አትሌት አብርሃ | Abraha Milaw
አትሌት አብርሃ የስቶክሆልም ማራቶንን ካሸነፈ በኋላ። (ፎቶ፣ የስዊድኑ TV4)

ኢዛ (ቅዳሜ ግንቦት ፳፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም. June 3, 2017)፦ በዛሬው ዕለት በስቶክሆልም፣ ስዊድን በተደረገው ፴፱ኛው የስቶክሆልም ማራቶን ኢትዮጵያውያኖቹ አትሌቶች በሴቶችም፣ በወንዶችም አንደኛና ሁለተኛ በመሆን ውጤቱን ተቆጣጠሩት።

በወንዶች፣ የ፳፱ ዓመቱ አትሌት አብርሃ መላው አሰፋ ውድድሩን በ2:11:36 ሰዓት በመጨረስ አንደኛ በመውጣት አሸናፊ ሲሆን፣ በሴቶች ደግሞ አትሌት ቆንጅት ጥላሁን አንደኛ የወጣችው ውድድሩን በ2:35:45 ሰዓት በማጠናቅቅ ነበር።

አትሌት በላይነሽ ሺፈራው እና አትሌት ሳሙኤል ጌታቸው በሴቶችና በወንዶች ሁለተኛ የወጡ ሲሆን፣ በላይነሽ ውድድሩን በ2:36:00 ሰዓት ስታጠናቅቅ፣ ሳሙኤል ደግሞ ውድድሩን የጨረሰው በ2:12:27 ሰዓት መሆኑ ታውቋል።

አትሌት አብርሃ ያስመዘገበው የዛሬው ሰዓት በስቶክሆልም ማራቶን ታሪክ የሁለተኛነት ስፍራ የተሰጠው ሲሆን፣ ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት ኬንያዊው አትሌት ስታንሊ ኮኢቼ ያስመዘገበው 2:10:58 ቀዳሚነቱ እንደያዘ ይገኛል።

”ክብረወሰኑን መስበር ፈልጌ ነበር። እንደጠበቅኹት ባይሆንም፣ የዛሬው ውጤት ምንም አይልም። ምንም እንኳን ክብረወሰኑን የማግኘት ጉጉት የነበረኝ ቢሆንም፣ በውጤቴ አልተከፋሁም” በማለት አትሌት አብርሃ ለጋዜጥኞች ከውድድሩ ፍጻሜ በኋላ ገልጧል።

አትሌት ቆንጅት ጥላሁን | Konjit Tilahun
አትሌት ቆንጅት የስቶክሆልም ማራቶንን ካሸነፈች በኋላ። (ፎቶ፣ Jonas Ekstromer/TT)

አትሌት ቆንጅት በበኩልዋ፤ ”በጣም ደስተኛ ነኝ። ከሰላሳ ሁለቱ ኪ.ሜ. በኋላ እንደማሸንፍ ታውቆኝ ነበር። በጥሩ አቋም ላይም ነበርኩ” በማለት ለስዊድን መገናኛ ብዙኀን ገልጣለች።

የስቶክሆልም ማራቶን ውጤት (ከአንደኛ እስከ ሰባተኛ)

በወንዶች

 1. Abrham Milawi (ETH) 2:11:36
 2. Samuel Getachew (ETH) 2:12:27
 3. Samuel Kalalei (KEN) 2:12:36
 4. Daniel Yator (KEN) 2:13:13                           
 5. Mike Mutai (KEN) 2:13:22     
 6. Yuki Kawauchi (JPN) 2:14:04
 7. Eric Kering (KEN) 2:15:15

በሴቶች

 1. Konjit Tilahun (ETH) 2:35:45
 2. Balaynesh Shifera (ETH) 2:36:00
 3. Alice Kibor (KEN) 2:36:19
 4. Tiruwork Mekonen (ETH) 2:37:03
 5. Yoshiko Sakamoto (JPN) 2:41:34
 6. Mikaela Larsson (SWE) 2:42:21                       
 7. Lisa Ring (SWE) 2:43:14

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!