ጽዮን ግርማ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.(በፋክት መጽሔት የታተመ)
የታሰሩት ስድስቱ ጦማሪያንና (Bloggers) ሦስቱ ጋዜጠኞች 3 jailed journalists and 6 bloggers
ሚያዚያ 17 እና ሚያዚያ 18 ቀን 2006 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር የዋሉት ስድስቱ ጦማሪያንና (Bloggers) ሦስቱ ጋዜጠኞች በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ማዕከል (ማዕከላዊ) ከታሠሩ ዛሬ ሃያ ሦስተኛ ቀናቸውን ይዘዋል። በእነዚህ ጊዜያት ውስጥም በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት በጊዜ ቀጠሮ መዝገብ ሁለት ጊዜ ቀርበዋል። እሁድ ሚያዝያ 19 ቀን 2006 ዓ.ም. ለመጀመሪያ ጊዜ ሲቀርቡ ብቻቸውን በመኾኑም የፍርድ ቤቱ ድባብ ምን ይመስል እንደነበር የሚያውቅ አንድም ታዛቢ ሰው አልነበረም።

ፍርድ ቤት መወሰዳቸው የተሰማውም በማግስቱ ቁርስ ለማድረስ ወደ ማዕከላዊ የሄዱት ቤተሰቦቻቸው ካገኙት ጥቆማ ነበር። ከፍርድ ቤቱ የጊዜ ቀጠሮ መዝገብ የተገኘው መረጃ እንደጠቆመው ዘጠኙ ተጠርጣሪዎች በሦስት የጊዜ ቀጠሮ መዝገብ ተለያይተው መቅረባቸውን ነበር። የጊዜ ቀጠሮ ማመልከቻው ጭብጥም፤ [ራሱን የመብት ተሟጋች ነኝ ብሎ ከሚጠራ የውጭ ድርጅቶች ጋራ በሐሳብና በገንዘብ በመረዳዳት ማኅበራዊ ድረ ገፆችን በመጠቀም ሕዝቡን ለአመፅ ለማነሳሳት የተለያዩ ቀስቃሽ መጣጥፎችን ለማሰራጨት ሲዘጋጁ ተደርሶባቸዋል።] የሚል ነበር። 

ፖሊስ ያሰራቸውን ተጠርጣሪዎች ምርመራ እስኪያጠናቅቅም የዐሥራ አምስት ቀናት የጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው ቢጠይቅም ፍርድ ቤቱ የፈቀደው ዐስር ቀናት ብቻ በመኾኑ፤ ጋዜጠኛ ተስፋዓለም ወልደየስ፣ ጋዜጠኛ አስማማው ኃይለ ጊዮርጊስና የሕግ መምሕርና የዞን ዘጠኝ ጦማሪ ዘለዓለም ክብረት እንዲሁም በሁለተኛው መዝገብ ጋዜጠኛ ኤዶም ካሳዬ፣ የዞን ዘጠኝ ጦማሪዎቹ ናትናኤል ፈለቀና አጥናፉ ብርሃነ በአጠቃላይ ስድስቱ ተጠርጣሪዎች ለሚያዚያ 29 ቀን 2006 ዓ.ም ተቀጥረው ነበር። በሦስተኛው መዝገብ ደግሞ ሦስቱ የዞን ዘጠኝ ጦማሪዎች አቤል ዋበላ፣ በፍቃዱ ኃይሉና ማኅሌት ፋንታሁን ለሚያዝያ 30 ቀን 2006 ዓ.ም. ከጠዋቱ አራት ሰዓት እንዲቀርቡ ቀጠሮ ተሰጥቷቸው ነበር። 

