በማግነስ ፍራንክሊን

ሰዎች በአንድ አካባቢ መሥፈር የጀመሩት የወንዝ ተፋሰሶችን ተከትለው ነው። በዋነኝነትም ወንዞች ለሠፈራ ቁልፍ ሚና ነበራቸው፤ ነገር ግን ከንግድ ተቋማት ጋር ሲተሳሰሩ ምን ይፈጠራል?

 

ዝናባማ ወቅት የተገባደደበት ጊዜ ሲሆን ዓለሙ መንግሥቱ ከአዲስ አበባ ወጣ ብሎ በሚገኘው በአቃቂ አካባቢ የእርሻ መሬቱን ለቀጣይ እርሻ ያዘጋጃል። ይሁን እንጂ እስካሁን ማረስ አልጀመረም። ምክንያቱም ላለፉት ሦስት ወራት በጐርፍ መጥተው፣ የእርሻ ማሳውን የሸፈኑትን የፕላስቲክ ፌስታሎች፣ ጫማዎች፣ ጐማዎችና ሌሎች ጥራጊዎች ይለቃቅማል። የዓለሙን እርሻ አደጋ ላይ የሚጥለው የቆሻሻ ጥርቅሙ ብቻ አይደለም። በጐርፍ አማካይነት የእርሻ መስኩ ላይ የወደቁት ከባድ ብረቶችና መርዛማ ኬሚካሎችም ጭምር እንጂ። በነዚህ መርዛማ ኬሚካሎች ነው እንግዲህ አትክልት የሚያመርተው፤ የአዲስ አበባ ገበያዎችን የሞሉትም በዚህ ዓይነት መንገድ በመርዛማ ዝቃጭ በተበከለው በአቃቂ ወንዝና ገባሮቹ የተመረቱ አትክልት ናቸው።

 

Fragile earth: a farmer removes river waste from his land in an effort to encourage crops to grow. Photograph: Guy Walder/Polaris

በበርካታ የዓለማችን ክፍሎች እንደሚታየው፣ የአቃቂ ወንዝ በርካታ ጉዞ ተጉዞ አይደለም ወደ ከተማዋ እንብርት የሚዘልቀው። ከከተማዋ ወጣ ብሎ ከሚገኝ ከፍታ ሥፍራ የሚነሳው የአቃቂ ወንዝ ረጅም ርቀት አይጓዝም፤ ወንዙ ከከተማዋ ወጥቶ ሲጓዝ ያልተበከለ ቢሆንም በጉዞው መርዛማ ዝቃጭ ተሸክሞ ይሄዳል። የሚበክለውም የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆን በወንዙ የታችኛው ክፍል የሚገኙ ተጠቃሚ ኅብረተሰቦችንም ጭምር ነው። ወንዙ እያደረሰ ላለው ጉዳት አንድን ወገን ተጠያቂ ማድረግ አይቻልም፤ ችግሩ ውስብስብ ነውና።

 

በአዲስ አበባ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች፣ ተረፈ ምርታቸውን በቀጥታ የሚለቁት ወደ ወንዞች ነው። ከተማዋ አንዳንድ አካባቢዎች ሠገራ፣ የፕላስቲክ ከረጢቶች፣ ያለቁ ነጠላ ጫማዎች፣ የቤት ጥራጊዎች ሁሉ የወንዙን መውረጃዎች ተከትለው ይጓዛሉ። መንግሥት ግን በራሪ ወረቀት በማሠራጨት የህዝቡን ግንዛቤ በማዳበር ለውጥ የማምጣት ዕቅድ አለው፣ ዕቅዱ ከችግሩ ባህርይ አንፃር ቀድሞ የመጣ አይደለም እንጂ።

 

በአቃቂ ወንዝ የሚታየው ብክለት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። ማንነታቸው እንዳይገለጽ የሚፈልጉ የመንግሥት ምንጮች እንደሚገልፁት፣ የከተማዋ የፍሳሽ ማከሚያ ከዚሁ ወንዝ ጋር የተያያዘ ነው። በዚህ ወንዝ የሚታከመው ውሃ የከተማዋን 5 በመቶ ቤተሰቦች ፍላጐት ያሟላል። ወደ ውሃ ማከሚያው ከሚገባው ውሃ ይልቅ ታክሞ የሚለቀቀው ውሃ መርዛማ እንደሆነም ነው የሚገልፁት። የአቃቂ ወንዝ ብክለት በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ላይ ቀጥተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው። በወንዙ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች እንደሚገልፀት ደረቅ የበጋ ወራት ሲመጣ፣ ወንዙ መጥፎ ሽታ ያላቸውን ዝቃጨች አጥቦ መጓዝ አይችልም፤ የወንዙን ወለል እያቀለመ፣ የጥራጊውን መጥፎ ነገር እያራገፈና የአካባቢውን አየር እየበከለ ይነጉዳል።

