Dr. Negasso Gidada ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳየሶሻል ዲሞክራት ፓርቲ ኃላፊዎችንና ኢትዮጵያውያንን አነጋገሩ

Ethiopia Zare (ቅዳሜ መስከረም 8 ቀን 2003 ዓ.ም. September 18, 2010)፦ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት፣ የአሁኑ የመድረክ የውጪ ኮሚቴ አባል፣ የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበርና የውጪ ጉዳይ ኮሚቴ ሰብሳቢ የስዊድን ሾሻል ዲሞክራት ፓርቲ ባደረገላቸው ጥሪ መሰረት ካለፈው ረቡዕ ጳጉሜን 3 ቀን ጀምረው በስቶክሆልም በመገኘት እንቁጣጣሽን ከኢትዮጵያውያን ጋር አብረው አሳለፉ።

 

ዶ/ር ነጋሶ በዚሁ ቆይታቸው ከስዊድን የሶሻል ዲሞክራት ፓርቲ ኃላፊዎች መካከል የወቅቱ የስዊድን እና የአውሮፓ የ60 ሚሊዮን ከሠራተኛች ሊቀመንበር ከሆኑት ከወ/ሮ ቫኛ ሉንድቢ ቬዲን፣ ከዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ማኅበር ሊቀመንበር፣ ከሴቶች ማኅበር ሊቀመንበር እና ከወጣቶች ማኅበር ሊቀመንበር ጋር ተገናኝተው በኢትዮጵያ ስላለው የዲሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ጥያቄ በተለይም ስለ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ጉዳይ ተወያይተዋል።

 

እንዲሁም ቅዳሜ መስከረም 1 ቀን 2003 ዓ.ም. (ሴፕቴምበር 11 ቀን 2010 እ.ኤ.አ) የስዊድን የኢትዮጵያ ድምፅ ራዲዮ የተመሰረተበትን 17ኛ ዓመትና የኢትዮጵያን አዲስ ዓመት በማስመልከት በአደርገው የእንቁጣጣሽ ዝግጅት ላይ የስዊድን የሠራተኞው ማኅበር ፕሬዝዳንት ከሆኑት ከወ/ሮ ቫኛ ሉንድቢ ቬዲን ጋር በክብር እንግድነት ተገኝተዋል።

 

በዚሁ ቀን ዶ/ር ነጋሶ እራሳቸውን ለህዝቡ ያስተዋወቁ ሲሆን፣ ከወ/ሮዋ ጋር በመሆን የቀኑ ዝግጅት መገባደጃ ድረስ ቆይተዋል።

 

ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በማግስቱ እሁድ መስከረም 2 ቀን (ሴፕቴንበር 12) ኢትዮጵያውያንን ለማነጋገር በያዙት ቀጠሮ መሰረት በተያዘላቸው የስብሰባ አዳራሽ ከሰዓት በኋላ 10፡30 ሰዓት (16፡30 ሰዓት) ጀምሮ ተገኝተዋል። ውይይቱም እስከ ምሽቱ 2፡30 ሰዓት (20፡30) ድረስ ተካሂዷል።

 

የውይይቱን መጀመር ያበሰሩት አቶ ታምራት አዳሙ ሲሆኑ፣ በስዊድን የአንድነት ፓርቲ ድጋፍ ማኅበር ሰብሳቢ የሆኑት አቶ የራስወርቅ መንገሻ ደግሞ የመክፈቻ ንግግር አሰምተዋል። በመቀጠልም ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ስለእራሳቸው፣ አሁን አባል ስለሆኑባቸው ፓርቲዎች፣ ስለምርጫ 2002፣ ስለወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ … እንዲሁም በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ንግግር በማድረግ በአዳራሹ ከተገኙ ኢትዮጵያውያን ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።

 

Stockholm, Sept. 12, 2010ዶ/ር ነጋሶ ቀድሞ በስደት ከሚኖሩበት ከጀርመን በ1983 ዓ.ም. መጨረሻ ጀምሮ ወደ ሀገራቸው በመግባት ከተለያየ ሥልጣን አንስቶ እስከ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንትነት ድረስ ሲሠሩ እንደቆዩ ገልጸው፤ አሁንም በመድረክና በአንድነት የፓርቲ አመራር ኃላፊነት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

 

አያይዘውም ስለ ወ/ሪት ብርቱካን ሲያብራሩ ብርቱካን አሁንም የአንድነት ሊቀመንበር እንደሆነች ገልጸው፤ የኢትዮጵያ ህዝብም ለሚያደርገው የነፃነት ትግል በቆራጥነት የቆመች የመጀመሪያዋ ታታሪ ወጣት ሴት መሪና የሠላማዊ የነፃነት ትግል ምልክት ጭምር ናት ብለዋል። ብርቱካን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ትፈታ በማለት ደጋግመን የጠየቅን ሲሆን፣ አሁንም የማስፈታት ትግሉን በተጠናከረ ሁኔታ እንቀጥላለን ሲሉ ገልጸዋል።