ቀን ሁለት - ጠዋት
በቀጠሮው ቀን ጉዳዩን ለመከታተል ወደ ፍርድ ቤት የሚመጡ ሰዎችን የእርስ በእርስ ስልክ አጨናንቆ የነበረው ዋናው ጉዳይ የፍርድ ቤቱን አድራሻ ማግኘት ነበር። አራዳ ምድብ ችሎት ቀደም ሲል ይገኝበት ከነበረው የፒያሳው ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አቅራቢያ ተሰውሯል። አካባቢው በባቡር መተላለፊያ ሃዲድ ግንባታ ምክንያት ፈራርሶ ፍርድ ቤቱ በአካባቢው ካለ የጤና ጣቢያ ግቢ ጋር ተቀላቅሏል። ፍርድ ቤቱን ለማግኘት በመጸዳጃ ቤት ሽታ የታወደውን ጓሮ ማቋረጥ የግድ ነበር። የፈራረሰው አጥር እጅግ ካረጁትና አቅም ካጡት የፍርድ ቤቱ ችሎቶች፣ ጽሕፈት ቤትና ግቢው ውስጥ ካሉት ሌሎች ቤቶች ጋር ተደማምሮ የፍርድ ቤቱን ድባብ አስፈሪ አድርጎታል።

የአራዳ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት የጊዜ ቀጠሮ መዝገብ መመልከቻ ጊዜ ከሰዓት በኋላ ቢኾንም መጀመሪያ ላይ ጉዳዩን የተመለከቱት ዳኛ ቀጠሮ የሰጡት ለሚያዚያ 29 ቀን 2006 ዓ.ም ጠዋት አራት ነበር።በዚህ ሰዓት ፍርድ ቤት ግቢ የደረሰው ችሎት ተከታታይ በርካታ ነው። ገና አራት ሰዓት ሳይሞላ ግቢው በእስረኞቹ ቤተሰብ፣ ወዳጅ ዘመድ፣ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ብዙኃን መገናኛ ጋዜጠኞች፣ የአሜሪካ ኤምባሲ፣ የአውሮፓ ሕብረትና የሌሎች አገራት ዲፕሎማቶች ተሞልቶ ነበር። አንዳንድ ያልታወቁ ጸጉረ ልውጦችም በግቢው ውስጥ መታየታቸው አልቀረም።

እንዲህ አዲስ ጉዳይ ሲገጥም እንደሚደረገው ኹሉ በዕለቱ የሚኖረውን ችሎት ለመታዘብ የመጡት በርካታ ሰዎች እርስ በእርስ ስለ ጉዳዩ የራሳቸውን መላ ምት ይሰጣሉ። ሁሉም ከእስረኞቹ መካከል የሚያውቀውን ስም እየመዘዘ ምግባራቸውን ለሌሎች ያካፍል ነበር። አንዳንዱም በዕለቱ ተጠርጣሪዎቹን ወክለው ጥብቅና ለመቆም ወደ መጡት አቶ አመሐ መኮንን ቀረብ እያለ አስተያየት ይጠይቅ ነበር። በተለይ የሰዓቱ ኹኔታ በጣም አጠራጣሪ ስለነበር ፖሊስ እስረኞቹን ያቀርባቸዋል አያቀርባቸውም የሚለው አወዛጋ ጉዳይ ነበር። በአጠቃላይ በችሎቱ ታዳሚዎች ፊት ላይ ግራ መጋባት ይነበብ ነበር። 

ከተቀጠረበት ሰዓት ሠላሳ ደቂቃ እንዳለፈም የችሎቱ ጸሐፊ ወደ ጠበቃው ቀርባ፤ ”ችሎቱ ለጠዋት አራት ሰዓት የተቀጠረው በስህተት ነው። እሁድ ዕለት የተሰየሙት ተረኛ ዳኛ ስለ መደበኛው የችሎት ሰዓት ባለማወቅ የሰጡት ቀጠሮ በመኾኑ አሁን በፍርድ ቤት ውስጥ ይህ ሁሉ ሰው ከሚቆም ሂዱና ስምንት ሰዓት ላይ እንድትመጡ ተብሏል”በማለት መልዕክት አስተላለፈች። ጠበቃው፤ ታዳሚውም ኾነ እርሳቸው ከሄዱ በኋላ ፖሊስ እስረኞቹን ቢያቀርባቸውስ ? ሲሉ አጥብቀው ጠየቁ። ጸሐፊዋ መልዕክቱን እንድታደርስ ከችሎት መላኳንና ፖሊስም የሰዓቱ ጉዳይ ስለተነገረው ከሰዓት በኋላ እንደሚያቀርባቸው አስረግጣ ተናገረች። 
ማንም ግን ይህን መልዕክት ብቻ ተቀብሎ ግቢውን ለቆ ለመውጣት ፈቃደኛ አልነበረም። አብዛኛው ሰው ለሠላሣ ደቂቃ ያህል ባለበት ከቆመ በኋላ ባገኘው መቀመጫ ላይ ራሱን አሳረፈ። የምሳ ሰዓት ሲደርስ ግቢውን ለቆ ከወጣው ጥቂት ሰው በስተቀር ብዙሃኑ በተለይ የእስረኞቹ ቤተሰቦች እዛ ግቢ ውስጥ እንደተቀመጡ የከሰዓቱ ቀጠሮ ደረሰ። 

