ጽዮን ግርማ (የአዲስ አድማስ ጋዜጣ አዘጋጅ)

W/t Birtukanየአዲስ አድማስ ጋዜጣ አዘጋጅ የሆነችው ጋዜጠኛ ጽዮን ግርማ የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ከእስር በተፈታችበት ዕለት ከቃሊቲ እስር ቤት ጀምሮ ፈረንሣይ በሚገኘው መኖሪያ ቤትዋ ድረስ የነበረውን ትዕይነት በዚህ ሪፖርቷ ታስቃኘናለች። የአንድነት አመራሮች (እነ ኢ/ር ግዛቸው) እንዲሁም የመርኅ ይከበር አባላት (እነ ፕ/ር መስፍን) በወ/ት ብርቱካን ቤት መገናኘትን፣ የፖለቲከኞቹን አስተያየት፣ የህዝቡንና የአካባቢውን ሰዎች አስተያየት ታስነብበናለች። ወ/ት ብርቱካን ለጠ/ሚ መለስ ዜናዊ የፃፈችውን ደብዳቤ፣ የመንግሥት መገናኛ ብዙኀኑን ዘገባ፣ በተለይም በሰነዱ አንደምታ ላይ እና በ”ይቅርታው” ጉዳይ ላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፍልስፍና እና የኢንስቲትዩት ኦፍ ሂዩማን ራይት መምህር የሆኑት ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋን አናግራለች። ዶ/ር ዳኛቸው ሰነዱን ከአራት ነጥቦች አንጻር በመመዘን ሰፋ ያለ ትንታኔ ሰጥተዋል። ይህንን ሰፋ ያለ ሪፖርታዥ ታነቡ ዘንድ እንጋብዛለን! … መልካም ንባብ!

የአንድነት ለዴሞክራሲ እና ለፍትሕ ፓርቲ ሊቀመንበር ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ከታሰረችበት ጊዜ ጀምሮ ባሉት የኢትዮጵያውያን ታላላቅ በዓላት ፈረንሳይ ለጋሲዮን በሚገኘው መኖሪያ ቤቷ ስልክ ሳይደወል አይውልም - “ብርቱካን ተፈታች የሚል ወሬ ሰምቼ ነው” የሚል። “ልጅዎ ትፈታለች” የሚለውን ወሬ በተደጋጋሚ ከመስማት ውጪ አዲስ ነገር ጠብ ያላለላቸው እናቷ ወ/ሮ አልማዝ እና ቤተሰቦቿ በዚህ ጥያቄ ተሰላችተው ሰንብተዋል።

 

የልጃቸው የእስር ጊዜ እየተራዘመ መምጣቱ ደግሞ የበለጠ አስጨንቋቸዋል። ከጥቂት ወራት በፊት የተባበሩት የሀገር ሽማግሌዎች በፕሮፌሠር ኤፍሬም ይስሐቅ እና በፓስተር ዳንኤል በኩል እንቅስቃሴ ስለመጀመራቸውን ሹክ መባላቸው በ2003 ዓ.ም. አዲስ ዓመት መግቢያ ላይ ትፈታለች የሚል አዲስ ተስፋን ፈጥሮባቸው ነበር። ነገር ግን ያሰቡት አልሆነም። ልጃቸው ባለመለቀቋም መሪር ሐዘን ወደ ውስጣቸው ገብቶ እንደነበር በቅርብ የሚያውቋቸው እና ሁኔታውን ሲከታተሉ የነበሩ ይናገራሉ።

 

ምንጮች እንደሚሉት ወ/ት ብርቱካን መስከረም 5 ቀን 2003 ዓ.ም. የይቅርታ መጠየቂያ ደብዳቤውን መፈረሟን ከሰሙ በኋላ ተስፋቸው እንደገና ታድሶ ነበር። ከሰኞ መስከረም 24 ቀን ጀምሮም መላ ቤተሰቡ ወ/ሪት ብርቱካንን በጉጉት መጠበቅ ጀመረ። በማግስቱ ማክሰኞ ጠዋት እንደምትፈታ በርግጠኝነት ሲጠባበቁ ቢቆዩም የሀገር ሽማግሌዎቹ ረቡዕ ጠዋት እንደምትፈታ አስረግጠው በመናገራቸው በወ/ት ብርቱካን ቤት የአቀባበል ዝግጅት ተጀመረ።

 

የአዲስ አድማስ ዘጋቢዎች ረቡዕ መስከረም 26 ቀን 2003 ዓ.ም. ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት አካባቢ በወ/ት ብርቱካን ቤት ሲደርሱ፤ በቤቱ በረንዳ ላይ በዲጂታል አርት የተሠራ እና ”እንኳን ለቤትሽ አበቃሽ!” የሚል ጽሑፍ የታተመበት ትልቅ ፖስተር ተለጥፏል። ግቢው በአረጓዴ፤ ቢጫ ቀይ ባንዲራ አሸብርቋል። ከግቢው ውጭ ግን አሥር ከማይሞሉ የአካባቢው ወጣቶች በስተቀር ምንም ሰው አልነበረም።

 

