ኬንያውያን አትሌቶች ኢትዮጵያውያኑን በልጠው ተገኝተዋል

Meseret Defar, Berlin 22 Aug 2009, Bronz medal (AP)

Ethiopia Zare (ቅዳሜ ነሐሴ 16 ቀን 2001 ዓ.ም. August 22, 2009)፦ በዛሬው ዕለት (ቅዳሜ ነሐሴ 16) ስምንተኛ ቀኑን በያዘው በበርሊኑ 12ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በወንዶች ማራቶን 3ኛ፣ 4ኛ እና 15ኛ ሲወጡ፣ በሴቶች 5000 ሜትር ደግሞ 3ኛ፣ 4ኛ እና 5ኛ ወጥተዋል። የዛሬውን ሁለት የነኀስ ሜዳሊያ ለኢትዮጵያ ያስገኙት አትሌት ፀጋዬ ከበደ በማራቶን፣ አትሌት መሰረት ደፋር ደግሞ በ5000 ሜትር ነው።

 

በወንዶች ማራቶኑም ሆነ በሴቶች 5000 ሜትር ኢትዮጵያውያኑን በማሸነፍ አንደኛ እና ሁለተኛ የወጡት ኬንያውያን አትሌቶች ናቸው። ምንም እንኳን ውድድሮቹ ፉክክር የታየባቸው ቢሆንም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከዚህ የ12ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ጥሩ ልምድ እንደሚቀስሙ ይጠበቃል።

 

Tsegaye Kebede, marathon, Berlin 22 Aug 2009, Bronz medal (Reuters)

ዛሬ ቅዳሜ ነሐሴ 16 ቀን 2001 ዓ.ም. ጠዋት ላይ በተካሄደው የወንዶች ማራቶን አትሌት ፀጋዬ ከበደ ሦስተኛ በመውጣት የነኀሴ ሜዳሊያ ሲያገኝ፣ አትሌት የማነ ፀጋዬ አራተኛ እንዲሁም አትሌት ደጀኔ ይርዳው 15ኛ ወጥቷል። በማራቶኑ ከተሳተፉት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ውስጥ ደረጀ ጨሜሳ እና ድሪባ መርጋ ውድድሩን ሳይጨርሱ አቋርጠው ወጥተዋል።

 

Meseret Defar, Berlin 12th iaaf, 3rd in 5000 m (G)

በዛሬው ዕለት ማምሻውን በሴቶች 5000 ሜትር በተደረገው የፍፃሜ ውድድር አትሌት መሠረት ደፋር ውድድሩን በ14 ደቂቃ 58፡41 ሰከንድ በመጨረስ ሦስተኛ ወጥታ የነኀስ ሜዳሊያ ያገኘች ሲሆን፣ አትሌት ስንታየሁ እጅጉ በ15 ደቂቃ ከ3፡38 ሰከንድ በመጨረስ አራተኛ፣ አትሌት መሰለች መልካሙ በ15 ደቂቃ ከ3፡72 ሰከንድ ውድድሩን በመጨረስ አምስተኛ፣ እንዲሁም አትሌት ገንዘብ ዲባባ በ15 ደቂቃ ከ11፡12 ሰከንድ ስምንተኛ ወጥታለች።

 

ኬንያውያኑ አትሌቶች ቪቪያን ቼሩዮት በ14 ደቂቃ ከ57፡97 ሰከንድ አንደኛ በመውጣት የወርቅ ሜዳሊያ፣ አትሌት ሲልቪያ ጄቢዮት ኪበት ደግሞ በ14 ደቂቃ ከ58፡33 ሰከንድ ውድድሩን በሁለተኝነት በመጨረስ የብር ሜዳሊያ አግኝተዋል።

 

እሁድ ነሐሴ 17 ቀን 2001 ዓ.ም. (August 23, 2009) የሚደረጉት ውድድሮች

በነገው ዕለት (እሁድ ነሐሴ 17 ቀን 2001 ዓ.ም.) በሚካሄደው የ12ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሴቶች ማራቶን፣ በወንዶች 1500 ሜትር እና በወንዶች 5000 ሜትር ይሳተፋሉ።