ቀን ሁለት - ከሰዓት በኋላ
ከሰዓት በኋላ የተገኘው ሰውም ከጠዋቱ በቁጥር የጨመረ ነበር።ችሎቱ ጠባብ በመኾኑ እንደተከፈተ ቅድሚያ ለመግባት የጓጓው ሰው አስቀድሞ የችሎቱ መግቢያን ይዟል። የሁሉም ሰው ዐይን በጓሮው በር ላይ ተተክሏል።ከኤዶም ካሳዬ በስተቀር የሁሉም ተጠርጣሪዎች ጠበቃ አቶ አመሐ መኮንን የነበረውን ኹኔታ ለ”ፋክት መጽሔት” ሲያስረዱ፤ ”በዕለቱ የነበረው በርካታ ሰው ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹን ያቀርባቸዋል አያቀርባቸውም የሚለው ላይ ጥርጣሬ ነበረው። ከቀረቡስ በኋላ ምን ዓይነት ውጤት ይገኛል? የሚለውም ሌላ አሳሳቢ ነገር ነበር። በተለይ ደግሞ በጠበቃ ተወክለው የሚቀርቡበት የመጀመሪያ ቀን ስለነበር በችሎት ሊፈጠር የሚችለውን ነገር የማወቅ ጉጉት ነበር።እንዲሁም ቤተሰብ ከዐሥራ ሁለት ቀናት በኋላ ልጁን ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያይበት ቀን በመኾኑ የሰዓቱን መድረስ በጉጉት ነበር የሚጠብቀው” ይላሉ። 

ከቀኑ ስምንት ሰዓት ሲኾን፤ ”መጡ፣ መጡ” የሚል ድምፆች በቀስታ መሰማት ጀመሩ አንድም ሰው ሳይቀር ወደ በሩ አሰፈሰፈ። በፌደራል ፖሊስ ከፍተኛ ጥበቃ ሥር የወደቁ ሦስት ወጣቶች ተራ በተራ ወደ ግቢው ዘለቁ። ከተጠርጣሪዎቹ የመጀመሪያውን ሰልፍ የያዘው አጥናፉ ብርሃነ ነበር። አጥናፉ እጁን በሰንሰለት እንደታሰረ ለሚያውቃቸው ሰዎች በፈገግታ ሰላምታ ለመስጠት ይሞክር ነበር። እጇን በሰንሰለት ባትታሰርም ግራ የመጋባትና የመሸማቀቅ ስሜት ይዛ ወደ ግቢው የገባቸው ሁለተኛዋ እስረኛ ኤዶም ካሳዬ ናት። ኩርፊያ እና ሐዘን ተቀላቅለው ፊቷን አጠይመውታል። ከሁለቱም በቁመት ዘለግ ያለውና አንገቱን ወደ ታሰሩት እጆቹ አዘቅዝቆ በከፍተኛ ሐዘን ወደ ግቢው የገባው ናትናኤል ፈለቀ ዐይኖች መቅላትና ማበጥ ምናልባት ተጠርጣሪዎቹ ድብደባ ሳይደርስባቸው አይቀርም አሳድሮ ነበር።