በእንዲህ ዐይነት ሁኔታ እስከ አራት ሰዓት ድረስ ከዘለቀ በኋላ፤ አምስት ሰዓት ላይ ከእስር ቤት ስለምትወጣ ቤተሰቦቿ ቃሊቲ ወደሚገኘው ማረሚያ ቤት ተገኝተው ልጃቸውን እንዲረከቡ የሚል መልዕክት ከሀገር ሽማግሌዎቹ በስልክ መጣ። የስልክ መልዕክቱ ቤተሰቦቿ ማረሚያ ቤት አካባቢ እንዲደርሱ ምልክት ሲሰጣቸው፤ ወደ ማረሚያ ቤት ግቢ እንዲገቡ የሚል ነበር። እናም እናቷ ወ/ሮ አልማዝ፣ ልጇ ሃሌ፣ ወንድሟ አየለ እና እኅቷ ኢየሩሳሌም ከቀኑ አምስት ሰዓት አካባቢ በማረሚያ ቤቱ በር ላይ ደረሱ።

 

ማረሚያ ቤቱ አካባቢም ፕሮፌሠር መስፍን ወ/ማርያም፣ ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም፣ ከአንድነት ፓርቲ የታገዱት ጥቂት አባላት እና ጋዜጠኞች ቀድመው ደርሰው ነበር። የወ/ሪት ብርቱካን እናት ቃሊቲ ደርሰው ለእነዚህ ሰዎች ሠላምታ እያቀረቡ ባሉበት ፍጥነት ወደ ግቢው እንዲገቡ ስልክ ተደወለላቸው።

 

ቤተሰቡን የያዘችው መኪና በጥድፊያ ወደ እስር ቤቱ ግቢ ዘለቀች። ከ20 ደቂቃዎች ቆይታ በኋላ መኪናዋ በቤተሰቡ ላይ ወ/ት ብርቱካንን ጨምራ ወደ መውጫው በር ተጠጋች፤ ከውጭ የቆመው ሰውም ወደ በሩ መቅረብ ጀመረ። ጥቂት ቆይቶ በሩ ተዘጋ እና ወ/ሪት ብርቱካንን የያዘችው መኪና እዚያው ቆየች። እሷን ጨምሮ ቤተሰቡ ከመኪናው እንዲወርድ ተደረገ። የማረሚያ ቤቱ ፖሊሶች ደግሞ በር ላይ የተሰበሰበውን ሰው ከአካባቢው አባረሩ። ጥቂት ቆይቶ አንዲት ነጭ ሚኒባስ ከማረሚያ ቤቱ ግቢ በፍጥነት ወጥታ መንገዱን ያዘች። በመኪናዋ ውስጥ ወ/ት ብርቱካን መኖሯን ያወቁ ወዳጆቿ ስሟን ጠርተው ከፍተኛ ጩኸት አሰሙ። ሚኒባሷ ጉዞዋን ወደ ፈረንሳይ ተያያዘችው።

 

ከ30 ደቂቃ ጉዞ በኋላ ወደ ፈረንሳይ ስንመለስ ሁኔታው ከሰዓታት በፊት ከነበረው ተቀይሮ ጠበቀን። ከዋናው አስፋልት የመኪና መንገድ ወደ መኖሪያ ቤቱ መግቢያ በሚያስጀምረው ኮረኮንች መንገድ ቄጠማ ተጎዝጉዞበታል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በበዓላት ወቅት የሚሰቀሉት አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ባንዲራ አንድ ኪሎ ሜትር በሚሆነው መንገድ ላይ ተሰቅሏል። በዓይን ግምት ከአንድ ሺሕ ያላነሰ ሰው የሚሆን የአካባቢው ሕዝብ እየዘመረ፣ እየጨፈረ፣ ጧፍ እያበራ ከፍተኛ አቀባበል አደረገላት። ወጣቶቹ ከመኪናው ወርዳ አጅበዋት በእግሯ እንድትገባ ጥያቄ ቢያቀርቡም የማረሚያ ቤቱ ሰዎች ፈቃደኛ ባለመሆናቸው መኪናው በሰዎች ታጅቦ ወደ ውስጥ ጉዞውን ቀጠለ። ለቤቱ መዳረሻ 100 ሜትር ያህል ሲቀር ግን ወ/ሪት ብርቱካን ከመኪናው ወርዳ በእግሯ እየሄደች ሊያጅቧት የፈለጉቱ፣ ”ቀይ ምንጣፍ አንጥፈንላታልና በሱ ላይ ነው የምናስገባት” በሚለው አቋማቸው ጸኑ። መኪናው ለጥቂት ደቂቃዎች ከቆመ በኋላ አማራጭ ስላልነበረው ከመኪና እንድትወርድ ተደረገ።

 

ወ/ሪት ብርቱካን በአካባቢው ነዋሪዎች ታጅባ እየተጨፈረ ወደ መኖሪያ ቤቷ ገባች። ግቢው የቻለውን ያህል ሰው ወደ ውስጥ እንዲገባ ከተደረገ በኋላ ከፍ ባለው በረንዳ ላይ ቆማ፤ ”እኔ ንግግር ረስቻለሁ፤ ምን እንደምላችሁ አላውቅም። የእናንተ ድጋፍ እና ሞራል እኔንም ቤተሰቤንም ጠብቆ እዚህ አድርሶናልና ስላደረጋችሁልኝ ሁሉ አመሰግናለሁ፤” በማለት ወደ ውስጥ ዘለቀች። ከፍተኛ ደስታ እና በእንኳን ደስ ያለሽ ሠላምታ የሚጠመጠምባትን ሰው ማስተናገድ ያዘች። ከውጭ እየተንደረደሩ መጥተው ጉልበቷን የሚስሙትን ቀና እያደረገች የሚያለቅሱትን እያጽናናች ሠላምታዋን ቀጠለች።