 

መንግሥት የአቃቂ ወንዝ ከሚደርስበት ጉዳት ለመታደግ የሚያስችለውን ጥሩ የሕግ ማዕቀፍ አዘጋጅቷል፤ ወንዙን ለመታደግ የተዘጋጀው ፖሊሲውም በለንደን የታሜስ ወንዝ ወይም በፓሪስ የሴይኒ ወንዝን ከጥፋት ለመታደግ ከተዘጋጁት ፖሊሲዎች የተሻለ እንጂ የከፋ አይደለም። ሌላው የሕግ ማስፈፀም ጉዳይ ነው፤ የኢትዮጵያ ፌደራል አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን እንደሚለው አሁን ያሉትን ሕጐች በሥራ ላይ ለማዋል በቂ የሰው ኃይልና ሀብት የለውም። ለምሳሌ በኢትዮጵያ ስስ ፌስታል እንዳይመረት የሚከለክል ሕግ ቢወጣም፣ በዓለሙ መንግሥቱና በሌሎችም የእርሻ መሬቶች ላይ የሚታዩት ስስ ፌስታሎች ሕጉ ቢኖርም አፈፃፀሙ ውጤታማ አለመሆኑን ያሳያሉ።

 

በኢትዮጵያ በብክለት በኩል የሚጠቀሱት ኢንዱስትሪዎች ሲሆኑ፣ የአንበሳውን ድርሻ የሚይዙት የቆዳ ፋብሪካዎች ናቸው። የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣንም ተቋማቱ ንፁኅ ቴክኖሎጂ እንዲጠቀሙ የ5 ዓመት ጊዜ ገደብ ሰጥቷቸዋል። ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የባለሥልጣኑ አንድ የሥራ ኃላፊ እንደሚገልጹት፣ የቆዳ ፋብሪካዎቹና የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በብክለቱ በኩል በቀዳሚነት ይሰለፋሉ። ነገር ግን ልቅ የሆነ ሕግ ስላለ ፋብሪካዎቹን መዝጋት ችግር ነው፤ በመሆኑም ፋብሪካዎቹን ከመዝጋት ይልቅ የብክለት ቁጥጥር ዘዴ ተግባራዊ እንዲያደርጉ ማድረግ አማራጭ ነው ይላሉ። የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን በሚቀርብለት ውጤት ላይ ከመስማማት በዘለለ የሚያደርገው ነገር የለም። የሰልፈሪክ አሲድ ሽታ ከፋብሪካዎች ከወጣ በኋላ ሊቋቋሙት በማይቻል መልኩ በርካታ ሜትሮች የሚጓዝ ሲሆን፣ በወንዙ አካባቢ የሚገኙ አለቶች፣ አትክልቶችና የውሃ ቧንቧዎች ሳይቀሩ በወፍራም ዘይታማና በጥቁር ዝልግልግ ነገር እየተሸፈኑ ነው።

 

ብሩክ የተባለ አንድ የ15 ዓመት ሕፃን እንደተናገረው፣ ወንዙ ከሚያደርሰው የአካባቢ ብክለት ይልቅ ሽታው የከፋ ነው። በረግራጋማና ከፋብሪካ በስተጀርባ የሚገኝ መንደር ያደገው ብሩክ፣ ሽታው በሚጠነክርበት ጊዜ ምግብ ለመመገብ እንደሚቸገሩ ቢገልጽም፤ እስካሁን ድረስ የአካባቢው ሕፃናት በወንዙ ከመዋኘት ውጪ ምንም አማራጭ የላቸውም።

 

ለኢንዱስትሪዎች ትኩረት መስጠት፣ ለችግሩ መፍትሔ ለመፈለግ ግማሽ መንገድ እንደ መጓዝ ይቆጠራል። ከሰዎች የሚወጡ እንደ ዓይነምድርና ጥራጊ ያሉት ቆሻሻዎች፣ የአዲስ አበባ ጐዳናዎችና የአቃቂ ወንዝን እየበከሉት ነው። የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የንግድ ተቋማት ለአካባቢ ጥበቃ ሕግ ተገዢ እንዲሆኑ ለማድረግ አልቻለም።