ፖሊሶቹ እስረኞቹን ይዘው ሲመጡ በር ላይ የተሰበሰበውን ሰው አባረሩና በአንድ ጊዜ አካባቢውን አጸዱት። እስረኞቹንም ከአነስተኛዋ ችሎት ጎን በሚገኘው ሌላ ክፍል በማስገባት ፊታቸውን ወደ ግድግዳው እያዞሩ ሰንሰለቱን ከእጃቸው ላይ አወለቀሉላቸው።ጥቂት ቆይተውም ወደ ችሎት አስገቧቸው። ተጠርጣሪዎቹን ወክለው በችሎት የተገኙት ጠበቃ አቶ አመሐ መኮንን ስለ ችሎቱ አሰያየም ሲናገሩ፤ ”ፍርድ ቤቱ ጉዳዩ በዝግ ችሎት ይታያል ሲል በግልጽ ትዕዛዝ ባይሰጥም በተግባር ግን ዝግ ነበር ማለት ይቻላል። ጉዳዩ በታየበት ክፍል ውስጥ ከዳኛ፣ ከፖሊስ፣ ከተጠርጣሪዎቹ፣ ከየችሎት ሥርዓት አስተናባሪዎችና ጠበቆች ውጪ ማንም እንዲገባ ስላልተፈቀደ በዝግ ነው የታየው ማለት ይቻላል።”ብለዋል። 

መጀመሪያ ወደ ችሎት የገቡት ሦስቱ ተጠርጣሪዎች ብቻ ስለነበሩ በዕለቱ ተቀጥረው የነበሩትን ሌሎቹን ሦስቱን እስረኞች ፖሊስ ላያቀርባቸው ይችላል በሚል ስጋት ተፈጥሮ ነበር። ቆየት ብሎ ግን በተመሳሳይ ኹኔታ በተጠናከረ የፖሊስ ጥበቃ ተስፋዓለም ወልደየስ፣ አስማማው ኃይለጊዮርጊስና ዘለዓለም ክብረት እጆቻው በሰንሰለት ታስረው በሰልፍ ወደ ፍርድ ቤቱ ግቢ ገቡ። ልክ እንደ ቀደሙት ኹሉ የእነርሱም እጆች ከሰንሰለት ተላቀው ዳኛ ፊት ቀረቡ። አቶ አመሐ እንደሚሉት፤ ”ከተጠርጣሪዎቹ ጋራ ቀደም ብለን ተገናኝተን ስላልነበር በችሎት ላይ ምን ዓይነት መብት ሊኖራቸው እንደሚችል፣ ስለ አያያዝ ሁኔታቸውም መናገር እንደሚችሉ አያውቁም ነበረ።እኛም በአያያዛቸው ላይ የተለየ ችግር እንደነበር መረጃው አልነበረንም።” ይላሉ። አያይዘውም በማናቸውም ጉዳይ ተጠርጥሮ የታሰረ ሰው ከተያዘበት ቀን ጀምሮ ጠበቃ የማግኘት መብቱ በሕግ የተደነገገ በመኾኑ ደንበኞቻቸው በጣቢያ እያሉ ለማግኘት ጥረት አድርገው እንደተከለከሉ ለችሎት በማሳወቅ ለትክክለኛ ፍትሕ አሰጣጥ እንዲበጅ ደንበኞቻቸውን እዛው ለዐሥራ አምስት ደቂቃ እንዲያነጋግሩ እንዲፈቀድላቸው ለችሎት ያመለክታሉ።

