እሁድ ኖቨምበር 24 ቀን 2013 (እ.ኤ.አ.) በፍሎሪዳ ስቴትስ በምትገኘው ታምፓ ቤይ ከተማ ውስጥ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላት በሳዑዲ ዐረቢያ በሚገኙ የኢትዮጵያ ስደተኞች ላይ እየደረሰ ያለው ኢሰብዓዊ በደል ከልብ እንዳስቆጣቸው ገልጠዋል።

በታምፓ ከተማ የሚኖሩት የኢትዮጵያ ማኅብረሰብ አባላት ለአሜሪካ መንግሥትና ለመላው የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በኢትዮጵያ ስደተኞች ላይ የሚፈጽመውን ኢሰብዓዊ ድርጊት ለማስቆም በሳውዲ መንግሥት ላይ ትርጉም ያለው ተጽዕኖ እንዲደርግ ጠይቀዋል።

በሳዑዲ ዐረቢያ በግፍ የተገደሉትንና የተሰቃዩትን ወገኖቻቸውን በፀሎች ለማሰብ በፔኒንሱላር ቤተክርስቲያን የሻማ ማብራት ሥነሥርዓት ያካሄዱት የታምፓ ነዋሪዎች፤ የሳውዲ መንግሥት ለሚፈጽመው ኢሰብዓዊ ድርጊት በሕግ መጠያቅ ይኖርበታል ብለዋል።

በዓለም አቀፍ ዙሪያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የፖለቲካ ልዩነታቸውን አቻችለው እንደ አንድ ሕዝብ የተቃጣባቸውን በደል እንዲከላከሉና ባስፈላጊው ጊዜ ሁሉ ለወገኖቻቸው መድረስ እንዲችሉም ጥሪ አቅርበዋል።

በሳውዲ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ስደተኞች ሰው በመሆናቸው ብቻ የሚገባቸውን ክብርና የሕግ ከለላ እንዳጡ ተሰብሳቢዎቹ በቁጭት ተናግረዋል። በሳዑዲ ዐረቢያ መንግሥት የሚፈጸመውን አስከፊ ወንጀል በማጋላጥ ረገድም ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና የመገናኛ ብዙኀን ያልተቆጠበ ጥረት እንዲያደረጉ አደራ ብለዋል።

የታምፓ ቤይ የኢትዮጵያ ማህብረሰብ አባላት በዚሁ የሻማ ማብራት ሥነሥርዓት ላይ የተጎዱ ወገኖቻቸውን በሚችሉት አቅም ሁሉ ለመርዳት ቃል ከመግባት ባለፈ፤ በዕለቱ የገንዘብ ማሰባሰብ ሥራ ጀምረዋል። በቀጣይም፤ በማህበረሰቡ የሚመረጥ ኮሚቴ አዋቅረው የተጎዱ ወገኖቻቸውን ለመርዳትና ተመሳሳይ ወንጀሎችን ለመካላከል የበኩላቸውን እንደሚጥሩ አስታውቀዋል።

በሻማ ማብራት ሥነሥርዓቱ ላይ በሳዑዲ ዐረቢያ በሚኖሩ የኢትዮጵያ ስደተኞች ላይ የተፈጸሙ አሰቃቂ ወንጀሎችን የሚያሳዩ የፎቶግራፍ እና የቪድዮ መረጃዎች ለዕይታ የቀረቡ ሲሆን፤ ታዳሚዎችም ስሜታቸውን መቆጣጠር ባለመቻል ሲያለቅሱ ተስተውለዋል።

ታምፓ/ፍሎሪዳ
ጊዜያዊ አስተባባሪ ኮሚቴ

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!