 

በርካታ ድሃ ማኅበረሰብ በሚበዛበት አዲስ አበባ፣ ለአንድ ቤተሰብ በቀን 7 ብር ማግኘት እንግዳ አይደለም፤ ይሁን እንጂ መፀዳጃ ቤት እንደማግኘት አይከብድም። ውሃ የሚፈስበት ሽንት ቤት ማግኘት ደግሞ ለድርቅ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የሚተገበር አይመስልም። ንፁኅ ውሃ ማግኘት እንኳ ውድ ነውና። ውሃ ያላቸው መፀዳጃ ቤቶች ከ15 በመቶ አይዘሉም። እነዚህ መፀዳጃ ቤቶች በቅርብ ጊዜያት ስለሚሞሉ ለማስመጠጥ ይከብዳል። ከዚህ በተጨማሪ አንዳንዶች ሽንት ቤት ለመገንባት አቅሙ የሌላቸው ሲሆኑ፣ የተቀሩት ደግሞ በቂ ቦታ አይኖራቸውም። ወደ 30 በመቶ የሚሆኑት የከተማ ነዎሪዎች መፀዳጃ ቤት የሚጠቀሙበት አማራጭ ስለሌላቸው በየጥጋጥጉ ይፀዳዳሉ።

 

“በሕይወቴ ሙሉ ሽንት ቤት ተጠቅሜ አላውቅም” የምትለዋ በማዕከላዊ አዲስ አበባ፣ በአቃቂ ዳርቻ የምትኖረዋ ፎዚ ያሲን፣ ሽንት ቤት መሄድ ሲኖርባት ወደ ወንዝ እንደምትሄድ ትናገራለች። ምሽት ሲሆን ወንዙ ስለሚያስፈራም ከባለቤቷ ጋር ሆና ወደ ወንዙ እንደምትሄድና ልጇም ብትሆን ወደ ወንዙ በመሄድ እንደምትፀዳዳ ትገልፃለች።

 

የሽንት ቤት አለመኖር የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ ነው። ምክንያቱም በርካታ ሰዎች ስለሽንት መነጋገር አይወዱም። የብሪታኒያው የረድዔት ድርጅት ወተር ኤይድ እንደሚለው፣ ኢትዮጵያ በዓለም ዝቅተኛ የንፁኅ መጠጥ ውሃ ሽፋንና የንፅኅና አገልግሎት ካላቸው ሀገራት መካከል አንዷ ናት። ከህዝቦቿ ንፁኅ መጠጥ ውሃ የሚያገኘው 1/4ኛው ብቻ ነው። በቂ የንፅኅና አገልግሎት የሚያገኘው ደግሞ 1/6ኛው ነው። በዚህ የተነሳ ከውሃ ጋር የተያያዙ በሽታዎች በብዛት የሚዘወተሩ ሲሆን፣ የጤና አገልግሎቱም ውስን ነው።

 

የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት፣ የውሃ ማከሚያ ተቋማትና የከተማዋን አጠቃላይ የፍሳሽ ሥርዓት የሚያሳይ ካርታ አዘጋጅቷል። ካርታው ግን ከወረቀት የዘለለ አይደለም። ካርታው እንደሚገልፀው 10 በመቶ ቤተሰቦች የፍሳሽ ማስወገጃ ያላቸው ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ግማሾቹ ብቻ ናቸው በትክክል ከከተማዋ የፍሳሽ ማስወገጃ ጋር የተገናኙት። በወንዝ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ወንዝን የሚመለከቱት እንደ ቆሻሻ ማስወገጃ ነው። ቆሻሻ ሲጥሉም ምንም ፀፀት ወይም የጥፋት ስሜት አይሰማቸውም። በአቃቂ ወንዝ የተፈጠረውም ይኼው ነው። ዓለሙና ሌሎች ሰዎች የአቃቂ ወንዝ የሰበሰበውን ፌስታል ከማሳቸው ላይ በማንሳት ሲያፀዱ፣ ቆሻሻ ፌስታሉን ወደ ወንዙ በመወርወር ነበር።


ምንጭዘ ጋርዲያን

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!