”ለፍርድ ቤቱ ያመለከትነው ከደንበኞቻችን ጋር በጣቢያ ቀርበን መነጋገር አለመቻላችን እስከታመነ ድረስ ለትክክለኛ ፍትሕ አሰጣጥ እንዲበጅና በፖሊስ ጣቢያ የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት ሲባል ችሎት ላይ ማነጋገር እንዲፈቀድልን ነበር። ነገር ግን ከፍርድ ቤቱ የተነገረን ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ጉዳይ እንዲህ ያለ ጥያቄ ተነስቶ ተጠርጣሪዎቹ ፍርድ ቤት የመጡት ለሌላ ጉዳይ ስለኾ ፖሊስ ፈቃደኛ አልነበረም። ስለዚህም አሁን ለመፍቀድ እንቸገራለን። በማለት ሳይፈቀድልን ቀርቷል” በማለት ደንበኞቻቸውን ችሎት ላይ ለማነጋገር ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ መቅረቱን ይናገራሉ። 

”ስለዚህ በቀጥታ የተገባው ተጨማሪ ዐሥራ አምስት ቀን ጊዜ ቀጠሮ ይሰጠኝ ሲል ፖሊስ ወዳቀረበው ማመልከቻ ነው” ይላሉ የፍርድ ቤቱን ሂደት ሲናገሩ። ቀደም ሲል በነበረው ቀጠሮ ተጠርጣሪዎቹ የታሰሩት ከማኅበራዊ ድረ ገጽ ጋራ በተያያዘ መኾኑን በተባባሪ ወሬ ሰምተው ስለነበር በዕለቱም የገመቱት ተመሳሳይ ነገር ነበር። በዚህም ምክንያት ፖሊስ በያዘው ማመልከቻ ያቀረበውን የጥርጣሬ ምክንያት ሲሰሙ አዲስ ነገር ኾኖባቸው እንደነበር ይናገራሉ። 

”እኔና የኤዶም ካሳዬ ጠበቃ ዶ/ር ያሬድ ለገሰ ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ ልጆቹ የተጠረጠሩበትን ጉዳይ የሰማነው የዛን ዕለት ነው። ቀደም ሲል አግኝተናቸው ቢኾን ከእነርሱ በርካታ ነገር ልንሰማ እንችል ነበረ። ይህ ሳኾን በመቅረቱ ፖሊስ በዛን ዕለት፤ [ተጠርጣሪዎቹ በሕዝብ ተመርጦ ሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት ምርጫ 2007 ከመድረሱ በፊት ሕዝብን ለአመጽ አነሳስቶ መንግሥትን ለመጣል እንዲያስችላቸው በሕቡዕ ተደራጅተው ሲያበቁ አመጹን የሚያስነሱበትን መንገድና ኹኔታ በመንደፍና ዕቅድ በማውጣት፣ ለሌሎች ሰዎች ስልጠና በመስጠት ከዛም ሕዝባዊ አመፁን ለመምራት ዝግጅት ላይ እንደነበሩ፣ ለዚህም ይረዳቸው ዘንድ በአገር ውስጥና በውጭ አገር ከሚገኙ ሽብርተኛ ድርጅቶች ጋራ ግንኙት በመፍጠር የገንዘብ ድጋፍ ማግኘታቸውን፣ ከአፍሪካና ከዛም ወጪ እስከ ስዊድን ድረስ ሄደው በሥራቸው ሽፋን የተለያየ ሥልጠና መውሰዳቸውን፣ በሕግ ተፈርዶባቸው እስር ቤት ያሉ ሰዎችን እንዲፈቱ የተለያየ ግፊት ማድረጋቸውን] በመግለጽ ሰፋ ያለ ውንጀላ አቅርቦባቸዋል።” ያሉት አቶ አመሐ ፖሊስ ለዚህ ጥርጣሬው አጋዥ የሚኾነውን ምርመራ አጠናቆ ስላልጨረሰ ተጨማሪ የዐሥራ አምስት ቀን ጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው የጠየቀበትም ምክንያት በችሎት ማብራራቱን ይናገራሉ። 

ስለ ማብራሪያው ሲገልጹም፤ ”ፖሊስ ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ የጠየቀበትን ምክንያት ሲያስረዳ፤ [ያልተያዙ የተጠርጣሪዎቹን ግብረ አበሮች መያዝ፣ የምስክሮችን ቃል መቀበል፣ ሰነዶች ማስተርጎም እና ተጠርጣሪዎቹ ከውጭ አገር ባገኙት ገንዘብ የገዟቸውን የተለያዩ ኮምፒዩተሮችና የመገናኛ መሳሪያዎች ቤታቸውና ከቤታቸው ውጪ ባለ ሌላ ስፍራ ስላስቀመጡ እሱን በብርበራ መያዝ ይቀረናል እንዲሁም የተያዙትን ንብረቶችና ሰነዶች በቴክኒክ ማስመርመር ይቀረናል] በማለት ነበር።”

