በቅርቡ ጥናት ያደረጉ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ በአዲስ አበባና በሌሎች የሀገሪቱ ዋና ዋና ከተሞች ድህነት መባባሱን ነው። በተለይም በመዲናዋ አዲስ አበባ የድህነት ገጽታው በከፍተኛ ፍጥነት ማሻቀቡን ከሚታየውና ከሚሰማው ነገር መረዳት ይቻላል።

 

የማኅበራዊ ጥናት መድረክ ተመራማሪ የሆኑት ወ/ት ነፃነት ተክለኃይማኖትም ባለፈው ሣምንት በአራዳ፣ በልደታና በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተሞች የሚታየውን የድህነት ገፅታ ይፋ ካደረጉ በኋላ፣ የእንቢልታ ዘጋቢዎች ዓይናለም ፈለቀና አጥናፉ አለማየሁ ድህነት በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ያለውን ገጽታ በመንደርደርያነት እንደሚከተለው አቅርበውታል፦

 

በተጣበበውና የውሃ መውረጃ ቦይ ያህል በተቀደደው የውስጥ ለውስጥ መንገድ አቆራርጠው ወደ ውስጥ ሲዘልቁ፣ ተመሳሳይ ቅርጽ ያላቸው የጭቃ ቤቶች ተሰግስገዋል። በራቸው ደጃፍ ላይ ቁጢጥ ብለው፣ ከጎረቤታቸው ጋር ወግ የያዙት ወ/ሮ ቀለሟ መንግሥቱ ገርበብ ያለችውን የቆርቆሮ መዝጊያቸውን ገፋ አድርገው ወደ ውስጥ ይዘውን ዘለቁ።

 

በቆርኪ ክዳን አጋዥነት ዙሪያውን በምስማር የተመታውና መስኮቱን የሸፈነው ላስቲክ፣ ለቤቱ ብርሃን ሰጥቶታል። ጨለምለም ያለችውና ከጭቃ የተሠራችው ከሁለት በሦስት የማትበልጠዋ ጠባብ “ቤት” እንደ ገጠር ጎጆ የጭቃ መደብ ተሠርቶባታል።

 

በአንድ ጥግ በኩል ከሳጠራ የተሠራ አግዳሚ መቀመጫና፣ ከተለያዩ ጣውላዎች በርብራብ የተሠራው ሰማያዊ የእንጨት ዕቃ ማስቀመጫ ሳጥን አናቱ ላይ፣ የብረት ሣጥን ተደርቦበታል። ተላልጦ መርገፍ በጀመረው ግድግዳ ላይ ከየመጽሔቶቹና ጋዜጣዎች የተለቃቀሙ የተለያዩ አርቲስቶች ፎቶግራፎች ተለጥፏል።

 

ወ/ሮ ቀለሟ እንደነገሩ ጣራና ግርግዳ ካላትና፣ በወር ሰባት ብር በሚከፍሉት በዚህች ጠባብ ቤት መሳይ ውስጥ፣ በቅርቡ አባታቸው ከሞቱባቸው ዘጠኝ ልጆቻቸውና ከአንድ የልጅ ልጃቸው ጋር አብረው ይኖራሉ።

 

የመጀመሪያውና ወንዱ ልጃቸው የትና ምን እንደሚሠራ አያውቁም። በአቅም ማነስ ልጆቻቸውን በሚገባ ባለማስተማራቸው “የት ወጣችሁ? የት ገባችሁ? ምን እየሠራችሁ ነው? የማለት መብት የለኝም” ብለው ስለሚያስቡ ማንንም ምንም አይናገሩም።

 

እናም ልጆቻቸው እቤት ሲውሉ ስምምነት ስለሌላቸው፣ በአብዛኛው ሥራ እንዳለው ሰው በጠዋት ተነስተው ይወጣሉ፣ ማታ ተመልሰው ይመጣሉ።

 

በአነስተኛ ዕድሜ ክልል ላይ ያለው ወጣቱ ልጃቸው ፓርኪንግ ተቀጥሮ ይሠራል። የመጨረሻ ልጃቸው ትምህርቷን ከሰባተኛ ክፍል አቋርጣ፣ መንደር ውስጥ ከእኩዮቿ ጋር ትዞራለች።

