አቢይ አፈወርቅ
Sydney candlelight vigil. በሊቢያ በደቡብ አፍሪካና የመን ለተገደሉ ወገኖቻችን በሲድኒ የሻማ ማብራት ሥነሥርዓት ተከናወነ

በሊቢያና በደቡብ አፍሪካ በሚኖሩ ወገኖቻችን ላይ የተፈጸመው አሰቃቂ ግድያ ያስቆጣቸው የሲድኒ ነዋሪ ኢትዮጵያዊያን እሁድ ኤፕሪል 26 ቀን 2015 ዓ.ም. ልዩ የሻማ ማብራት ስርአት አካሂደዋል። በዚህ በኒው ሳውዝ ዌልስ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ማህበር አስተናባሪነት በተዘጋጀው ሥነሥርዓት ላይ ቁጥራቸው ከ350 በላይ የሚሆኑ የከተማዋ ነዋሪ ኢትዮጵያዊያን ተገኝተው ነበር።

ፓራማታ በተሰኘው ቀበሌ አንድ የመናፈሻ ስፍራ ላይ የተሰባሰቡት እነዚህ ኢትዮጵያውያን እራሱን እስላማዊ መንግስት እያለ የሚጠራዋ አሸባሪ ኃይል ሊቢያ ውስጥ በአሰቃቂ ሁኔታ የገደላቸውን 28 ወገኖቻቸውንና በሌላ መልኩም በደቡብ አፍሪካ በግፍ የተገደሉ ወንድሞቻቸውን በከፍተኛ ስሜት ዘክረዋል። መናፈሻው የመሪር ሀዘን፣ የቁጭትና ቁጣ ድባብ አጥልቶበት ነበር ያመሸው።

በረጅሙ ከተዘረጋ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ የኢትዮጵያ ባንዲራ ጀርባ ተደርድረው ሻማ ሲያበሩ ያመሹት የሲድኒ ነዋሪ ኢትዮጵያውያን ኃዘን በሰበረው ልብ፣ በቆሰለ ስሜትና በትካዜ ዘለግ ያለ የፅሞና ጊዜ የወሰዱ ሲሆን የማህበሩ ፕ/ት አቶ አያሌው ሁንዴሳ ምጥን ግን ህሊናን ሞጋች የመግቢያ ንግግር አድርገው ሌሎችም ስሜታቸውን እንዲገልጹ ጋብዘዋል።

በዚህም መሰረት የተለያዩ ኢትዮጵያውያን የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘንና ቁጣ እንደየዕይታቸው ለመግለጽ ዕድል አግኝተዋል። ሰለባዎቹን በመዘከርና ገዳዮቹን በመኮነን ሳይወሰኑ የችግሩን ምንጭ ለመመርመር የሞከሩም ነበሩ። በታሪካችን ባልታየ ደረጃ የኢትዮጵያ ልጆች እንዲሰደዱና ክብራችን በማንም የሚደፈር የተናቅን እንድንሆን ያበቃን የኛው ገዢ መንግስት ነው የሚሉ ጠንካራ አስተያየቶች የተሰሙ ሲሆን ፈጣሪ ኢትዮጵያውያንን ያስባል፣ ጸንተን እንጸልይ የሚሉ ጥሪዎችም ቀርበዋል። የሲድኒ ደብረ ፂዮን ቅድስተ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ዋና አስተዳዳሪ የሆኑት ቀሲስ ደረሰኝ መንግስቴም ከዕምነት አኳያ ለተሰዉት ሰማዕታትክብር ሰጥተውና መጽናናትን መክረው ፀሎት አድርሰዋል።

የግብጽ ኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን ተወካይ፣ የክርስቲያን ዲሞክራቲክ ፓርቲ ፕ/ት እና የኒው ሳውዝ ዌልስ መንግስት ም/ቤት ሴናተር የሆኑት ሪቨረንድ ፍሬድ ናይል እንዲሁም ባለቤታቸው ሲልቫና ኔሮ የኃዘናችን ተጋሪዎች መሆናቸውን ከገለጹትና መልእክት ካስተላለፉት መሀል ይጠቀሳሉ።

ከ26 ዓመታት በላይ የዘለቀው በኒው ሳውዝ ዌልስ የኢትዮጵያውያን ኮሚኒቲ ማህበር በጥቂት ቀናት ዝግጅት ማህበረሰቡን በከፍተኛ ቁጥር አሰባስቦ ኃዘናችንን በጋራ እንድንወጣና ሰለባ ወገኖቻችንን እንድንዘክር በማመቻቸቱ የተለያዩ ወገኖች ምስጋና አቅርበውለታል።

በተመሳሳይ መልኩ የሲድኒ ደብረ ፂዮን ቅድስተ ማርያም ቤተ ክርስቲያን እሁድ ጠዋት በሊቢያና በደቡብ አፍሪካ በግፍ ለተሰዉት ወገኖቻችን ፍትሀተ ፀሎት ያደረገች ሲሆን ከ150 በላይ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች በቅድስት ቤተ ክርስቲያኗ ተገኝተው ፀሎት ማድረሳቸውንና ትምህርት መቀበላቸውን ለመረዳት ተችሏል። ተጨማሪ ፎቶዎችን ከዚህ በታች ይመልከቱ!

Sydney candlelight vigil. በሊቢያ በደቡብ አፍሪካና የመን ለተገደሉ ወገኖቻችን በሲድኒ የሻማ ማብራት ሥነሥርዓት ተከናወነ

Sydney candlelight vigil. በሊቢያ በደቡብ አፍሪካና የመን ለተገደሉ ወገኖቻችን በሲድኒ የሻማ ማብራት ሥነሥርዓት ተከናወነ

Sydney candlelight vigil. በሊቢያ በደቡብ አፍሪካና የመን ለተገደሉ ወገኖቻችን በሲድኒ የሻማ ማብራት ሥነሥርዓት ተከናወነ

Sydney candlelight vigil. በሊቢያ በደቡብ አፍሪካና የመን ለተገደሉ ወገኖቻችን በሲድኒ የሻማ ማብራት ሥነሥርዓት ተከናወነ

Sydney candlelight vigil. በሊቢያ በደቡብ አፍሪካና የመን ለተገደሉ ወገኖቻችን በሲድኒ የሻማ ማብራት ሥነሥርዓት ተከናወነ

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!