤት የውሕደት አጀንዳን ተወያይቶ ለመወሰን ሕጋዊና ፖለቲካዊ ሥልጣን እንደሌለው ተደምድሟል።

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የውሕድ ፓርቲ የጥናት ውጤት ላይ ለመወያየት የያዘው አጀንዳ ወደ ጎን በመተው ወደ ውሕደት እንሻገር በሚል ያስተላለፈው ሕጋዊ ያልኾነ ውሳኔ በምክር ቤቱ እንዲደገም እየተደረገ በመኾኑ፤ ከዚህም በተጨማሪ የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ በጥናቱ ውጤት ላይ እንዲወያይ ተወስኖ እያለ፤ ምንም ዐይነት ውይይት ሳይደረግ በጥደፊያ የምክር ቤት ስብሰባ መጠራቱ ተገቢ ባለመኾኑ፤ በውሕደት ሰበብ ሕወሓትን ለማፍረስ የሚያስችል ሕጋዊ ሥልጣን ስለሌለን በኢሕአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ተገኝተን የሕወሓትን መዋሐድ ለመወሰን አንችልም። የሕወሓት እጣፈንታ ሊወስን የሚችለው በየደረጃው ውይይት ከተደረገበት በኋላ በሕወሓት ጉባዔ ብቻ በመኾኑ፤ በአሁኑ ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ የማንችል መኾኑን እናሳውቃለን።

ከሰላምታ ጋር
ዓለም ገብረዋኅድ
የሕወሓት ፖለቲካዊ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ
ኅዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