አትሌት ገለቴ ተገፍትራ በመውደቋ ሜዳሊያ አጣች
ገፍታሪዋ የወርቅ ሜዳሊያውን ተነጠቀች
Ethiopia Zare (እሁድ ነሐሴ 17 ቀን 2001 ዓ.ም. August 23, 2009)፦ በሴቶች 1500 ሜትር ርቀት ውድድሩን እስከ 1200 ሜትር ስትመራ የነበረችው አትሌት ገለቴ ቡርቃ በስፔይኗ አትሌት ናታሊያ ሮድሪከዝ ተገፍትራ መሬት ላይ በመውደቅዋ ውድድሩን ሳታሸንፍ ቀርታለች። ናታሊያ ውድድሩን በአንደኝነት ብትጨርስም ዳኖቹ አሸናፊነትዋን ውድቅ በማድረግ የወርቅ ሜዳሊያውን እንዳታገኝ አድርገዋል።
አትሌት ገለቴ ዛሬ እሁድ ነሐሴ 17 ቀን 2001 ዓ.ም. በተደረገው በዚህ ውድድር አሸናፊ ትሆናለች ተብሎ ትልቅ ግምት ተሰጥቷት ነበር። አትሌቷ ስትመራ በነበረችው ውድድር ላይ ተገፍታ ብትውድቅም፤ ከወደቀችበት ተነስታ ውድድሩን በ4 ደቂቃ ከ11፡21 ሰከንድ 11ኛ ሆና ለመጨረስ ተገድዳለች። ስፔናዊቷ አትሌት ውጤቷ ውድቅ በመደረጉ የአትሌት ገለቴ ውጤት 10ኛ ሆኗል። ሌላዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ቃልኪዳን ግዛኸኝ በ4 ደቂቃ ከ08፡81 ሰከንድ አስረኛ ሆና የጨረሰች ቢሆንም በተደረገው የውጤት ማስተካከያ ዘጠነኛ ሆናለች።
በቴሌቭዥን በቀጥታ ለመላው ዓለም ሲተላለፍ በነበረው በዚሁ ውድድር ላይ ስፔናዊትዋ አትሌት ናታሊያ አትሌት ገለቴን ገፍትራ የጣለቻት የሚመስል ቢሆንም፤ አትሌት ናታሊ ከውድድሩ በኋላ በሰጠችው ቃለምልልስ ላይ “ቀድማ የገፈተረችኝ ገለቴ ናት” ስትል ተደምጣለች።
አትሌት ናታሊያ ውድድሩን የጨረሰችው በ4 ደቂቃ ከ03፡36 ሰከንድ የነበረ ቢሆንም፤ ውጤቷ አይመዘገብላትም። በዳኞቹ ውሳኔ የውጤት ማስተካከያ መሠረት በ4 ደቂቃ ከ03፡74 ሰከንድ ሁለተኛ የገባችው በትውልድ ኢትዮጵያዊት የሆነችውና የባህሬኗ ማሪያም የሱፍ ጀማል የአንደኝነት ቦታውን በመያዝ የወርቅ ሜዳሊያውን አግኝታለች። በዚህ የውጤት ማስተካካያ መሠረት እንግሊዛዊቷ ሊሳ ዶብሪስኪ በ4 ደቂቃ ከ03፡75 ሰከንድ የብር ሜዳሊያ፣ አሜሪካዊቷ ሻኖን ሮበሪ በ4 ደቂቃ ከ04፡18 ሰከንድ የነኀስ ሜዳሊያ አግኝተዋል።
የ24 ዓመትዋ ወጣት አትሌት ማሪያም የሱፍ ጀማል በርካታ ኮከብ አትሌቶችን ባፈራችው አርሲ ውስጥ ክርስቲያን ከሆኑ ኦሮሞ ወላጆችዋ መስከረም 6 ቀን 1976 ዓ.ም. ሲሆን፣ መጠሪያ ስሟ (የቀድሞ) ዘነበች ቶላ ነበር። እ.ኤ.አ. 2004 የበጋ ኦሎምፒክ ውድድር ሟሟያ ሰዓቱን ብታስመዘግብም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በኦሎምፒኩ እንዳትሳተፍ ካደረጋት በኃላ ወደ ስዊዘርላንድ ከባለቤትዋ ጋር በመሄድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጥገኝነት ጠይቃለች።
ከትውልድ ሀገሯ ኢትዮጵያ ተሰድዳ ነዋሪነትዋን በስዊዘርላንድ ካደረገች በኋላ ለአሜሪካ፣ ለካናዳና ለፈረንሣይ ጥንድ ዜግነት አመልክታ በነበረበት ወቅት ነበር በባህሬይን ዓይን ውስጥ የገባቸው። ባህሬን በስፖርቱ ዓለም ምስሏን ለማሳደግ ባቀደችበት ወቅት አትሌቷ ስሟን ወደ ዐረብኛ በመቀየር እ.ኤ.አ. 2006 በኳታር ዶሃ ላይ በተደረገው የእስያ ውድድር ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ባህሬንን ወክላ ተወዳድራለች። ምንም እንኳን ስሟን እንድትቀይር ብትደረገም፤ የክርስትና ኃይማኖትዋን ግን እንድትቀይር በባህሬይን አልተገደደችም።
ጃፓን ኦሳካ ላይ በተደረገው 11ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናም በ1500 ሜትር አትሌት ማሪያም ለባህሬይን የወርቅ ሜዳሊያ አስገኝታለች። በዚህ በ12ኛውም የሻምፒዮና ውድድር ላይ በርቀቱ የወርቅ ሜዳሊያ አግኝታለች።
ዘጠነኛ ቀኑን የያዘው 12ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በዛሬው ዕለት ይጠናቀቃል።