 

በወ/ሮ ቀለሟ ቤት ጠዋት፣ ጠዋት የሚቀርብ ቁርስ የለም፤ ምናልባት የልጆቻቸው የትናንት አዋዋላቸው ጥሩ ከሆነና ዕድል ከቀናቸው፣ ከየኪሳቸው ለቃቅመው በሚያዋጧት ፍራንክ ሽልጦ፣ ዳቦ ወይም እንጀራ ገዝተው በሻይ አሊያም በውሃ ይመገባሉ።

 

ምሳ ተሠርቶ ወጉን ይዞ መብላት ፍፁም የሚታሰብ አይደለም። ከተገኘ ግን እቤት ያለ ሰው ይቃመሳል። በእራት ሰዓት ሁሉም የቤተሰቡ አባል ስለሚሰበሰብ በተደጋጋሚ ጥቁር እንጀራ በሽሮ ይመገባሉ፣ ከታጣም ሽልጧቸውን ተቃምሰው በውሃ ያወራርዳሉ።

 

ወ/ሮ ቀለሟን ሁሌም የሚያሳስባቸው መኝታቸው ነው። ከአምስተኛው ልጃቸው ወሊድ በኋላ የጀመራቸው የወገብ ሕመም ምቾት እንዲሰጡት ይወተውታቸዋል። እሳቸው ግን በአንዷ መደብ ላይ ተጣበው ከሴት ልጆቻቸው ጋር ይተኛሉ። ወንዶቹ ማታ ማታ በሚዘረጉት ሰማያዊ የላስቲክ ምንጣፍ ላይ፣ ንጣፉን አደላድለው ከሣቸው በስተቀር ሁሉም እያንኮራፉ ይተኛሉ።

 

ወ/ሮ ቀለሟ ሲመሽ የሚጠለሉበት ጣሪያና ግርግዳ ያለው ቤት፣ ሲነጋ ከፍተው የሚወጡት መዝጊያ፣ እንደምን አደራችሁ? የሚባባሉት ጎረቤት አላቸው። ነገር ግን እሳቸውም ሆኑ ልጆቻቸው ሲታመሙ የሚታከሙበት፣ ሲራቡ የሚመገቡበት ገንዘብ፣ ተገላብጠው የሚተኙበት መኝታ፣ ቡና አፍልተው የሚጠራሩበት ገንዘብ የሌላቸው የከተማ ደሀ ናቸው።

 

እንደሳቸውና ከሳቸው በባሰ የኑሮ አዘቅት ውስጥ ገብተው፤ ከመኖር ጋር ትግል የገጠሙ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር በርካታ ነው። በነዚህ የከተማ ድሆች ላይ በርካታ ጥናት የተደረገ ሲሆን፣ በቅርቡም በሦስት ክፍለ ከተሞች ላይ ጥናት ያደረጉት ወ/ት ነፃነት ተክለኃይማኖት አንዷ ናቸው።

 

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በኢኰኖሚክስ በመጀመሪያ ዲግሪ፣ በኋላም በጀርመን ሀገር ጆርጅ ኦገስት ዩኒቨርሲቲ (Socio-Economics of Rural Development) በማስተርስ የተመረቁት ወ/ት ነፃነት፤ በአሁኑ ወቅት በማኅበራዊ ጥናት መድረክ በተመራማሪነት እየሠሩ ይገኛሉ።

 

ወ/ት ነፃነት ኅዳር 18 ቀን 2000 ዓ.ም.፣ ማኅበራዊ ጥናት መድረክ ባዘጋጀውና ለግማሽ ቀን በተካሄደው የከተማ ድህነት ዓውደ ጥናት ላይ በአራዳ፣ በልደታና በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተሞች የድህነት ገጽታ ላይ ጥናት አቅርበው ነበር።

 

