Miruts Yifter

ኢትዮጵያ ዛሬ (ሰኞ ታህሳስ ፲፯ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም. Dec. 26, 2016)፦ ባለፈው ኅሙስ ታህሳስ ፲፬ ቀን ፳፻፱ (Dec. 22, 2016) በሰባ ሁለት ዓመቱ ሕይወቱ ያለፈችው፣ የጀግናው አትሌት ሻምበል ምሩጽ ይፍጠር የጸሎተ ፍትሐቱ ሥነሥርዓት ነገ ማክሰኞ ታህሳስ ፲፰ ቀን (Dec. 27) ጠዋት አምስት ሰዓት ላይ ቶሮንቶ ካናዳ በሚገኘው ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን እንደሚፈጸም ለኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ የደረሳት ዘገባ አስረዳ።

ሻምበል ምሩጽ ይፍጠር በኦሎምፒክ ታሪክ እ.ኤ.አ. 1972 በጀርመን ሙኒክ በአስር ሺህ ሜትር ርቀት የነኀስ ሜዳሊያ፣ በ1980 በሞስኮ ደግሞ ሁለት የወርቅ ሚዳሊያ በአምስት እና በአስር ሺህ ሜትር ለኢትዮጵያ ማስገኘቱ ይታወሳል።

እ.ኤ.አ. 1973 በሌጎስ በተደረገው የኦል አፍሪካ ጌምስ፣ በአስር ሺህ ሜትር የወርቅ፣ በአምስት ሺህ ሜትር ደግሞ የብር ሜዳሊያዎች ለማግኘት መብቃቱ አይዘነጋም።

የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እ.ኤ.አ. 1977 በደስልዶልፍ እና በ1979 በሞንትሪያል ባዘጋጃቸው ውድድሮች በአስር ሺህ እና በአምስት ሺህ ሜትር ርቀቶች በሁለቱም ዓመታት ሁለት ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማግኘት፤ ጀግናው አትሌት ሻምበል ምሩጽ ለበርካታ ኢትዮጵያውያን ምርጥ አትሌቶች የጀግና ተምሳሌት ሊሆን የቻለ ምርጥ ኢትዮጵያዊ አትሌት እንደነበር ይታወቃል። ከእነዚህም ውስጥ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ እና ቀነኒሳ በቀለ ይጠቀሳሉ።

አትሌት ሻምበል ምሩጽ ይፍጠር ”ማርሽ ቀያሪው” (Miruts the Shifter) በሚል ቅጽል ስም ይታወቅ እንደነበር አይዘነጋም። ይህንንም ስም የተጎናጠፈው፣ በውድድሮቹ መጨረሻ ሰዓት ላይ ፍጥነቱን በመጨመር አሸናፊነቱን ይጎናጸፍ ስለነበር እንደሆነ የታወሳል።

አትሌት ሻምበል ምሩጽ ይፍጠር የሰባት ልጆች አባት ነበር።

የኢትዮጵያ ዛሬ ድረገጽ ዝግጅት ክፍል ለቤተሰቦቹ፣ ለዘመድ አዝማዶቹና ለአፍቃሪዎቹ መጽናናትን ይመኛል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