 

ምርጫ 2002ን አስመልክተው ሲናገሩ ደግሞ፤ የምርጫው ሂደት የተጀመረው የምርጫ አስፈጻሚዎችን በምርጫ ክልልና ጣቢያ በመደብደብ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ነጋሶ፤ ስለጉዳዩ ሲያብራሩ የተቃዋሚ ፖለቲካ መሪዎችን አሰረ፣ ከህዝብ ጋር እንዳይገናኙ እንቅስቃሴዎችን አገደ፣ ጠንካራ የተባሉት ድርጅቶች እንዲከፋፈሉ ስም በማጥፋትና የመገናኛ ብዙኀንን ለብቻው በመጠቀም አሳሪ ገዳቢና አስፈሪ ሕጎችን አወጀ፣ … በማለት የምርጫውን አጀማመር አስረድተዋል።

 

ምርጫው ከተጀመረ በኋላ ደግሞ የዕጩዎች ምዝገባ አወዛጋቢና ለኢህአዴግ ወገንተኛ በሆነ መንገድ መከናወኑን፤ የመድረክ የምረጡኝ ቅስቀሳ ከፍተኛ ችግር እንዲደርስበት መደረጉን፤ የህዝብ መገናኛ ብዙኀን አጠቃቀም ፍትሃዊ እንዳልነበር፤ በዕጩዎች ተጽዕኖ ማሳደርና እራሳቸውን ከዕጩነት እንዲያገሉ ዘመቻ ማካሄድ፤ የመራጭ ነፃነት አለማክበር፣ ህዝብን ማስፈራራት፤ ኢህአዴግን ካልመረጥክ የሥራ ዕድል፣ የርዳታ እህል፣ … አታገኝም በማለትና በማሸማቀቅ፤ የምርጫ ካርድ አስቀድሞ በማሰራጨትና የተቃዋሚ ወኪሎችን ማስፈራራት፤ … የመሳሰሉት ድርጊቶች ተፈጽመው እንደነበር ገልጸዋል።

 

በተጨማሪ በምርጫው ዕለት የነበረው ሁኔታ እንዴት እንደነበር ሲገልጹ፤ የተቃዋሚ ድርጅት ወኪሎች ወደምርጫ ጣቢያ እንዳይገቡ ተከልክለዋል፣ ተደብድበዋል፣ ከጣቢያ እንዲባረሩ ተደርገዋል፣ ታስረዋል፣ በጥይት ተመትተዋል፣ በጩቤ የተወጉም ሲኖሩ የምርጫ ቦታ ምስጥራዊነትም አልተጠበቀም፤ የምርጫ ታዛቢዎችና የምርጫው አስፈጻሚ ኃላፊዎች የኢህአዴግ አባላት ወይንም ደጋፊዎች ነበሩ፤ ብዙ መራጮች ከአንድ ካርድ በላይ ይዘው ተገኝተውል፤ የመድረክ ካርዶች ተለይተው ተጥለዋል፤ በብዙ ቦታ የተካሄደው ድምፅ ቆጠራ መራጩ ከተመዘገበው በላይ መሆኑ ታይቷል ብለዋል።

 

እነዚህ ሁሉ ጥፋቶችና ወንጀሎች ባሉበት ሁኔታ ኢህአዴግ ምርጫውን በ99.6 አሸንፌአለሁ ብሎ አውጇል። እኛ ግን ምርጫውን እንደ ድራማ ተመልክተነዋል። የዚህ ተውኔት ፀሐፊ፣ አዘጋጅና ተዋናይ እራሱ ኢህአዴግ ነበር በማለት ገልጸዋል።

 

ምርጫውን አስመልክቶ ፓርቲአቸው ስለወሰደው እርምጃም ሲናገሩ፤ ምርጫው ቀላል ሌብነት ሳይሆን ዓይን ባወጣ አይነት ሁኔት የተከናወነ ዝርፊያ እንደነበር በመጥቀስ ለዚሁም በቂ መረጃ በማያያዝ ለምርጫ ቦርድ አመልክተን ምርጫው እንደገና እንዲደገም መጠየቃቸውን ገልፀዋል። ቦርዱ ግን ሕጉን ለማስከበር ፍቃደኛ ሆኖ ስላላገኘነው ፍርድ ቤት በመሄድ ይሄንኑ ጠይቀን እዛም ከቦርዱ የተለየ መልስ ስላላገኘን ወደ ህዝብ ከመሄድ በቀር አማራጭ አላገኘንም ብለዋል።

 

ወደምርጫ መግባታቸው ጠቀሜታ እንደታየበት የገለጹት ዶ/ር ነጋሶ፤ ባንገባ ኖሮ ሜዳውን ሙሉ ለሙሉ ለኢህአዴግ ለቀንለት እንደልቡ መፈንጫ ያደርገው ነበር፤ በመግባታችን የምርጫውን የውሸት ድራማ ለማጋለጥ የቻልንበትን ውጤት አስመዝግቧል ብለዋል።