 

 

በወቅቱ ለነበሩ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጋዜጠኞችም፤ ”ከእስር ተፈትቼ ከእናቴ፣ ከልጄ እና ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በመቀላቀሌ በጣም ደስ ብሎኛል፤ ተጨማሪ ዝርዝር ነገሮችን በሚመለከት ጊዜ ስለሚኖረን ወደፊት እንነጋገራለን፤” በማለት ምላሿን አጠናቀቀች።

 

በልጃቸው መፈታት የደስታ ሲቃ የያዛቸው የወ/ት ብርቱካን እናት ወ/ሮ አልማዝ ገ/እግዚአብሔር፤ ”ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል፤ እሷም እኛም ከእስር ወጥተናል፤ እግዚአብሔርን፣ የኢትዮጵያ ሕዝብን፣ መንግሥትን፣ የሀገር ሽማግሌዎቹን ከልጅ እስከ ዐዋቂው ሁሉንም የኢትዮጵያ ሕዝብ በጣም አመሰግናለሁ፤” በማለት ምስጋናቸውን ገልፀዋል።

 

ልጇ ሃሌ ከእናቷ ጋራ ወደ ቤት ስትገባ የተመለከተችው ግርግር አስጨንቋት ይሁን ወይም እናቷን በማግኘቷ ደስታን ፈጥሮባት ብቻ በማይታወቅ ምክንያት በጩኸት አለቀሰች። ከተረጋጋች በኋላም፣ ”እናትሽ በመፈታቷ ምን ተሰማሽ?” አልናት ”Free” አለች። ምን ማለት እንደሆነ ጠየቅናት፣ ”በቃ እኔም ከቃሊቲ ሙቀትና አቧራ ተገላገልኩ። እሷም ተገላገለች ... እ ... ደሞ ከዚህ በኋላ ቅዳሜና እሁድ ቃሊቲ ሳይሆን ቦራ (የሕፃናት መጫወቻ ቦታ) እሄዳለሁ፤” በማለት የእናቷ መፈታት ለእሷ የሰጣትን ትርጉም አጫወተችን።

 

መስፍን አረጋ ይባላል፤ በወ/ት ብርቱካን መፈታት ደስታውን ለመግለጽ በአካባቢው የተገኘ ወጣት ነው፤ “ወ/ት ብርቱካንን ለሰፈራችን የጀግና ምሳሌ አድርገን ነው የምንመለከታት በመታሰሯ በጣም አዝኜ ነበር በመፈታቷ ደግሞ ተደስቻለሁ፤ እስካሁን የጥንካሬ ምሳሌ ኾናልናለች፤ ወደፊትም ትሆነናለች፤ እስከ አሁን የቻለችውን ሁሉ አድርጋለች። ትግሏን የሚያግዝ እና የሚቀበል ያስፈልጋል፤ ደስታዬ ግን ወደር የለውም፤” ብሎናል።

 

የወ/ት ብርቱካን አቀባበል የተለየ እንዲሆን ያስተባበሩትን ወጣቶች፤ ላደረጉት ደማቅ አቀባበል ምን እንዳነሣሣቸው ጠየቅናቸው፤ ”እኛ የዚህ አካባቢ ነዋሪዎች በወ/ት ብርቱካን ምክንያት ፖለቲካውን ዐውቀናል፤ የመንግሥት ሥርዓት ምን እንደሚመስልም ተመልክተናል፤ እሷና የእሷ ቤተሰብ በዚህ ሥርዓት በተደጋጋሚ የደረሰባቸውን በደል ተገንዝበናል፤ በዚህ ሁሉ ችግር ውስጥ የተማረች ሴት፣ በሞያዋ ሠርታ መኖር የምትችል ሴት ሆና እናቷን እና ልጇን ጥላ ለወራት እስር ቤት በእንቢተኝነት መቆየቷ ከተገነዘብነው ለሌሎቻችን ጥንካሬን የሚሰጥ ነው። ስለዚህ ከሚገባት በጣም ያነሰውን ነው ያደረግንላት፤” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ጧፍ እያበሩ በእልልታ የተቀበሏት አዛውንት እናቶች በበኩላቸው፣ ”ልጃችን ቤቷ ስለገባች በጣም ተደስተናል፤” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

 

የአመራሮቹ ግጥምጥሞሽ

ፕሮፌሠር መስፍንን ጨምሮ ከአንድነት ፓርቲ የታገዱት ”የመርኅ ይከበር” ጥቂት አባላት ከቃሊቲ ጀምሮ አቀባበል በማድረግ በመኖሪያ ቤቷ ተገኝተዋል። ወደ ቤት ከገባች ከቆይታ በኋላ ደግሞ ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው፣ አቶ ስየ አብርሃ፣ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ እና ሌሎች የአንድነት ፓርቲ አመራር አባላት እና የጽ/ቤት ሠራተኞች እቅፍ አበባ ይዘው ወደ ወ/ት ብርቱካን ቤት በማምራት ላይ ነበሩ። ”የመርኅ ይከበር” አባላቱ ከቤት ሲወጡ እና የአንድነት አመራሮች ወደ ውስጥ ሲገቡ መንገድ ላይ ተገናኙ። በሞቀ የእንኳን ደስ ያለን ስሜትም ሠላምታ ተለዋወጡ። ይህን የተመለከቱ አንዳንዶች፣ ”ምናልባት የወ/ት ብርቱካን ከእስር መፈታት ሁለቱን ወገኖች አንድ ለማድረግ ዕድል ይፈጥር ይሆን?” ሲሉም መጠየቅ ጀመሩ።

