በስዊድን የተካሄደ ብርቱካን ትፈታ ህዝባዊ ስብሰባ

ስሜነህ ታምራት - ከስዊድን

Stockholm 2010, 02, 20 Free Birtukan!

የመሰብሰቢያ አዳራሹ በኢትዮጵያና በስዊድን ሰንደቅ ዓላማዎች ከብርቱካን ፎቶግራፍ ጋር ተውበዋል። ወደ ውስጡ ሲገባ ብርቱካን ቃሌ ብላ ከሰጠችው የተወሰደው የእውነተኛ ምስክርነት ንግግርና ለእስር ምክንያት ተብሎ የቀረበው በስዊድን ጉብኝትዋ ስለምህረቱ አፈፃፀም ያደረገችው ንግግር ይሰማል። በተለያዩ ሀገሮች ከህዝብ ጋር ስትወያይ ”ባገራችን ሠላም ዲሞክራሲና የሕግ የበላይነት እንዲከበር እኔ በዓላማዬ ፅኑ ነኝ እናንተስ?” በማለት ያስተላለፈችውና በማንኛውም ሐቀኛ ዜጋ ዘወትር የማይረሳው የቆራጥነት መንፈሧ በአየር ላይ ይታያል።

 

ሻምበል ”እኛስ ኮራን በብርቱካን” በማለት መታሰብያነቱን ለዚች እንቡጥ እስረኛ ያዜመው ጣዕመ ዜማ በንግግሮቿ ጣልቃ ይደመጣል። ወደ አዳራሹ ሲገቡና የእሷን ንግግር ሲሰሙ እንባ ያዘሉ አይኖች በርካታ ነበሩ። ”ኢትዮጵያ ሐቀኛ ልጆች እስከመቼ ነው በአምባገነኖች እሳት የሚለበለቡት” እያሉ በቁጭትም ተናግረዋል።

 

የአንድነት ለዲሞክራሲና ፍትህ ፓርቲ ሊቀመንበር ዳኛ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ለሁለተኛ ጊዜ ታስራ በስቃይ ላይ መሆንዋን በማስታወስ በስዊድን የ”ትፈታ!” ትግሉን ለማጠንከር ስቶክሆልም ኤ.ቢ.ኤፍ. አዳራሽ ፌብሩዋሪ 20 ቀን 2010 እ.ኤ.አ. (የካቲት 13 ቀን 2002 ዓ.ም.) ታላቅ ህዝባዊ ስብሰባ ተካሂዷል።

 

ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የዛሬ ዓመት በታህሳስ ወር በአውሮጳ ጉብኝትዋ በተለይ በስዊድን ባደረገችው ንግግር መንግሥት የሰጠሽን ምህረት ክደሽ በምህረት አልወጣሁም ብለሻልና ይህን ቃልሽን አስተባብለሽ መግለጫ ስጪ ትባላለች። ብርቱካን ግን የማስተባበያ መልሷን እንድትሰጥ ከተሰጣት ጊዜ ቀድማ ”ቃሌ” በሚል ርዕስ ከተማረችው የሕግ ሙያ አንፃር የይቅርታ አሰጣጡን አስመልክታ የተናገረችውን እንደማትለውጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ትሰጣለች። ይህ ንግግሯና ድፍረቷ ሞራሉን የነካው የመሰለው እብሪተኛ መንግሥትም በፀጥታ ኃይሎች እያዋከበ ቃሊቲ እስር ቤት ከወረወራት አንድ ዓመት አልፏል።

 

Ato Raswork Mengesha, 2010, 02, 20ስዊድን የሚገኘው የአንድነት ፓርቲ የድጋፍ ማኅበር ባዘጋጀው ስብሰባ ላይ ፕሮግራሙ የተጀመረው አንድ ወጣት ስለ ብርቱካን እንባ እየተናነቀው ባሰማው ግጥምና በአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት ነበር። በመቀጠልም ስብሰባውን የመሩት አቶ ታምራት አዳሙ በኢትዮጵያ ያለው አንባገነናዊ ሥርዓትን ከገለፁ በኋላ ፕሮግራሙን በማስተዋወቅ የስዊድን የድጋፍ ማኅበሩ ሊቀመንበር የመግቢያ ንግግር እንዲያደርጉ ጋበዙ።

 

አቶ ራስወርቅ መንገሻ የስዊድን የድጋፍ ማኅበር ሊቀመንበር ባደረጉት ንግግር በኢትዮጵያ የሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ጭራሽኑ እየታፈኑ እንደመጡና እብሪተኛው መንግሥት ወይዘሪት ብርቱካንን በማሰር የተቀጣጠለውን ህዝባዊ አመፃን ማፈን እንደማይቻልና እንዳውም ትግሉ በነፃነት እልህ እንደሚቀጥል ገልፀው፤ ብርቱካንና መላው የፖለቲካ እስረኞችን የማስፈታት ትግላችን ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

