(ሪፖርታዥ)

Nine Killed in Somalia After Firing at Airport Ethiopia Zare (ቅዳሜ መስከረም ፲፯ /17 ቀን ፳፻፩/2001 ዓ.ም. September 27, 2008)፦ ሶማሊያ በድህነት እና በአክራሪ ጽንፈኞች ስር ሆና ያልተሳኩ የሠላም ስምምነቶችን እየተፈራረመች ወደ 20 ዓመታት አካባቢ አሳልፋለች።

 

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የምዕራባውያን ድጋፍ ያለውን የሶማሊያ የሽግግር መንግሥት በመደገፉና እስላማዊ ጽንፈኛ ቡድኖችን በመምታቱ፣ ለጊዜው በሀገሪቱ ሠላም የሰፈነ ቢመስልም፣ ህዝቡ እስካሁን ድረስ የኢትዮጵያን ወታደሮች የሚመለከተው እንደ ወራሪዎች ነው።

 

በሰሜን ካሮሊና የዴቪድሰን ኮሌጅ የሶማሊያ ኤክስፐርት ሚስተር ኬን ሜንካሁስ እንደሚገልፁት በሶማሊያ ሲፈጠሩ ለነበሩት ግጭቶችና ብጥብጦች ከስሩ መፍትሔ ለመስጠት አልተቻለም።

 

በአሁኑ ወቅት በሶማሊያ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የጅምላ ጥቃት እየተሰነዘረ ነው የሚሉት ሚስተር ኬን፣ የኢትዮጵያ ወታደሮች ከሶማሊያ የመልቀቃቸው ጉዳይ የሽግግር መንግሥቱና የተቃዋሚ ቡድኖች ያለመግባባት ምክንያት እየኾነ መምጣቱን ይናገራሉ።

 

በያዝነው ሣምንት እንኳ የኢትዮጵያን ወታደሮች የሶማሊያ ቆይታ የሚቃወሙት እስላማዊ ታጣቂዎች አዲስ ጥቃት ሰንዝረው በትንሹ 30 ሰዎች ተገድለዋል። በርካቶችም ከቀያቸው መልቀቅ ጀምረዋል።

 

ታጣቂዎች የአፍሪካ ሕብረት ሠላም አስከባሪ አባላት በሆኑት የዩጋንዳ ወታደሮች ላይ ጥቃት ሰንዝረው በትንሹ 8 ሠላማዊ ሰዎች ሞተዋል። በታጣቂዎች የሞርታር ጥቃት ከተገደሉት መካከል የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ ስድስት ሰዎች እንደሚገኙበት ታውቋል።

 

እስላማዊ ታጣቂዎች በሞቃዲሾ በሚገኝ ባከራ በተባለ የገበያ ሥፍራ ላይ ተኩስ ከፍተው ከ30 በላይ ሰዎች መግደላቸውም በወሩ ከተፈፀሙት ጥቃቶች ሁሉ እጅግ የከፋ ተብሏል። የአፍሪካ ሕብረት ሠላም አስከባሪ ጦር ቃል አቀባይ ሜጀር ባሆኩ ባሪጌ ግን በሠላም አስከባሪው ላይ የከፋ ጉዳት አለመድረሱን አስተባብለዋል።

 

የዩጋንዳ ሠላም አስከባሪዎች የሽግግር መንግሥቱን ከሚደግፉት የኢትዮጵያ ወታደሮች ይልቅ በሶማሊያውያን ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነት እንዳላቸው የሚታወቅ ሲሆን፣ ታጣቂዎች ጥቃት ከሰነዘሩ በኋላ ሠላም አስከባሪዎቹ በታንክና በከባድ መሣሪያ የታገዘ የአፀፋ እርምጃ መውሰዳቸው በነዋሪዎቹ ዘንድ ቁጣ ቀስቅሷል።

 

የቢቢሲ ጋዜጠኛ ከሞቃዲሾ እንደዘገበው፣ ታጣቂዎቹ ቀደም ባሉት ጊዜያት ጥቃት ከሰነዘሩ በኋላ ይሰወሩ ነበር፤ አሁን ግን የታክቲክ ለውጥ በማድረግ ፊት ለፊት መታኰስ መጀመራቸውን ገልጿል።

 

በዚህ ሣምንት ታጣቂዎች በሰነዘሩት ጥቃት፣ የአፍሪካ ሕብረት ሠላም አስከባሪዎች የማዘዣ ጣቢያ (Base) የጥቃት ዒላማ የነበረ ሲሆን፣ አካባቢው የሞቃዲሾን ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ከፕሬዝዳንቱ ቤተመንግሥት ጋር የሚያገናኝ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያለው አካባቢ መሆኑ ታውቋል።

 

ከጥቃቱ በኋላም ለሊቱን በሙሉ ከባድ የተኩስ ልውውጥ እንደተደመጠና ለቀናት ያለ እንቅልፍ ማደራቸውን የዓይን እማኞች ገልፀዋል።

 

K4 በተባለው ለአየር ማረፊያው ቅርብ በሆነው አካባቢ የተፈፀመው የታጣቂዎች የሞርታር ጥቃት፣ የአንድ ቤተሰብ አባላትን ብቻ ሳይሆን እነርሱን ሊረዱ የመጡት ሁለት ጎረቤቶቻቸውን መግደሉ የሞቃዲሾን ነዋሪዎች አስቆጥቷል።

 

ጥቃቱ የተሰነዘረው በጅቡቲ ሊካሄድ የነበረው የሠላም ውይይት በድጋሚ መዘግየቱን ተከትሎ መሆኑን ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ ወገኖች እየገለፁ ነው። የሠላም ውይይቱ የዘገየውም የመንግሥትና የታጣቂ ቡድኖቹ ተወካዮች፣ የኢትዮጵያ ወታደሮች ከሶማሊያ ምድር በሚለቁበት ሁኔታ ላይ ባለመግባባታቸው ነው።

 

የአሜሪካ የቀድሞ ዲፕሎማት የነበሩትና በአሁኑ ወቅት በጆርጅ ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምሩት ሚስተር ዴቪድ ቫን እንደሚሉት፣ አልሸባብ የተባለው ጽንፈኛ ቡድን የኢትዮጵያ ወታደሮች ከሶማሊያ እንዲወጡ ለማድረግ የተቻለውን ሁሉ እያደረገ ነው። ለዚህ ማሳያ አድርገው የሚጠቅሱት ደግሞ የኢትዮጵያ ወታደሮች በሚገኙበት አካባቢ አልሸባብ በደፈጣ የሚሰነዝረውን ጥቃት ነው።

 

አንዳንድ ሱማሊያውያን ደግሞ አሁን በሀገሪቱ ላለው ችግር በአጭር ጊዜ መፍትሔ መስጠት ይከብዳል፤ በመሆኑም ችግሩን ጊዜ፣ ትዕግስትና መግባባት ብቻ እንደሚፈታው ይናገራሉ።

 

ሌሎች ደግሞ ለሶማሊያ ቀውስ መፍትሔ የሚያስገኘው የተሳካ ድርድር ነው ይላሉ። ይሁን እንጂ ድርድር ለማካሄድ የኢትዮጵያ ወታደሮች በዚያ መቆየት እንቅፋት እየሆነ ነው። በመሆኑም በአስቸኳይ የኢትዮጵያን ወታደሮች ከሶማሊያ በማስወጣት ለሀገሪቱ አስቸኳይ መፍትሔ መፈለግ እንደሚገባ በርካቶች ያምናሉ።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!