የታሰሩት በአውሮፓ ሕብረት ባደረጉት ንግግር እና ከፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ጋር በመታየታቸው ይሆናል ተብሎ ይገመታል

Prof. Merera Gudina

ኢትዮጵያ ዛሬ (ረቡዕ ኅዳር ፳፩ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም. Nov. 30, 2016)፦ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ሊቀመንበር የሆኑት ፕ/ር መረራ ጉዲና መታሰራቸው ተጠቆመ። ፕ/ር መረራ የታሰሩበት ምክንያት ለጊዜው በትክክል ባይታወቅም፤ በአውሮፓ ሕብረት ተገኝተው ባደረጉት ንግግርና ከፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ጋር በመታየታቸው ሊሆን ይችላል ተብሎ ይጠረጠራል።

የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች እንደሚሉት ከሆነ ፕ/ር መረራ ዛሬ ማምሻውን ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የደህንነት ሰዎች በቁጥጥር ስር አውለዋቸዋል።

የታሰሩበት ምክንያት ከአርበኞች ግንቦት ሰባት ሊቀመንበር ከሆኑት ከፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ጋር ረቡዕ ጥቅምት ፴ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም. (November 9, 2016) የአውሮፓ ሕብረት በብራስልስ ኢትዮጵያውያንን ጋብዞ ባደረገው ስብሰባ ላይ በመታየታቸው እንደሆነ ይታመናል።

የገዥው ፓርቲ ደጋፊዎች በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ ሁለቱ ፕሮፌሰሮች ለምን አብረው ታዩ በማለት ጫና ሲያሳድሩ እንደነበር ይታወቃል።

ምንም እንኳን የታሰሩበት ምክንያት እስካሁን ባይታወቅም፤ ከዚህ ቀደምመንግሥት በፀረ ሽብር ሕጉ ማንም ሰው አሸባሪ ተብለው በፓርላማ ከተፈረጁ ድርጅቶች ጋርም ሆነ ግለሰቦች ጋር መገናኘትን ከሚከልክለው ሕግ እንደሆነ ይታመናል።

ከዚህ ሌላ ፕ/ር መረራ በዚሁ የአውሮፓ ጉዞአቸው በሆላንድ ባደረጉት ሕዝባዊ ውይይት ላይ መንግሥትን የተቹ ከመሆናቸውም በላይ፤ አዲሱ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ የአያቱን ከ”ወልደሚካኤል” (የትግሬ ስም) ወደ ”ነጋዎ” (የኦሮሞ ስም) ቀይሮ ”ኦሮሞ ነኝ” ማለቱን በማስረጃ ማጋለጣቸው ሌላው ምክንያት ሳይሆን እንደማይቀር ታውቋል።

ይህ ዜና እስከተጠናከረበት ሰዓት ከመንግሥት በኩል የተሰጠ መግለጫ የለም።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!