 

ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ዜናዎች ለኢትዮጵያውያን በራዲዮ በማቅረብ ጎበዝ ሚና የሚጫወተው በስዊድን የኢትዮጵያ ራዲዮ ድምፅ አዘጋጅና የኢትዮጵያዊያን ማኅበር ሊቀመንበር አቶ አህመድ ዓሊ በበኩላቸው እንዲህ ሲሉ ንግግር አሰምተዋል። ኒልሰን ማንደላ ታስሮ በነበረበት ወቅት በግንባር ከተሰለፉት ኃይሎች ስዊድኖች የመጀመሪያዎቹ መሆናቸውንና ማንዴላ ከነፃነት በኋላ ስዊድንን ሲጎበኙ መስክረዋል። ይህም የቀድሞውን የስዊድን ጠቅላይ ሚኒስትር ጨምሮ ብዙ ስዊድናውያንን እጅግ እንደኮሩ ገልጠዋል። ዛሬ ለእኛዋ ብርቱካንም የሚደረገው እገዛም ወደፊት ተመሳሳይ ታሪክ እንደሚኖረው ገልፀው፤ መላው የስዊድን የፓርቲና የፓርላመንት ባለሥልጣናት ብርቱካን ሚደቅሳና ሌሎችም የፖለቲካ እስረኞችም እንዲፈቱ ተግባራዊ ግፊት እንዲያደርጉ ጥሪውን አቅርበዋል።

 

ሚስስ ቫኛ ሉንድቢ ቬዲን የአውሮፓ የሠራተኛ ማኅበር ሊቀመንበር በመቀጠልም ንግግር ያደረጉት የአውሮጳ 60 ሚሊዮን ሠራተኞች የሚወክሉትና የአውሮጳ የሠራተኛ ማኅበር ሊቀመንበር የሆኑት ቫኛ ሉንድቢ ቬዲን ናቸው። እሳቸውም የኢትዮጵያንና የስዊድንን የረዥም ጊዜ ግንኙነት ገልፀው፤ ዛሬ በኢትዮጵያ ያለው የሠራተኛ ማኅበር ኮንፌዴሬሽን ራሱ ምንም ነፃነት እንዳሌለውና በሀገሪቱ የሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች በእጅጉ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኙና ይህን ለመለወጥ የትግል አንድነት አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል። አያይዘውም አምነስቲ ኢንተርናሽናል ብርቱካን ሚደቅሳን አስመልክቶ ያወጣውን መግለጫ በእንግሊዝኛ በንባብ ካሰሙ በኋላ፤ በሃሳቡ መቶ በመቶ እንደሚስማሙና ትግላቸውንም እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

 

የተከበሩ ሚስስ ቫኛ ሉንድቢ ቬዲን የአውሮፓ የሠራተኛ ማኅበር ሊቀመንበር በአውሮፓ ሕብረት ውስጥ ከአና ጎሜዝና ከማሪታ ኡልቭስኩግ ጋር በመሆን በኢትዮጵያ ያለውን ኢ-ሰብዓዊ እና ኢ-ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት በማጋለጥ ከኢትዮጵያዊያን ጎን ተሰልፈው ለሠላም፣ ለፍትህና ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲሁም ለብርቱካንና መሰል የፖለቲካ እስረኞች መፈታት በሕብረት እንደሚታገሉ ይጠበቃል።

 

በስዊድን የሚገኙ እናቶችና እህቶች ከዚህ ቀደም ለብርቱካን ቤተሰብ መርጃ የሚሆን የራት ዝግጅት አድርገው የድርሻቸውን መወጣታቸው ይታወሳል። በዚህ ታሪካዊ የ”ብርቱካን ትፈታ” ህዝባዊ ስብሰባ ላይም ሴቶችን በመወከል ወይዘሮ የሺ ወንድሜነህ በኢትዮጵያ ከፍትህ ማጣት የተነሳ የሴቶችን ጣምራ ችግርና መፍትሔውም መልካም አስተዳደር መመስረት መሆኑን ገልፀዋል። ወይዘሮ የሺ ከዚህ ቀደም ካሳተሟቸው መጻሕፍት 20ዎቹ ተሽጠው ገቢው ለብርቱካን ቤተሰብ ገንዘብ ማሰባሰቢያ ምሽት እንዲውል ያደረጉና የወጣት ሴቶችን ትግል የሚያበረታቱ ጠንካራ ኢትዮጵያዊት ናቸው። በዚህ አጋጣሚ ሌሎችም በቂ እውቀትና ልምድ ያላቸው እህቶቻችን እንደ ወይዘሮ የሺ ወንድሜነህ ምሳሌነታቸውን ተግባሪዊ በሆነ አስተዋፅዖ እንዲያሳዩ ብዙ ይጠበቅባቸዋል።