 

በወቅቱ ጥያቄ ፕሮፌሠር መስፍን፤ ወ/ሪት ብርቱካን ከእስር በመፈታቷ የተሰማቸውን ደስታ ከገለጹ በኋላ፣ ”በፓርቲው ውስጥ የተፈጠረው ችግር ወ/ሪት ብርቱካን ከመፈታቷ በፊት እንዲቃለል ጥረት ለማድረግ ሞክረን ነበር። እርሷ ከችግር ወጥታ ወደ ችግር እንዳትገባ ነገሮችን ወደነበሩበት ለመመለስ ኃላፊነት ወስደን ነበር፤ ነገር ግን እነሱ ወደ ዐምባገነንነት መንገድ በመሄዳቸው ልንጨርሰው አልቻልንም። አሁንም ይኸው ፍላጎት አለን። ነገር ግን በአሁኑ ሰዓት እኛ የምናስበው ለእርሷ ነው። ይህን በሚመለከትም አንድም ነገር አላነሣንባትም። ዕረፍት ማድረግ አለባት፤” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

 

ኢ/ር ግዛቸው በበኩላቸው፤ ”እኛ ቀደም ሲልም ቢሆን ግንኙነት አላቋረጥንም። እኔ ለምሳሌ ከጥቂት ቀናት በፊት ፕሮፌሠር መስፍን ቤት ሄጄ ነበር። በመካከላችን የሐሳብ ልዩነት ተፈጥሯል ማለት እኛ ተለያይተናል ማለት አይደለም፤ ችግሩን ለመፍታትም በግለሰቦች እና በቡድኖች ደረጃ ለመነጋገር ሞክረን ነበር። ነገር ግን ውሳኔው የምክር ቤቱ በመሆኑ ጉዳዩን ተቋማዊ አድርጎ ለመነጋገር በሕጉ እና በደንቡ መሠረት የምናየው ይመስለኛል። ወ/ት ብርቱካን በመፈታቷ ለውጥ ይመጣል ወይ? የሚለውን በሚመለከት የወደፊቱን ሁኔታ ለመተንበይ እቸገራለሁ። ነገር ግን በጎ ሂደት እና በጎ ተግባር እንደሚኖር ይታየኛል” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

 

ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በተፈታች ማግስት ከሰዓት በኋላ በፓርቲው ጽ/ቤት ተገኝታ ከአመራሮቹ ጋራ ተወያይታለች። በዚህም ወቅት የፓርቲው ም/ሊቀመንበር እና የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው ፓርቲው ያለበትን ሁኔታ በሚመለከት አጠቃላይ ሪፖርት እንዳቀረቡላት ታውቋል። በዚሁ ዕለት ማምሻውን ከፕሮፌሠር መስፍን ወ/ማርያም ጋራ መገናኘቷን የገለጹት ምንጮች፤ ለሁለቱም ወገኖች ለጥቂት ጊዜ ዕረፍት እንደሚያስፈልጋት በመግለጽ እንደተሰናበተቻቸው ታውቋል። በዛሬው ዕለትም (ቅዳሜ መስከረም 29 ቀን 2003 ዓ.ም) ለአንድ ሳምንት ዕረፍት ከቤተሰቦቿ ጋራ ከአዲስ አበባ ከተማ ውጭ እንደምትሄድ ታውቋል።

 

የሰነዱ አንድምታ

ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ከዳኝነት ወደ ጥብቅና ሞያ ከዚያም፤ በ1992 ዓ.ም. በግል የፓርላማ ተወዳዳሪ በመሆን የኢትዮጵያን ፖለቲካ የተቀላቀለች ወጣት ፖለቲከኛ ናት። በ1997 ዓ.ም. ለቅንጅት ለአንድነት እና ለዴሞክራሲ የሕግ አገልግሎት ድጋፍ ለመስጠት፣ በኋላም ቀስተ ደመና የተባለውን ፓርቲ መቀላቀሏ ይታወሳል። በሂደትም የፓርቲው ተ/ም ሊቀመንበር በመሆን ለጥቂት ወራት ካገለገለች በኋላ ከምርጫ 97 የሕዝብ መነሣሣት ጋራ ተያይዞ ወደ እስር ቤት አምርታለች። ከእስር በይቅርታ ከወጣች ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ ውጭ ሀገር ባደረገችው ንግግር ምክንያት ታኅሣሥ 20 ቀን 2001 ዓ.ም. በድጋሚ ለአንድ ዓመት ከዘጠኝ ወር በእስር ቆይታ መስከረም 26 ቀን 2003 ዓ.ም. በድጋሚ ይቅርታ ተለቃለች።

 

