Addis Ababa

ኢዛ (ረቡዕ ታህሳስ ፳፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም. Jan. 04, 2017)፦ በ1994 ዓ.ም ተግባራዊ መደረግ የጀመረው ዘጠነኛው ማስተር ፕላን በ2006 ዓ.ም. የመጠቀሚያ ጊዜው አብቅቷል። አሥረኛው ማስተር ፕላን ከኦሮሚያ ልዩ ዞን ጋር አቀናጅቶ ለማካሄድ በርካታ ሥራዎች የተሠሩ ቢሆንም፣ ከኦሮሚያ ክልል ተቃውሞ በመቅረቡ እንዲቀር ተደርጓል። በዚህ ምክንያት ባለፉት አራት ዓመታት አዲስ አበባ ይፋ ማስተር ፕላን ሳይኖራት ቆይቷል።

ይሁንና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ማስተር ፕላኑ ከመጽደቁ በፊት የወረዳ፣ የክፍላተ ከተማና ማዕከል የሚገኘው ዋናው ምክር ቤት ጋር በጋራ እንዲወያዩበት ማድረጉን ገልጿል።

ታኅሳስ 22 ቀን 2009 ዓ.ም. በተካሄደው ውይይት በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ወይም 25 ዓመታት ተግባራዊ የሚደረገው ማስተር ፕላን ይዘትና ይዟቸው የሚመጣቸው ተስፋዎች ላይ፣ የቀድሞው የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ፕሮጀክት ኃላፊ አቶ ማቴዎስ አስፋው ማብራሪያ ሰጥተዋል።

አዲስ አበባ ከተማ በ130 ዓመት ታሪኳ ዘጠኝ ማስተር ፕላን አስተናግዳለች።

ከዚህ ቀደም ወደ ጎን ስትለጠጥ ቆይታ ያላትንም 54 ሺሕ ሔክታር መሬት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ግንባታ ያካሄደችበት አዲስ አበባ፣ ከኦሮሚያ ክልል በደረሰው ከፍተኛ ደም አፋሳሽ ተቃውሞ ሳቢያ "በአዲሱ ማስተር ፕላን ወደ ጎን መለጠጧን አቁማ ወደ ላይ ከፍ ማለት ትጀምራለች" ሲሉ አቶ ማቴዎስ ገልጸዋል።

በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት የአዲስ አበባ ሕዝብ ቁጥር አሁን ካለበት አራት ሚሊዮን በተጨማሪ፣ 1.3 ሚሊዮን ሕዝብ አዲስ ነዋሪ ሆኖ እንደሚመዘገብና ይህ ሁሉ ሕዝብ በመሀል ከተማ እንደሚሰፍር ይታወቃል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