Dr. Merera and Prof. BeyeneEthiopia Zare (ኀሙስ ነሐሴ 28 ቀን 2001 ዓ.ም. September 3, 2009)፦ በእንግሊዝ ኤምባሲ አግባቢነት መጪውን የ2002 ዓ.ም. የሀገር አቀፍ ምርጫን አስመልክቶ በተቃዋሚዎችና በገዥው ፓርቲ መካከል የተጀመረውን ስብሰባ መድረክ (መድረክ ለዲሞክራሲያዊ ምክክር በኢትዮጵያ) ዛሬ (ኀሙስ ነሐሴ 28 ቀን 2001 ዓ.ም.) ረግጦ ወጣ።

 

በአዲስ አበባ በሚገኘው የእንግሊዝ ኤምባሲ አግባቢነት ባለፈው ሰኞ ነሐሴ 25 ቀን 2001 ዓ.ም. ተጀምሮ በነበረውና መድረክን ጨምሮ አምስት ፓርቲዎች በተሳተፉበት ስብሰባ ላይ፤ መድረኩ ውይይቱ ለሁለት ቀናት እንዲራዘሙለት ባቀረበው ጥያቄ መሠረት ውይይቱ ማክሰኞ እና ረቡዕ ተቋርጦ ዛሬ ከሰዓት በኋላ ቀጥሎ ነበር።

 

እንደ ኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ከሆነ በፓርላማው ሕንፃ ውስጥ “መከላከያ አዳራሽ” አምስቱም ፓርቲዎች በተገኙበት ተጀምሮ በነበረው በዚሁ ስብሰባ ላይ መድረኩን ወክለው የተገኙት ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ፣ ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ ኢንጂንየር ግዛቸው፣ አቶ አስራት ጣሴ እና አንድ ግለሰብ ነበሩ። መድረኩ ውይይቱን ጥሎ የወጣበት ምክንያት ከገዥው ፓርቲ ኢህአዲግ ጋር በተናጠል ብቻ ነው መወያየት የምፈልገው በማለት እንደሆነ የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች አስረድተዋል።

 

በዚህ ስብሰባ ላይ ከመድረክ ሌላ ተሳታፊ የነበሩት ገዥው ፓርቲ ኢህአዲግ (የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር)፣ መኢአድ (የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት)፣ ኢዴፓ (የኢትዮጵያዊያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ) እና ቅንጅት (ቅንጅት ለአንድነት ለዲሞክራሲ ፓርቲ) ናቸው። መድረክ ስብሰባውን ረግጦ ሲወጣ ሌሎቹ ፓርቲዎች ግን ስብሰባውን ቀጥለውበታል።

 

ኢህአዲግን በመወከል በስብሰባው ላይ የተገኙት አቶ በረከት ስምዖን (የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ)፣ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ (በሚኒስትር ማዕረግ የጠ/ሚ/ሩ አማካሪ) እና የኢህአዲግ የድርጅት ጽ/ቤት ኃላፊው አቶ ሙክታር ከድር መገኘታቸውን የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገልፀዋል።

 

ከተቃዋሚዎች ወገን ደግሞ ከመኢአድ ዶ/ር ታዲዮስ፤ ከኢዴፓ አቶ ሙሼ ሰሙ እና አቶ አብዱረህማን አህመዲን፤ ከቅንጅት ደግሞ አቶ አየለ ጫሚሶ፤ እንዲሁም የእንግሊዝ ኤምባሲ ታዛቢዎች በስብሰባው ላይ መገኘታቸውን ምንጮቻችን አክለው ገልፀዋል።

 

ይሄንን የጋራ ስብሰባ የእንግሊዝ ኤምባሲ እንዲያወያይ ኃላፊነት የተሰጠው ተቀማጭነታቸው በኢትዮጵያ ከሆኑ የለጋሽ ሀገራት አምባሳደሮች ሲሆን፤ ሃሳቡም ለሚቀጥለው የ2002 ሀገር አቀፍ ምርጫ ገዥው እና ተቃዋሚ ፓርቲዎች በጋራ የምርጫውን የሥነምግባር ረቂቅ ደንብ ላይ እንዲወያዩ ለማድረግ ታቅዶ ነው። ስብሰባው የደቡብ አፍሪካ፣ የጋና እና ናይጄሪያን የምርጫ ሥነምግባር ደንቦች መነሻ በማድረግ እንደሚካሄድ ለመረዳት ችለናል።

 

ሰኞ ነሐሴ 25 ቀን በድርድሩ ቅድመ ሁኔታዎች ላይ ማለትም በስብሰባው አጀንዳዎች፣ በስብሰባው አመራር፣ በስብሰባው ተሳታፊዎች፣ በሰነድ አያያዝ እና በመሳሰሉት ላይ እንደተወያየ ምንጮቻችን ጠቁመዋል።

 

ዛሬ ስብሰባውን ረግጦ የወጣው መድረክ (መድረክ ለዲሞክራሲያዊ ምክክር በኢትዮጵያ) ስምንት ተቃዋሚ ፓርቲዎችንና ሁለት ታዋቂ ግለሰቦችን የያዘ መሆኑ ይታወቃል። ፓርቲዎቹ ኢሶዲፓ (የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ፣ ደኢህዲሕ (የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ሕብረት፣ ኦብኮ (የኦሮሞ ህዝብ ኮንግረንስ)፣ ኦፌዲን (የኦሮሞ ፌደራሊስት ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ)፣ ዓረና (ዓረና ትግራይ ለዲሞክራሲና ለሉዓላዊነት)፣ ሶዲኃቅ (የሶማሌ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ቅንጅት)፣ ኢዲአን (የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ አንድነት ንቅናቄ) እና መጨረሻ ላይ መድረኩን የተቀላቀለው አንድነት (አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ) ሲሆኑ፤ ግለሰቦቹ ደግሞ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ (የቀድሞው የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት) እና አቶ ስየ አብርሃ (የቀድሞ የመከላከያ ሚኒስትር) እንደሆኑ ይታወቃል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