ወ/ት ብርቱካን ከእስር የተለቀቀችው ይቅርታ ጠይቃ መሆኑን የገለጸች ሲሆን፤ በኮምፒዩተር የተጻፈውን የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የይቅርታ ደብዳቤና እሷ የሰጠችው የደብዳቤው ማረጋገጫ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ተላልፏል።

 

የደብዳቤውም ይዘት፤

”ለክቡር አቶ መለስ ዜናዊ

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር

አዲስ አበባ

”አመልካች እኔ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ለክብርነትዎ የማመለክተው ጉዳይ እንደሚከተለው ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ ከምርጫ 97 ዓ.ም. ጋር ተያይዞ ሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ ተንቀሳቅሳችኋል የሚል ክስ በፍ/ቤት ተመስርቶብን ለበርካታ ወራት ከተከራከርን በኋላ ጥፋታችን በማስረጃ ተረጋግጦ በወንጀለኝነት የዕድሜ ልክ እሥራት ተፈርዶብን ነበር።

 

ይሁንና እኔና የቅንጅት ፍርደኛ ባልደረቦቼ ከፍርዱ በኋላ በጋራና በየግላችን የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ጉዳዩን በሆደ ሰፊነት ተመልክተው ይቅርታ እንዲያደርጉልን እኛ ዳግም በሌላ ጥፋት ላይ ላለመገኘት ባቀረብነው ጥያቄና በገባነው ቃል መሰረት በቅድመ ሁኔታ ላይ የተመሰረተ ይቅርታ ተሰጥቶን በነፃነት መንቀሳቀስ ችለን ነበር።

 

ይሁንና ለሥራ ጉዳይ ወደ ውጭ ሀገር በሄድኩበት ወቅት በበኩሌ ያቀረብኩት የይቅርታ ጥያቄ እንደሌለና መንግሥት ይቅርታውን ሳልጠይቅ እንደሰጠኝ በማስመሰል ለደጋፊዎቼ የተሳሳተና በክህደት ላይ የተመሰረተ መረጃ ሰጥቼ ነበር። ይህንኑ ምክንያት በማድረግ ወደ አገሬ ስመለስ መንግሥት ጠርቶ በድጋሚ የፈፀምኩትን ስህተት እንዳርም ተደጋጋሚ ምክር ቢለግሰኝም ይህንኑ ባለመቀበል እንደገና ሌላ ስህተት ልፈጽም ችያለሁ። ወደዚያ ስህተት ልገባ የቻልኩት መንግሥት የውጭ ኃይሎችን ተፅዕኖ በመፍራት ሊያስረኝ አይችልም፣ ካሰረኝም ተገዶ በአጭር ጊዜ ይፈታኛል በሚል የተሳሳተ ግንዛቤ ነው።

 

የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር

የተሰጠኝን ምህረት በመካድ የኢትዮጵያን ህዝብና መንግሥትን በማታለሌ ከፍተኛ ፀፀት ተሰምቶኛል። ዳግም በእንዲህ ያለ የማታለል ሥራ እንደማልሳተፍ በማረጋገጥ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥትን ይቅርታ እጠይቃለሁ።

 

በማረሚያ ቤት ቆይታዬ በቂ ትምህርት ስለቀሰምኩ ፀፀቱን አይተው ህፃንዋን ልጄንና አሮጊት እናቴን እንድጦር፣ እንደዚሁም ከቤተሰቦቼ ጋር እንድቀላል ዳግም ምህረት ይሰጠኝ ዘንድ በታላቅ ጉጉት እጠይቃሁ።” የሚል ነው።

 

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፍልስፍና እና የኢንስቲትዩት ኦፍ ሂዩማን ራይት መምህር የሆኑት ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ፣ ይህን ሰነድን ከአራት ነጥቦች አንጻር በመመዘን ትንታኔያቸውን ያስቀምጣሉ። የመጀመሪያ ነጥባቸው፣ ሰነዱን ከሕግ አኳያ መገምገም ነው፤ ”ከሕግ አኳያ የቀረበው ሰነድ በየትኛውም ዴሞክራሲያዊ ናቸው በሚባሉት አገሮች ከሕጋዊነት አግባብነት አንጻር ተቀባይነት አይኖረውም። አንድ እስረኛ ከአንድ ዓመት ከዘጠኝ ወር በላይ የሕግ የምክር አገልግሎት ተከልክሎ፣ ምንም ዐይነት የሕግ ምክር ከጠበቃ ጋራ ሳያደርግ መጨረሻ ላይ እንዲህ ብሎ ፈርሟል የሚለው ፍርድ ቤት ቢቀርብ ዳኛው በመጀመሪያ የሚያቀርበው ጥያቄ፤ ይህን ጽሑፍ ስትጽፍ የሕግ የምክር አገልግሎት አግኝተህ ነበር ወይ? የሚል ነው። ከዚህ አንፃር ለብቻዋ የታሰረች፣ ሁለት ጠበቆቿ እንዳያገኟት የተከለከለች ልጅ በመጨረሻ ይህን ሰነድ ፈርማለች ተብሎ ቢቀርብ በአሜሪካም ሆነ በአውሮፓ ሰነዱ ሕጋዊ ተቀባይነት የለውም። በሕግ ፊትም በእግሩ መሬት ረግጦ መቆም የሚችል ሰነድ አይደለም፤” በማለት ሕጋዊ አግባብነቱን በዓለም አቀፍ ደረጃ መዝነው ያጣጥሉታል።