እንደ ወ/ት ነፃነት ድህነት በተለያየ መልኩ ይገለፃል። አንዳንዶች ገቢ ላይ በተመሠረተ ኢንዴክስ (አመልካቾች) ሲገልጹ፣ ሌሎች ደግሞ በገቢ ላይ የተመሠረተ መረጃ በበቂ ሁኔታ የድህነትን ገጽታ ሊያሳይ አይችልም ይላሉ። ኾኖም ድህነት ከገቢ ማነስ ብቻ ሳይሆን መሠረታዊ የሆኑና ለሰው ልጅ አስፈላጊ ነገሮች ለምሣሌ የጤና አገልግሎት አለማግኘት፣ የመኖሪያ ቤት ችግር፣ የትራንስፖርት፣ ንጹኅ የመጠጥ ውሃና ሌሎችንም ነገሮች ሊያካትት እንደሚችል ይጠቅሳሉ።

 

ወ/ት ነፃነት ድህነትን በአራዳ በአዲስ ከተማና በልደታ ክፍለ ከተሞች ማጥናት ለምን እንዳስፈለጋቸው ሲገልጹ በከተማዋ መሀለኛ ክፍል ስለሚገኙና፣ በአመሠራረታቸውም ረጅም ጊዜ ያስቆጠሩ መሆናቸው አንደኛው ምክንያት ነው። ብዙውን ጊዜም ረጅም ዕድሜ ያስቆጠሩና ወደ መሀል የሚገኙ የከተማ ክፍል በድህነት እንደሚጠቁ ይታሰባል። ከዚህ በተጨማሪም በእነዚህ ሦስት ክፍለ ከተሞች የሚኖረው ህዝብ፣ ከአጠቃላዩ የከተማ ህዝብ 44 በመቶውን ይይዛል። ምንም እንኳ እነኚህ ሦስት ክፍለ ከተሞች፣ ከሌሎች ክፍለ ከተሞች ጋር ሲወዳደሩ በቆዳ ስፋታቸው አነስተኛ ቢሆኑም፣ ህዝብ ተጨናንቆ የሚኖርባቸው እንደሆኑ ጥናት አቅራቢዋ ተናግረዋል።

 

“እ.አ.አ. በ2008 ላይ 44 በመቶ የሆነው የነኚህ ሦስት ክፍለ ከተሞች ነዋሪ፣ በድህነት ውስጥ የሚገኝ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል” የሚሉት ወ/ት ነፃነት፣ 53 በመቶ የሚሆነው የልደታ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ከድህነት ወለል በታች የሚገኝ ነው። የተሻለ ገጽታ የሚታየው በአራዳ ክፍለ ከተማ ሲሆን፣ 29 በመቶ ነዋሪ ነው በድህነት ውስጥ የሚገኘው። በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ደግሞ 47 በመቶ የሚሆነው የፍጆታ ወጪው የድህነት ወለሉን መድረስ ያልቻለ እንደሆነ አብራርተዋል።

 

“ከድህነት ወለል በታች” ስለሚባልበት ትርጓሜ ሲያስረዱም፤ ሰዎችን “ድሀ” ናቸው ወይም አይደሉም የሚለየውን ለመለየት በገቢ ላይ ወይም በፍጆታ ወጪ ላይ የተመሠረተ የድህነት ወለል አለ። ይሄ ማለት የገቢያቸው ወይም የፍጆታ ወጪያቸው መጠን ከተመሠረተው የወለል ደረጃ የሚያንስ ከሆነ ድሀ፣ ከወለሉ የሚበልጥ ከሆነ ደግሞ “ድሀ” አይደሉም ብለን መለየት ወይም መፈረጅ እንችላለን ይላሉ።

 

ተመራማሪዋ ለጥናቱ መነሻ የተጠቀሙት 300 ቤተሰቦች እንደሆኑና፣ መረጃውን ለመሰብሰብ በሄዱባቸው አጋጣሚ በተለይ የአረጋውያኑ ሁኔታ እንዳሳሰባቸው ተናግረዋል።

 