”በኛም በኩል ለችሎቱ እንዲህ በማለት አስረድተናል፤ [ፖሊስ ያቀረበው አብዛኛው ጥያቄ ተጠርጣሪዎቹ ከመያዛቸው በፊት ሊሠራ የሚገባው ጉዳይ ነበር። ሕጉም የሚለው አንድ ሰው በወንጀል ተጠርጥሮ ሊያዝ የሚችለው ትርጉም ያለው ማስረጃ ከተሰባሰበ በኋላ ነው። የተዘረዘሩትን ነገሮች ለማጣራት ተጠርጣሪዎቹን በእስር ማቆየት አስፈላጊነቱ አይታየንም ስለዚህ በዋስ ተለቀው ምርምራው ሊቀጥል ይችላል] ብለን አመለከትን የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ፍርድ ቤቱ ፖሊስ ከጠየቀው ቀነ ቀጠሮ ላይ አምስት ቀን ቀንሶ ተጨማሪ ዐሥር ቀናትን ለምርመራ ፈቀደ።” በማለት ስለ ክርክሩ አስረድተዋል። 

ክርክሩ ካበቃ በኋላ ተጠርጣሪዎቹ ከችሎት ሲወጡ የተወሰኑት ፊት ላይ መረጋጋትና ፈገግታ ታይቷል። ግራ ቀኝ እየተዟዟሩም ቤተሰቦቻቸውን ሰላም ሲሉ ተስተውሏሏ። አንድ ኹለት የሚኾኑት ግን ቁጭትና ሐዘን እንዳጠላባቸው ነበር። ግራና ቀኝ በፖሊስ ጥበቃ የቆመው ቤተሰብ ጮክ ብሎ የልጆቹን ስም እየጠራ የማበረታቻና የሰላምታ ቃላትን ሲወረውር ነበር። የአብዛኛው እስረኛ ወላጆችም ልጆቻቸውን የሸኙት በለቅሶ ነበር። በዚህ ጊዜ የቀድሞ የአዲስ ስታንዳርድ አምደኛና የሕግ ባለሞያ ኪያ ጸጋዬ ተጠርጣሪዎቹ በፍርድ ቤት ግቢ እያሉ ፎቶ አንስተሃል በሚል ከከፍተኛ የፖሊስ ጥፊ ጋራ እስረኞቹ በመጡበት መኪና አብሮ ተጭኖ ተወስዷል። ከአንድ ቀን እስር በኋላም ተለቋል። በግቢው የነበረው ሰው ተጠርጣሪዎቹን ከሸኘ በኋላ በችሎት የተነገረውን ለመስማት የጠበቃውን አቶ አመሐ ዙሪያ ከቦ በመቆም ከችሎት ያገኙትን መረጃ እንዲያካፍሉት ሲወተውት ነበር። እርሳቸውም የፍርድ ቤቱን ሂደት በዝርዝር ለነበረው ሰው አስረድተዋል። 

ቀን ሦስት - ከሰዓት በኋላ
በማግስቱ ሚያዚያ 30 ቀን 2006 ዓ.ም የቀረቡት ተጠርጣሪዎች አቤል ዋበላ፣ በፍቃዱ ኃይሉና ማኅሌት ፋንታሁን ነበሩ። በፍርድ ቤት ግቢ ውስጥና በችሎት የነበረው ኹኔታ ከአንድ ቀን በፊት ከነበረው ጋር ተመሳሳይ ነበር። አቶ አመሐ ሲናገሩ፤ ”የዚህኛውን ቀን ለየት ሚያደርገው ቀደም ባለው ቀን ችሎቱ የታየው በዝግ እንደኾነ ተደርጎ መቅረቡ አግባብ እንዳልነበር፣ ጉዳዩ የሚታይበት ችሎት ጠባብ በመኾኑ ተጨማሪ ሰው የመያዝ አቅም ስለሌለው በመኾኑ በችሎቱ ተጨማሪ ሰው የመያዝ አቅም ልክ ተጠርጣሪዎቹ እንዲገባላቸው የሚፈልጉትን ሰው መርጠው እንዲያስገቡ ዕድል ተሰጥቷቸው ሦስት ሰው እንደገባ ተደርጓል” ብለዋል።