 

ዶ/ር ዳኛቸው የሰነዱን አግባብነት የገመገሙበት ሁለተኛው ነጥብ የሀገርን የይቅርታ ወግ እና ልማድ መሠረት ያደረገ ነው። ”በዐፄ ኃይለሥላሴ ጊዜ የነበረውን የቅርብ የኢትዮጵያ የይቅርታ ታሪክ ወደ ኋላ መለስ ብሎ ማየት ያስፈልጋል። በዐፄው ጊዜ ይቅርታ የጠየቁ ሰዎች እንዴት ነው የተስተናገዱት? ብሎ መመርመር ያስፈልጋል። ከዚህ አኳያ ከራስ ጌታቸው እስከ ጄነራል ታደሰ ብሩ እና አሁን በሕይወት ያሉት እነ ታምራት ከበደ ያስገቧቸውን ሰነዶች አይቻለሁ። በምንም መልኩ ከጽሕፈት ሚኒስቴር ዐፄ ኃይለሥላሴ ልከውላቸው የፈረሟቸው ሰነዶች አይደሉም። በርግጥ ይቅርታውን ጠይቀዋል፤ ይቅርታም ተሰጥቷቸዋል። ያቀረቡት ይቅርታ ግን ተሳስተናል፤ ይቅርታ እንዲያደርጉልን ዙፋኖ ሥር ወድቀናል በሚል በጥቅሉ የቀረበ እንጂ፤ በዚህ ቦታ እንዲህ አድርገናል፤ በዚህ ቦታ እንዲህ ብለናል በሚል የእነሱን ሰብዕና እና ማንነት በሚያዋርድ መልኩ የተዘጋጀ አይደለም፤” በማለት ወ/ሪት ብርቱካን የፈረመችው ሰነድ ከቆየው የሀገር የይቅርታ ወግ እና ልማድ ጋራ ተቃርኖ ያለው መሆኑን በምሳሌ ያስረዳሉ።

 

በሦስተኛነት ሰነዱ የሚሰጠውን ፖለቲካዊ ትርጉም ይፈትሻሉ፤ “የሰነዱን ፖለቲካዊ ይዘት መዝነው ለእኔ እንደሚገባኝ ሁለት መልዕክት ነው ያለው። በተለይ መንግሥት ለሁለት ዓመት ሲያቀርበው የነበረው ክርክር፣ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ያሻኝን ብናገር ምንም አልሆንም፤ ምክንያቱም እኔ ጠንካራ የውጭ ደጋፊዎች ስላሉኝ” ብላለች እያሉ ነው ጠ/ሚኒስትሩን ጨምሮ ሌሎች ባለሥልጣናትም ደጋግመው ሲነግሩን ነበር።

 

እዚህ ሰነድ ላይ ይሄ የእነሱ ንግግር መካተቱ በጣም የሚገርም ነገር ነው። ከታሰረች ጀምሮ ሲያቀርቡት የነበረው ክስ እና የእነሱ ትንታኔ በእርሷ አፍ ውስጥ ተጨምሮ የቀረበ ሰነድ ነው። የታሪክ ምሳሌ ብናጣቅስ ልጅ ኢያሱ ሰልመዋል ተብለው ነው የተከሰሱት፤ ከትግራይ በረሃ በሰንሰለት ታስረው ተይዘው ሲመጡ፣ “በል እንግዲህ አሁን መስለምህን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ንገር” ብሎ ጫና የፈጠረባቸው ሰው የለም። ይኼኛው ሰነድ ግን በወ/ሪት ብርቱካን ላይ ብርቱ ጫና የተፈጠረበትን ሁኔታ ያሳየናል። ወ/ሪት ብርቱካን ይቅርታውን ጻፊ ቢሏት በራሷ አንደበት እና ቋንቋ ትጽፈዋለች፤ ነገር ግን በባለሥልጣናቱ ሲነገረን የቆየው በሰነዱ ላይ መካተቱ እነሱ የደረሱበትን ደረጃ በውል የሚያሳይ መልዕክት ነው ያለው። …

 

ሁለተኛውን የሰነዱን ፖለቲካዊ መልዕክት ሲያስረዱም፤ “ይሄ ሰነድ ያለፈውን ብቻ ሳይሆን ወደፊት መሆን ያለበትን የሚጠቁም ነው። ይኸውም በወ/ሪት ብርቱካን ስም ይኼ ለዜጎች የተላለፈ መልዕክት አለ፤ ”አርፌ አሮጊት እናቴን እጦራለሁ፤ ልጄን አሳድጋለሁ” የሚለውን ወ/ሪት ብርቱካን እንዲህ ካለች ሌላ ጥያቄ ያላችሁ ዜጎችም ይህን መንገድ ብትከተሉ ይሻላችኋል የሚል ለዜጎች የተላከ መልዕክት ነው። በጣም የሚገርመኝ “እናትን የመጦር” ጥያቄ አለ። እነሱ በረሃ ክላሽ ይዘው ሲገቡ እናት አልነበራቸውም? እና አሁን ለእኛ ነው ”ዐርፈህ እናትህን ጡር፣ ልጅህን አሳድግ” የሚለው የሚነገረን? ይህ ከወ/ሪት ብርቱካን ጀርባ ለእኛ ለዜጎች የተሰጠ መልዕክት መኖሩን የሚያሳይ ነው፤ … በማለት ትንታኔያቸውን ይቀጥላሉ።