ወ/ት ነፃነት በጥናታቸው ሴቶች ከወንዶች በበለጠ በድህነት እንደሚጠቁ ያመለከቱበት ሁኔታ አለ። እናም ደሀ ከሆኑት ውስጥ 51.1 ከመቶ ሴቶች ሲሆኑ፣ 48.8 ከመቶ ደግሞ ወንዶች መሆናቸው ታውቋል። በጣም ጥቂት የሆኑ የሴት የቤተሰብ ኃላፊዎች በግል ወይም በመንግሥት ሥራ ላይ የተሰማሩ ሲሆን፣ አብዛኛው በእማወራ የሚመራ ቤተሰብ ግን ዝቅተኛ ገቢ በሚያስገኙ የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ ማለትም እንጀራ፣ ዳቦ፣ ከሰል፣ ጠላ፣ አረቄ እና መሰል ሥራዎች ላይ መሠማራታቸው ተጠቅሷል። ከዚህ በተጨማሪም በዚህ ጥናት እንደተመለከተው እነዚህ ሴቶች አብዛኞቹ ከትዳር አጋሮቻቸው ጋር የተለያዩ ወይም ባሎቻቸው የሞቱባቸው ናቸው።

 

በነዚሁ ክፍለ ከተሞች የሚገኙ መኖሪያ ቤቶችን ሁኔታ በሚመለከትም፣ 55 በመቶ የሚሆነው ነዋሪ ዝቅተኛ ኪራይ በሚከፈልባቸው የቀበሌ ቤቶች ውስጥ የሚኖር ሲሆን፣ 27 በመቶ የሚሆኑት ቤቱ የግላቸው ነው። በማናቸውም የኪራይ ቤቶች ላይ የሚከፍሉት አማካኝ ወርኃዊ የኪራይ መጠን ከ19 ብር ባይበልጥም፣ ተከራዮች ባለው የገበያ ዋጋ የሚከፍሉ ቢሆን የኪራዩ መጠን ወደ 358 ብር ከፍ ይልባቸው እንደነበረ በጥናቱ ተካቷል።

 

የቤቶቹ ግድግዳ ከእንጨትና ከጭቃ የተሠራ፣ ወለሉ አፈር ወይም በጣውላ የተሸፈነ፣ ጣራው ቆርቆሮ የለበሰ፣ የአማካኝ የቤቶቹ ስፋት 37 ካሬ ሜትር ቢሆንም 4 ካሬ ሜትር በሚሆን ቤትም ውስጥ የሚኖሩ እንደሚገኙ፣ በአብዛኛው አንድ ክፍል ቤት ለመኝታ፣ ለምግብ ማብሰያና ለመመገቢያ እንደሚያገለግል፤ በተለይም ብዙ የቤተሰብ አባላት ያላቸው በመኖሪያ ቤቶች ውስጥ ተጣበው እንደሚገኙና በአንዳንድ ቤተሰቦች ከ12 ሰዎች በላይ በአንድ ክፍል ውስጥ እንደሚኖሩ በጥናቱ ላይ ተካቷል።

 

ወ/ት ነፃነት የመፍትሔ ሃሳብ ሲያስቀምጡም፤ የድህነት ቅነሳ መርኀ-ግብር በሦስቱም ክፍለ ከተሞች በተለይም በልደታ ክፍለ ከተማ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚኖርበት አመልክተው፣ የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር አግባብነት ያላቸው የገንዘብ ፖሊሲዎችን መተግበር፣ የልማታዊ (Safty Nets) መርኀ-ግብር መዘርጋት፣ አነስተኛ የብድርና የኢንሹራንስ አገልግሎቶች መዘርጋት፣ የቤተሰብ ምጣኔ መርኀ-ግብርን ማጠናከር፣ የዝቅተኛ ዋጋ ቤቶች የልማት ሥራን ማጠናከር፣ የሰው ሀብት ልማትን (በተለይ ትምህርትን)፣ በመሠረታዊ ችሎታ ማዳበሪያ ሥልጠናዎች መስጠት፤ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት መሳተፍን ማበረታታት የ(Adult Literacy) መርኀ-ግብርን ማስፋፋት፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ማጠናከር እና የትምህርቱንም ጥራት መቆጣጠር፣ የመንግሥት የሕክምና ተቋማትን ማስፋፋት እና የደሃው የኅብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ መሆኑን ማረጋገጥ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!