 

በሴቶች ማራቶን

ኢትዮጵያውን ወክለው እሁድ በበርሊን ሰዓት አቆጣጠር 11፡15 ኤ.ኤም. ላይ በሴቶች ማራቶን የሚሳተፉት አትሌቶች አምስት ናቸው። እነሱም አሰለፈች መርጊያ፣ ድሬ ቱነ፣ ሩቤ ጉታ፣ አፀደ ባይሳ እንዲሁም ብዙነሽ በቀለ መሆናቸው ታውቋል።

 

በሴቶች 1500 ሜትር

በሴቶች 1500 ሜትር ርቀት አትሌት ቃልኪዳን ገዛኸን እና አትሌት ገለቴ ቡርቃ የሚሳተፉ ሲሆን፣ በውድድሩ ላይ ኢትዮጵያውያኖቹን አትሌቶች ጨምሮ 12 ተወዳዳሪዎች በዚህ የፍፃሜ ውድድር ላይ እንደሚሳተፉ ታውቋል። ውድድሩ በበርሊን ሰዓት አቆጣጠር ከሰዓት በኋላ 5 ፒ.ኤም. (17፡00) ላይ ይጀመራል። በዚህ ርቀት የዓለም ክብረወሰን በቻይናዊዋ አትሌት ኩ ዩክሲያ ቤጂንግ ላይ እ.ኤ.አ. ሴፕቴምበር 11 ቀን 1993 የተመዘገበው 3 ደቂቃ ከ50፡46 ሰከንድ መሆኑ ይታወቃል።

 

የወንዶች 5000 ሜትር

የወንዶች 5000 ሜትር ክብረወሰን የተመዘገበው ሜይ 31 ቀን 2004 እ.ኤ.አ. በአትሌት ቀነኒሳ በቀለ ኔዘርላንድ ላይ የተመዘገበው 12 ደቂቃ ከ37፡35 ሰከንድ መሆኑ ይታወቃል። በእሁዱ ውድድር ላይ ከአትሌት ቀነኒሳ በቀለ ጋር ኢትዮጵያን ወክሎ የሚሳተፈው አትሌት ዓሊ አብዶሽ መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል። ይህ ውድድር በተለይም በአፍሪካውን አትሌቶች መካከል ከፍተኛ ፉክክር የሚታይበት ሲሆን፣ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ሁለተኛውን የወርቅ ሜዳሊያ በ12ኛው የበርሊኑ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ያስመዘግባል ተብሎ ይጠበቃል። ውድድሩ በበርሊን ሰዓት አቆጣጠር ከሰዓት በኋላ 4፡25 ፒ.ኤም. (16፡25) ላይ ይጀምራል።

 

በቅዳሜው ምሽት ኢትዮጵያ በሜዳሊያ ሠንጠረዥ 10ኛ ላይ የምትገኝ ሲሆን፣ ጠቅላላ ያስመዘገበቻቸው ሜዳሊያዎች ስድስት ናቸው። አንድ የወርቅ፣ ሁለት የብር እና ሦስት የነኀስ። ኬንያ ደግሞ በ10 ሜዳሊያዎች (አራት የወርቅ፣ አራት የብር እና ሁለት የነኀስ) የሦስተኝነት ደረጃን ስትይዝ፤ ከአፍሪካ አንደኛ ለመሆን በቅታለች ኢትዮጵያ ደግሞ ከአፍሪካ ሀገሮች ሁለተኛ ላይ ትገኛለች።

 

በነጥብ ሠንጠረዡ ደግሞ ኬንያ በ109 ነጥብ አራተኛ፤ ኢትዮጵያ በ71 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ቅዳሜ ማምሻውን እንደሚገኙ ለማወቅ ችለናል።

 

እሁድ በሚደረጉት በእነዚህ ሦስት ውድድሮች ኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ ለኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድልን ትመኛለች።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