 

በሌላ በኩልም ሐቀኛ የዲሞክራሲ ኃይሎች በነበረው ሂደት ተስፋ ባለመቁረጥ ለወደፊት ትግል እራሳቸውን የሚያጠናክሩበት ሁኔታ እንደተፈጠረ አመላክተዋል። መድረክም እራሱን ወደ ግንባርነት በመለወጥ ከሌሎች ሐቀኛ የዲሞክራሲ ኃይሎች ጋር ተባብሮ ለመሥራት እንቅስቃሴ መጀመሩን አስረድተዋል።

 

በአሁኑ ጊዜ ኢህአዴግ የተቃዋሚ ተቃዋሚ የሆኑ ድርጅቶችን በግንባር እንዲደራጁ እያሰናዳ ከተቃዋሚዎች ጋር ድርድር እንፈልጋለን ማለቱ ድርድሩን ፈልጎት ሳይሆን ለዕኩይ ተግባር እየተሰናዳ ለማስመሰያ የፈጠረው አካሄድ እንደሆነ ድርጊቱ ያስረዳል ብለዋል።

 

ሆኖም ኢህአዴግ ለድርድር የተዘጋጀና እውነተኛ ፈቃደኝነት ካለው መድረክ በቅርቡ ያውጣውን መግለጫ በመከተል መደራደር እንደሚቻል ገልጸው፤ መግለጫውን ለተሰብሳቢው አንብበዋል። (የመግለጫው ሙሉ ቃል ለማንበብ እዚህ ይጫኑ!)

 

በመቀጠልም የጥያቄና መልስ ፕሮግራም ተጀምሮ፤ ከተሰብሳቢዎች በርካታ ጥያቄዎች ቀርበዋል። ከጥያቄና መልሶቹ መካከል እጅግ ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው።

 

“ወደምርጫ በመግባታችን ኢህአዴግን ለማጋለጥ ችለናል ስትሉ ህዝቡ በፊትስ ኢህአዴግን ያውቀው የለም ወይ? ምኑን ነው የምታጋልጡት?” ተብለው ለተጠየቁት ዶ/ር ነጋሶ ሲመልሱ፤ አዎን ኢህአዴግን ህዝቡ በደንብ ያውቀዋል፤ ነገር ግን እኛን የጥፋት ኃይሎች ከሚላቸው ጋር መድቦን ስለነበርና በተለይም የውጪ መንግሥታት እንድንደራደር ስለጠየቁን ድርድሩ እኛ በምንነድፈው ሰነድ ካልሆነ በቀር ውጤት እንደማያመጣ ገልጸን፤ የሚመጣውንም አስቀድመን አስረድተናቸው ስለነበር፤ ይህንን ሁኔታ በኛ ምርጫ መግባት በግልጽ ልናሳያቸው ችለናል ብለዋል።

 

“የወ/ት ብርቱካንን እስር በመቃውም ሰልፍ ስትወጡ ብዙ የሰው ኃይል ማሳየት ሲገባ ከሦስት መቶ መብለጥ የለብንም ብላችሁ እርሳችሁ ብቻ የወጣችሁት ለምንድነው? ህዝቡስ ይጎዳል ስትሉ ምን ማለታችሁ ነው?” ለተባለው ደግሞ፤ ብርቱካን ስትታሰር የወጣውን ሦስት መቶ ሰው ኢህአዴግ ወስኖ አልሰጠንም ሕጉም የሚያዘው ማስፈቀድ ብቻ ነው፤ ሆኖም ችግር እንዳይመጣ በማሰብና የ97ቱ አሰቃቂ እርምጃ ከህዝቡ አዕምሮ ስላልወጣ ብቻችንን ልንሰለፍ ችለናል ብለዋል።

 

“አሁን በውህደትና በመቀላቀል ጥያቄ ላይ ናችሁ። ስትቀላቀሉ የብርቱካን ጉዳይ እንዴት ይሆናል?” የሚል ጥያቄም ተነስቶላቸው ነበር። ዶ/ር ነጋሶ ለዚህ ጥያቄ፤ “የምንዋሃድም ቢሆን ብርቱካን የኛ መሪ እንድትሆን እንፈልጋለን፤ ብርቱካን ምንግዜም የሠላማዊ ትግል ምሳሌ ናት። ነገር ግን ይሄንን ጥያቄ አሁን የምንመልሰው አይሆንም” በማለት መልስ ሰጥተዋል።

 

ለቀረቡላቸው በርካታ ጥያቄዎች መልስ ሰጥተው ካበቁ በኋላ፤ ለወ/ት ብርቱካን መፈታት ጥረት ያደረጉትንና እያደረጉ ያሉትን፣ እሳቸውንም ጉብኝት እንዲያደርጉ የጋበዟቸውን የስዊድን ሶሻል ዲሞክራት ኃላፊዎችን እና ኢትዮጵያውያኑንም አመስግነው ውይይቱ ተጠናቅቋል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!