 

በዚህ የብርቱካን እስር አንደኛ ዓመት የትግል መግለጫ /solidarity/ እና የብርቱካን ትፈታ /free Birtukan/ ህዝባዊ ስብሰባ ላይ በጥበብ ሥራቸው በተለያዩ ድረ ገጾች በማራኪና ወለላ ድምፃቸው የሚታወቁት መስከረም አየለ እና ማቲያስ ከተማ ”እሪ አለች ምድሪትዋ” እና ”ብርቱካን ትፈታ!” በሚሉ ርዕሶች የግጥም ዝግጅቶች በማቅረብ ለስብሰባው ታላቅ ክብርና ሞገስ አላብሰውታል። ”እኛም አለን በተጠንቀቅ” የሚሉት የአንድነት ወጣቶችን በመወከልም ወጣት ብርሃኑ እና ወጣት ታጠቅ የብርቱካን ትፈታ አጭር ዝግጅታቸውን በማቅረብ ብሔራዊ ስሜትን ቀስቅሰዋል።

 

በታላቁ የግንቦት 97 ምርጫ የአውሮፓ ታዛቢ ቡድንን በመምራት የኢትዮጵያውያንን የነፃነት ጥማትና የአቶ መለስን መንግሥት ምንነት አበጥረው የሚያውቁት የአውሮፓ ፓርላሜንት አባል ሚስስ አና ጎሜዝ፤ ለሥራ ጉዳይ ከሚገኙበት ሕንድ ሀገር ሆነው ለስብሰባው ያላቸውን በጎ ምኞትና ለወ/ት ብርቱካን መፈታት፣ ከኢትዮጵያውያን የነፃነት ትግልም ጎን እንደሚሰለፉ መልዕክት በመላክ አረጋግጠዋል። በመልክታቸው መጨረሻ ላይ ያሉት አንድ ቁም ነገር አለ፤ ይህም ”አምባገነኖችን በተናጠል ትግል ማሸነፍ አይቻልም፤ ስለዚህ ትግላችሁን በሕብረትና በአንድነት ቀጥሉ!” ነበር ያሉት። በዚሁ ህዝባዊ ስብሰባ ላይ ኒልሰን ማንዴላ በግዞት በነበሩበት ጊዜ ለመስዋዕትነታቸው የተገጠመላቸውን የእንግሊዝኛ ስንኝም አቶ ደጀኔ ኃይሉ በማቅረብ፤ በማንዴላ ተምሳሌት የእኛዋን ብርቱካን እንድናስባት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

 

 

Stockholm 2010, 02, 20 Free Birtukan!
 

 

ዳኛ ብርቱካን ሚደቅሳ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርትዋን አጠናቅቃ ከተመረቀች በኋላ በሙያዋ የሕግ የበላይነትን በሀገሪቷ ለማስከበር ከነበራት ቀና ራዕይ ተነስታ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ በመሆን ሠርታለች። ይሁን እንጂ የገዢው ፓርቲ ሆድ አደር ዳኞችን እየተጠቀመ ወገኖችና ተቃዋሚዎቹን በሚጎዳበት የጥፋት ተግባር ፈፅሞ ባለመስማማቷ የዳኝነት ሥራዋን ለመተው ተገዳለች።

 

ይህ ዛሬ ካለንበት ዘመን አኳያ እጅግ ኋላ ቀርና ጠንቀኛ የሆነ የጎሣ ፖለቲካ አራማጅ መንግሥት በሀገሪቷና በዜጎቹ ላይ የሚፈፅመውን የእኩይ ተግባር ለመቃወምም ከተቃዋሚዎች ጎራ ተሰልፋ በግሏ ፓርላመንታዊ ተወዳዳሪ ሆና ነበር። ሆኖም ከቅድመ ቅንጅት የነበረው ምርጫ ሙሉ በሙሉ በወያኔ እጅ ስለነበር ያሰበችው አልተሳካላትም። በዚህ ጊዜ ነው የቅንጅት መስራች አንድ አካል የነበረውን የቀስተደመና ፓርቲን በመቀላቀል የተናጠል ትግልዋን ወደ ድርጅታዊ ትግል ያሳደገችው።

 