 

የፍልስፍና መምህር የሆኑት ዶ/ር ዳኛቸው በአራተኛነት ያስከተሉት ነጥብ የአርስቶትልን የፍልስፍና አስተምህሮ ምስክር የሚያደርግ ነው። ”እኔ ብዙ ጊዜ የማጣቅሰው የአርስቶትልን የኢቲክስ አስተምህሮ (Nicoomachain Ethics) ነው። በዚህ አስተምህሮ መሠረት ፈላስፋው ብርታት፣ ጉብዝናና ጀግንነት (Courage) ምን እንደሆነ በዘይቤ ያብራራበት ሁኔታ አለ። በአደገኛ እና አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ብርታት፣ ጉብዝናና ጀግንነትን ማሳየት እንዴት እንደ ሆነ ሲያስረዳ፣ ”ዐሥር ሰው ሲመጣብህ ሮጠህ ካልሸሸህ (ካላፈገፈግህ) ጀርጃራ ትባላለህ። አንድ ሰው ሲመጣብህ ከሸሸህ ግን ፈሪ ትባላለህ” የሚል በጣም አስገራሚ ምሳሌ ይሰጣል። እኔ ከዚህ ሰነድ የተረዳሁት ወ/ሪት ብርቱካን እንደ ሰው እና እንደ ፖለቲከኛ ብስለትን ያሳየችበት ውሳኔ ነው። የፈላስፋው ምሳሌ እንዲያውም ዐሥር ሰው ነው የሚለው፤ እርሷ 400 ሺሕ ወታደር ካለው ሰው ጋራ ፊት ለፊት የእሳት ራት አልሆነችም። የፖለቲካ ጎርፍ በመጣበት ጊዜ እንደ አግባቡ ዞር ማለት ብስለት ነው። ይሄ ሰነድ የሷን በሳል ሰብዕና፣ ብርታቷን፣ ጀግንነቷን እና ጉብዝናዋን የሚቀንሰው አይደለም። በአጠቃላይ ይሄ ሰነድ በአንድ በኩል ስለ ኢሕአዴግ በሌላ በኩል ለእኛ ለዜጎች የተላከውን መልዕክት ከማሳየት ሌላ ፋይዳ የሚኖረው አይደለም። በሕግ ፊት ቢቀርብም የሕግ ይዘት የሌለው ሰነድ ነው” በማለት ሰነዱን ፋይዳ ቢስ ያደርጉታል።

 

የወ/ት ብርቱካንን መታሰር የተቃወሙ፣ ከእስር እንድትፈታም ውትወታ ይካሄድበት የነበረው አንዱ መታገያ መንገድ ፌስ ቡክ ነው። ደጋፊዎች በገፆቻቸው በምስላቸው ምትክ የሷን ምስል ተክተው ቆይተዋል። የመፈታቷ ዜና እንደተሰማም ደስታቸውን የገለፁ በርካቶች ናቸው። በስሟ እና ”ነፃነት ለብርቱካን ሚደቅሳ” በሚል የተከፈቱ መጨመርያ መድረኮች (ብሎጎች) በመፈታቷ ደስታቸውን ገልው እስካሁን ድጋፋቸውን ሲሰጡ ለቆዩ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።

 

አንዳንዶች ደግሞ ”ወ/ሪት ብርቱካንን ያደነቅናት በእንቢተኝነቷ እና በቆራጥነቷ ነው፤ ይህን ብርታቷን አሁን በፈረመችው ወረቀት ስናጣው ሰጥተናት የነበረው ራንክ ዝቅ ይልብናል፤” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።

 