”የቀረበውም የጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ክርክር ተመሳሳይ ነበር። በኛ በኩል ግን ፖሊስ ሕቡዕ ሲል ምን ማለቱ እንደኾነ ጠይቀናል። ”ዕቡዕ” የሚባለው ሰዎች በግልጽ ሊያቋቁሙት ይገባቸው የነበረውን ድርጅት በድብቅ ሲያቋቁሙት እንደኾነ ተጠርጣሪዎቹ ግን በድረ ገጽም ላይ ሲጽፉ ከእነ ስማቸውና ፎቶግራፋቸው በግልጽ አስቀምጠው በመኾኑ በ”ሕቡዕ” ተደራጅተዋል ሊባል እንደማይገባ ገልጸን ስንከራከር። ፖሊስ በበኩሉ [ተጠርጣሪዎቹ የተያዙበት ጉዳይ በማኅበራዊ ድረ ገጽ ከመጻፍ ጋራ ምንም ግንኙነት የለውም] በማለት መከራከሪያ አቅርቧል። በማለት አስረድተዋል።

”በዕለቱ ከቀረቡት ሦስት ተጠርጣሪዎች መካከል አቤል ዋበላና በፍቃዱ ኃይሉ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር በሚገኙበት ቦታ በምርመራ ወቅት ድብደባ እንደተፈጸመባቸው፣ ውስጥ እግራቸው መገረፉን፣ ስድብና ማዋራድ የተፈጸመባቸው መኾኑን በመግለጽ በተለይ አቤል ዋበላ ይህንኑ መጀመሪያ ላይ ፍርድ ቤት በቀረቡበት ቀን መናገሩን በመግለጽ አያያዛቸው ላይ ሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸሙን ለችሎት አስረድቷል።ፖሊስ በበኩሉ የቀረበው ውንጀላ ውሸት መኾኑን በተቋሙ እንዲህ ያለ ነገር እንደማይፈጸም በመግለጽ ተከራክሯል። በኛም በኩል ልጆቹ ከጠበቃና ከቤተሰብ ጋራ እንዳይገናኙ ተደርጎ ከተያዙበት ኹኔታ አንጻር አቤቱታቸው ሊታመን የሚችል መኾኑን በመግለጽ፤ ፖሊስ እንደ ተቋም ድርጊቱን ላይፈጽም ይችላል ነገር ግን አባላቱ እንዲህ ያለ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሊፈጽሙ አይችሉም ብሎ መከራከር እንደማይቻል ምክንያቱም ከዚህ ቀደም በተግባር እንዲህ ዓይነት ድርጊት ተፈጽሞ ፖሊስ ራሱ አምኖበት እርምጃ ወሰድኳባቸው ያላቸው አባላት እንዳሉ በመግለጽ ለዚህ መፍትሔ የሚኾነው ያለምንም ቅድመ ኹኔታ እስረኞቹ በቤተሰቦቻቸውና በጠበቆቻቸው መጎብኘት መጀመር እንዳለባቸው ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥ ጠይቀናል። በመጨረሻም ከፖሊስም ከፍርድ ቤቱም ጋር ተማምነን ተጠርጣሪዎቹ ከቤተሰብም ከጠበቃም ጋር እንዲገናኙ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል” ብለዋል።

