ነፃ ፕሬሶች ምላሽ እየሰጡ ነው

Ethiopia Zare (አርብ ታህሳስ 9 ቀን 2002 ዓ.ም. December 18, 2009)፦ በኢትዮጵያ ነፃ ፕሬስ ላይ እንደሚዘምት ከሣምንት በላይ ነጋሪት ሲያስመታና ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በየዜናዎቹ መሃል ሳይቀር ማስታወቂያ ሲያስነግር የሰነበተው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፤ ለሦስት ቀናት የቀድሞ ነፃ ጋዜጦችንና ከ97 ወዲህ የተፈጠሩትን ጨምሮ በዩኒቨርሲቲ ምሁራንና በተለጣፊ የጋዜጣ ማኅበር አመራሮች በመጠቀም አብጠለጠለ። በተለያዩ ፕሬሶች ምላሽ እየተሰጠው መሆኑ ታወቀ።

 

የአዲስ ነገር ጋዜጠኞች መሥራት ባለመቻላቸው ሀገር ጥለው መሰደዳቸውን ከገለጹ በኋላ የተለያዩ የመንግሥት የመገናኛ ብዙኀን ጋዜጠኞቹንና ፕሬሱን የሚያንቋሽሹ ዘገባዎች ሲያሰራጩ መሰንበታቸው ይታወሳል።

 

ለሦስት ቀናት የዘለቀውን የኢትዮጵያ ቴሌቭዥንን ዘመቻ ተከትሎ ከማክሰኞ ጀምሮ በወጡ የነፃ ፕሬስ ጋዜጦች አፀፋዊ ምላሽ እየተሰጠው እንዳለ ለማወቅ ችለናል። በእነዚህ የግል ጋዜጦች ላይ እየተፃፉ ያሉት አስተያየቶች በኢቲቪ፣ በጋዜጠኞቹና በፕሮፖጋንዳ አቀናባሪ ካድሬዎች የአስተሳሰብ ደረጃ ማፈራቸውን የሚገልጹ ናቸው።

 

ረቡዕ ዕለት ከወጣው ከግል ጋዜጦች ጋር ተደብሎ ካልተከሰሰውና በአቶ አብነት የሜድሮክ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ዓመታዊ የ80 ሺህ ብር ድጎማ ይደረግለታል ከሚባልለት “ኢትዮ ቻናል” ጋዜጣ በቀር ሌሎቹ በተለያየ መንገድ የኢቲቪን ወቀሳ አበጠልጥለውታል። በርዕሰ አንቀጽ፣ በዜና፣ በዓምድ እና በአስተያየት መስጫ ገጽ ላይ የተተቸው ኢቲቪ መች እንዲሚሻሻል አጠያያቂ መሆኑን ተንትነዋል።

 

አርብ ዕለት የወጣው ጎግል ጋዜጣ በርዕስ አንቀጽ የልማት አብሳሪንም የመርዶ ነጋሪነትም ሚና እንደሚጫወቱ ገልጾ፤ በተለያየ ጊዜ የቀረቡ ዘገባዎችን ከልማትና ከመርዶ ጋር በማነፃጸር ትንታኔ ሰጥቶበታል።

 

ኢቲቪ “የግሉ ፕሬስ ልማት አብሳሪ ወይስ መርዶ ነጋሪ” እና “ተጣሞ ያደገው ነፃ ፕሬስ” በሚሉ ንዑስ ርዕሶች የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነት መምህር የሆኑትን ፕሮፌሠር ሽመልስ በጅጋን በመጥቀስና የጋዜጦችን ርዕስ ብቻ በመንቀስ ዱላ ቀረሽ ስድቡን አዝንቧል።

 

በነጋድራስ ጋዜጣ ላይ በኢቲቪ የቀረበው ቃለ ምልልሳቸው ሚዛናዊነቱን ያጣ ተቆራርጦ አመቺ በሆነ መልኩ ብቻ የቀረበ መሆኑን የተናገሩት የቀድሞ የእፎይታ ጋዜጣ ምክትል አዘጋጅ የአሁን የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ረዳት ፕሮፌሠር መኩሪያ መካሻ ናቸው። ነጋድራስ ጋዜጣ በዜና መልክ ያቀረበው ዘገባ የተለያዩ ጋዜጠኞች አስተያየት በመጥቀስ ሲሆን፤ የኢቲቪን ደካማ ጎን የሚያጎላ እንደሆነ አሳይቷል።

 

በሪፖርተር ጋዜጣ “ልናገር” አምድ ላይ የተብጠለጠለው ኢቲቪ የሪፖርተርን በአላሙዲን ላይ የተነጣጠሩ ዘጋባዎች እንኳሶ የነበረ ሲሆን፤ ጋዜጣው በወንጀል ሊጠየቅ እንደሚገባው በአቶ በረከት ምክትል በአቶ ሽመልስ ከማል ቀርቦ ነበር። ሪፖርተር ጋዜጣ የቴሌቪዥንን ዘገባ ከመጤፍም ሳይቆጥር እንደተራ ነገር በአምድ አስተናግዶለታል።

 

የ2002 ምርጫን አስታክኮ የአዲስ ነገር ጋዜጠኞችን ከጨዋታው ውጪ አድርጎ ለሌሎች ጋዜጦች ማስፈራሪያ እንዲሆን የተዘጋጀው የቴሌቪዥን ፕሮግራም ለአራተኛ ቀን የቀጠለ ሲሆን፤ የህዝብ አስተያየት እንዲሰጥበት ተደርጓል። ይህ የማሸማቀቅ ሥራ በአሁኑ ጊዜ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይም የቀጠለ ሲሆን፤ በየቀኑ በማይታወቁ ሰዎች ረዘም ያሉ መጣጥፎች እየቀረቡ ይገኛሉ።

 

አንዳንዶችም በኢቲቪ አንድም አስዳሳች ነገር አይተው እንደማያውቁና ፕሮግራሞቹም ሁልጊዜ ጭቅጭቅ፣ ብሶት ውሸትና ምሬት ስለሆነ በዐረብ ሳተላይት የሚተላለፉ ፕሮግራሞችን ማየት እንደሚያዘወትሩና የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ፕሮግራምን እንደማያዩ የአንባቢያን አስተያየቶችን አስፍረዋል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!