ብርቱካን በነበራት የለውጥ ፈላጊነት ስሜትና በምታቀርባቸውም ሀገራዊ ጉዳዮች /National values/ በወጣቶች ብቻ ሳይሆን ወልደው በሚያደርሷት የዕድሜ ባለፀጋዎችም ሳይቀር ታላቅ ክብርና ተወዳጅነትን እያገኘች መጣች። ለዚህም ነው በአጭር ጊዜ የቅንጅት ምክትል ሊቀመንበር ለመሆን የቻለችው።

 

በኃይል ከተነጠቀው ታላቁ የግንቦት ምርጫ በኋላ ለሁለት ዓመታት ያህል በእስር ቆየች። እንደተፈታችም ቅንጅት በልዩ ልዩ ምክንያቶች በቅንጅትነት ለመቀጠል ያልቻለበት ሁኔታ ተፈጠረ። ብርቱካን ግን ህዝባዊ ዓላማውን አንግባ ከመስል የትግል አጋሮቿ ጋር ”አንድነት ለዲሞክራሲና ፍትህ” ፓርቲን መስርታለች።

 

በሀገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያዋ ሴት የፓርቲ መሪ ሆና በቅንጅት ዓላማና መንፈሥ ”አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ” ፓርቲን በእግሩ አቁማ ህዝባዊ ዓላማውን ለማሳካትም ቆርጣ ተነሳች። ይህን አደገኛ የሚለውን እንቅስቃሴ በስጋት የተመለከተውና ዕረፍት ያጣው የኢህአዲግ መንግሥት ይህችን ወጣት፣ አንስታይ፣ የሕግ ባለሙያና የልጅ እናት በተለጣፊ ሰበብ በድጋሚ አሰራት። አዎ! ብርቱካንን አስሯታል። የብርቱካንን አይበገሬ ኢትዮጵያዊ መንፈሥ ግን ማሰር አይቻልም። እንዳውም እሷን ማሰሩ በወያኔ ዘንድ ዓለም አቀፍ ውግዘትን፣ ለእርስዋ ደግሞ ክብርና ፅናትን አጎናፀፏታል።

 

ብርቱካንን በማሰር ወያኔ የጠበቀው ፖለቲካዊ ትርፍ፤ በአንፃሩ ፖለቲካዊ ኪሳራን አስከትሎበታል። ለዚህም ነው ዛሬ በብርቱካን ዳግማዊ እስር የራሱ የወያኔ አባላት ሳይቀር የተለያየ አስተያየትና አመለካከት ያላቸው። የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ ብርቱካን ያለ አግባብ ታስረው ከሚገኙ በርካታ ዜጎች አንዷ መሆኗን ገልፆ መግለጫ አውጥተዋል። ይህ መግለጫ በራሱ የወያኔ መንግሥት ብርቱካንን በምንም ሳይሆን በፖለቲካ ምክንያት እንዳሰራት ታላቅ ማስረጃ ነው።

 

እንዲሁም በውጭ ያለው የሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ ጩኸት አሰሚ ወገን ሁሉ በያለበት ሀገር በየጊዜው የብርቱካን ትፈታ ጥያቄውን ማስተጋባቱ የብርቱካን ዓላማ አብሯት እንዳልታሰረ ያበስራል። አዎ! ብርቱካን ታስራለች። አንድ ወላድ እናት አዝናለች። የእናት ፍቅር ያጣችው ልጇ ሐሌም ታለቅሳለች። የብርቱካን የነፃነት ራዕይ ግን መጪውን የብርሃን ዘመን እያሳየና የነፃነት ፋና እያበራ ይገኛል። በሰፈሩት ቁና መሰፈር አይቀርምና፤ የብርቱካንና የመላው ኢትዮጵያዊያን የነፃነት ቀንም ሩቅ አይሆንም። እዚህ ላይ አንድ ነገር ልብ ይሏል። ብርቱካን እንድትፈታ የምንታገለው ብርቱካን በእናትነቷ በልጅ አሳዳጊነት እንድትወሰን ብቻ አይደለም፤ እንዳውም ብርቱካን ዛሬ በሀገራችን ከሚታየው የፖለቲካና የፖለቲከኞች መዋዠቅ አንፃር ያላት ቆራጥ አቋምና የመሪነት ብቃት /Leadership quality/ አንፃር ትክክለኛ የሀገር መሪ መሆን የምትችል ዓርማችን በመሆኗ ነው።

 

ብርቱካን ታስራለች ቢባልም፤ ህዝባዊ ዓላማዋ ግን በነፃነት ይንቀሳቀሳል። ይህ ዓላማዋ አሁንም በአንድነት እንታገል፣ በአንድነት ነፃ እንውጣ የሚለውን ብሔራዊ ጥሪ እያስተጋባ ይገኛል።


ስሜነህ ታምራት ከስዊድን

የካቲት 14 ቀን 2002 ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!