ችሎቱ እንደተጠናቀቀና ተጠርጣሪዎቹ ወደ መኪናቸው ከመወሰዳቸው አስቀድሞ የቆመውን ሰው የተቀላቀሉት ችሎት ገብተው የነበሩት ሦስቱ ቤተሰቦች፤ እስረኞቹ መደብደባቸውን ለችሎት ገልጸው እንደነበር አስቀድመው ሹክ በማለታቸው አብዛኛው ቤተሰብ በእልህና በለቅሶ ተወጥሮ ነበር። ልክ እስረኞቹ ወደ መኪናው መወሰድ ሲጀምሩ ሰዎ በፉጨት፣ በጭብጨባ፣ በጩኸትና ለቅሶ ሸኝቷቸዋል። ከተል ብለው የወጡት አቶ አመሐ ስለ ዕለቱ ውሎ ለተሰበሰበው ሰው ማስረዳት ሲጀምሩም በድጋሚ ችሎት ተጠርተው ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል። ማሳሰቢያውን እርሳቸውም እንደሚስማሙበት የተናገሩት አቶ አመሐ፤ ” ዳኛዋ በግቢው ውስጥ በርካት ችሎቶች ስለሚገኙ በጩኸቱ ሌላው ችሎት ይረበሻል ስለዚህ በድጋሚ እንዲህ ዓይነት ነገር የሚፈጠር ከኾነ ጭርሱኑ እንዳትገቡ ልትከለከሉ እንደምትችሉ ተናግረዋል ስለዚህ እንዲህ ያለው ነገር ደንበኞቼን ስለሚጎዳ በድጋሚ እንዳታደርጉት እንመክራለን” ብለዋል። 

ሃያ ሦስት ቀናት በማዕከላዊ
አቶ አመሐ እንዳሉት በፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ በሰጠ ማግስት እስረኞቹን ለመጎብኘት በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ማዕከል (ማዕከላዊ) እርሳቸውም ኾኑ ዶ/ር ያሬድ ለገሰ የተገኙ ቢሆንም ጉዳዩ ይመለከታቸዋል የተባሉትን ኃላፊ ጭምር አነጋግረው ሊፈቀድላቸው እንዳልቻለ ጠቁመዋል።”ቤተሰብም ቢኾን ወጥነት በሌለው ኹኔታ ለአንድ ጊዜ ብቻ ለጥቂት ሰዓታት አገናኝተው በድጋሚ እንደተከለከሉ ነግረውናል። ስለዚህ በዚህ ሣምንት ለመግባት እንሞክርና የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እንዲሰጥልን ለፍርድ ቤቱ እናመለክታለን” ብለዋል።

ፖሊስ አስቀድሞ በጹሑፍ ሳይቀር ተዘጋጅቶ እየቀረበ እነርሱ ግን ደንበኞቻቸውን ማግኘት ሳይችሉ ዝም ብሎ ችሎት እየመጡ መቆም ሒደቱን ከማዳመቅ ውጪ ምንም መፍትሔ እንደማይኖረው የጠቆሙት አቶ አመሐ፤ ”በዚህ ሣምንት ፖሊስ ደንበኞቻችንን የማያሳየን ከኾነ ፍርድ ቤቱ እርምጃ መውሰድ አለበት። እኛም የሚመለከተው የፖሊስ አካል ለምን የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ማክበር እንዳልቻለ ቀርቦ እንዲጠየቅ፣ እርምጃም እንዲወሰድበት፣ እስረኞቹ ከጠበቃና ቤተሰቦቻቻው ጋራ መገናኘት እንዲችሉ እንዲደረግ አቤቱታ እናሰማለን ይህ ካልኾነ ግን እርምጃው የየግላችን ይኾናል ብለዋል። ዘጠኙ ተጠርጣሪዎች ዛሬ (ቅዳሜ ግንቦት 9 ቀን 2006 ዓ.ም. / ሜይ 17 ቀን 2014 እ.ኤ.አ.) እና ነገ ይቀርባሉ።

Journalist Tsion Girma, ጋዜጠኛ ጽዮን ግርማ
ጽዮን ግርማ
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

(በፋክት መጽሔት የታተመ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!