ዶ/ር ዳኛቸው ለእንዲህ ዐይነቶቹ አስተያየት ሰጪዎች ምላሽ አላቸው “ሕዝቡ የወ/ት ብርቱካንን የአፈታት ሁኔታ የሚረዳ ይመስለኛል፤ ምንም ዐይነት ምርጫ ያልተሰጣት ልጅ ናት። እንደ ሰው ለራሷ ጤንነት፣ እንደ እናት ለልጇ ኃላፊነት አለባት። ይህን ሰነድ ባትፈርም ከልጇ እና በተዘዋዋሪ ከእናቷ ሁኔታ አኳያ የሞራል ጥያቄ ሊያስነሳ ይችላል። ይሄን ሕዝቡ ይረዳል፤ መረዳትም አለበት። አንድ ቀን ታስረው የማያውቁ ሰዎች የራሳቸውን ፍርድ ሊሰጡ ይችሉ ይሆናል። አንድ ዓመት ከዘጠኝ ወር ለብቻዋ ትንሽ አምባ ላይ ታስራ የነበረች ልጅ ናት። ወጣት ናትና ለነገ መትረፍ አለባት። እኔ ከምጠብቀው በላይ የምትችለውን ያህል ሄዳለች። መጀመሪያ ”ወዮ፣ እናቴ” ብላ ማልቀስ ትችል ነበር፤ አላደረገችውም። ወ/ት ብርቱካን እኮ ፖለቲከኛ ናት እንጂ ክርስቶስ ሠምራ ወይም አቡነ ገብረመንፈሥ ቅዱስን አይደለችም። ይህን መለየት አለብን። እርሷ የኃይማኖት መሪ ወይም የመንፈሣዊ እንቅስቃሴ ኃላፊ አይደለችም። ከሀገራችን ጳጳሳት አንዳንዶቹ ሳይቀሩ መሥራት አልቻልንም እያሉ ስደት በሚሄዱበት ሀገር ላይ አይደለም እንዴ ያለነው? የቆየው ሥርዓት እና ትውፊት እኮ ይህን አይፈቅድላቸውም። ሕገ ቤተ ክርስቲያን የሚፈቅደው ክርስትና ማስተማር ሳይቻል ሲቀር ነው እንጂ፤ አንድ ካህን ለሕይወቴ ያሰጋኛል ብሎ መሸሽ የለበትም። ወ/ሪት ብርቱካን ጠንካራ የሆነች የፖለቲካ መሪ ናት። አሁን ለደረሰችበት ውሳኔ እንዲያውም እኔ ብስለትን ነው ያየሁባት፤ ምክንያቱም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ይፈልጋታል። እነሱ ሊያደርጉ የፈለጉት ያካበተችውን የፖለቲካ አቅም (ፖለቲካዊ ድልብ) እንዳለ አምክነው ሊያስወጧት ነው፤ ነገር ግን በጫና የተፈረመ ሰነድ ይህን ያካበተችውን እና ያዳበረችውን ብርታት፣ ጀግንነት እና ጉብዝና (courage) በምንም መልክ ሊቀንሰው የሚችል አይደለም የሚል አቋም ነው ያለኝ፤” በማለት አስተያየት ሰጥተዋል።

 

ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች በበኩላቸው፣ “ውሎ አድሮ እንዲህ ያለ ሰነድ መፈረሟ ካልቀረ ፊቱኑ የቀረበላትን አማራጭ ብትቀበል ኖሮ” በሚል ለሚሰጡት አስተያየት፤ ዶ/ር ዳኛቸው አጽንዖት ሰጥተው እያስረገጡ በሚናገሯቸው ቃላት መከራከሪያቸውን ያቀርባሉ። ”ጠንካራ ፖለቲከኛ ዝም ብሎ ወደ ኋላ ከመሸሽ ወደ ፊት በመምጣት ይጋፈጣል፤ ዋጋ ይከፍላል፤ እንደ አግባቡ ወደ ኋላ ያፈገፍጋል። ወ/ሪት ብርቱካን ይህን ነው ያደረገችው። ይህቺ ልጅ በመታሰሯ በሀገር ውስጥ ሆነ በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ በኢሕአዴግ ላይ ከፍተኛ ጫና እንዲደርስበት አድርጋለች። በእስሯም ሆነ በተፈታችበት ሁኔታ የሥርዓቱን ምንነት እንድንረዳው አድርጋናለች። ”ያኔ ነግረናት ነበር” የሚሉ ካሉ ዝም ብለው ያውሩ። እሷ ይህን መፈተሿ ፖለቲካው ምን ያህል ዋጋ እንደሚያስከፍል አሳይታናለች። እነኚህ ሰዎች ሥልጣናቸውን ለማስጠበቅ ምን እንደሚያደርጉ በወ/ሪት ብርቱካን እስር አሳይተውናል። ወ/ሪት ብርቱካን ያኔም ልክ ነበረች፤ አሁንም ልክ ናት፤” በማለት በይቅርታ ሰነዱ ላይ ያደረጉትን ምዘና እና ሒሳዊ ዕይታ ይቋጫሉ።

 

የአንድነት ለዴሞክራሲ እና ለፍትህ ፓርቲ የወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳን መፈታት አስመልክቶ ዓርብ መስከረም 28 ቀን ባወጣው መግለጫ ላይ የይቅርታ ሰነዱን በሚመለከት፣ “ወ/ሪት ብርቱካን ይቅርታ ጠየቀች መባሉ አልበቃ ብሎ፣ እነዚያ በመንግሥት የተገለጹት ሐረጐች የተፈለጉት ለዚህ ዓላማ እንደሆነና ወደፊትም የጠንካራ ተቃዋሚ መሪዎችን ክብር ዝቅ ለማድረግ ያስችላል ያለውን ማንኛውንም ስልት ከመጠቀም ወደ ኋላ እንደማይል ለማድረግ የታለመ መሆኑን አንድነት ይገነዘባል። እውነቱን ለሚያውቀው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲህ ያለውን የወረደ የኢሕአዴግ አስተሳሰብ ገዝቶ፣ ለወ/ሪት ብርቱካን ያለውን ከበሬታ ከመቀነስ ይልቅ ለዚህ መንግሥት ያለውን ግምት ይበልጥ ዝቅ እንዲል ያደርገዋል ብለን እናምናለን። በዚህ የኢሕአዴግ ስልት ተነድቶ የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ መድረስ የኢትዮጵያ የተቃዋሚ ኃይል ጠንካራና ተዓማኒ መሪዎች እንዳይኖሩት የማድረግ የኢሕአዴግ ስትራቴጂ ሰለባ መሆን እንደሆነ ልናስገነዝብ እንወዳለን። …” በማለት ገልጿል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!