የመድረክ የካቲት 28 ቀን 2002 ዓ.ም. ህዝባዊ ስብሰባ“ህዝቡ ፈርቶና ተሸማቆ መኖር የለበትም” የመድረኩ አመራር

Ethiopia Zare (ረቡዕ መጋቢት 1 ቀን 2002 ዓ.ም. March 10, 2010)፦ ህዝቡ ለነፃነቱ መስዋዕትነት መክፈል እንደሚኖርበት እና ፈርቶና ተሸማቆ መኖር እንደሌለበት የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች አንድነት መድረክ (መድረክ) የካቲት 28 ቀን ከቀትር በኋላ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ባካሄደው ህዝባዊ ስብሰባ ላይ ገለጸ።

 

የመድረክ የካቲት 28 ቀን 2002 ዓ.ም. ህዝባዊ ስብሰባከቀኑ 8፡30 እስከ 12 ሰዓት በዘለቀውና ምርጫ 2002ን ምክንያት ያደረገ ዕጩ ተወዳዳሪዎችን ከማስተዋወቅ አልፎ ከነዋሪው ህዝብ ጋር ለመወያየት በተጠራው ህዝባዊ ስብሰባ ላይ የመድረኩ ተጣማሪ ፓርቲ አመራሮችና የወቅቱ የመድረክ ሊቀመንበር ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ ተገኝተዋል።

 

በመቶዎች የሚቆጠሩ በቄራ አካባቢ የወረዳ 20 ቀበሌ 42 እና ከተለያዩ የአዲስ አበባ ክፍሎች የመጡ ዜጎች በታደሙበት የዕለተ ዕሁዱ ስብሰባ “በሀገር ጉዳይ ማኩረፍ፣ ተስፋ መቁረጥና ወደኋላ ማፈግፈግ እንደማይገባ፣ ህዝቡ መንግሥትን አክብሮ እንጂ ፈርቶና ተሸማቆ መኖር እንደሌለበት፣ ነፃነቱ የተገደበበት ህዝብ እጁን አጣጥፎ በመኖሪያ ቤቱ መቀመጥ እንደሌለበት፣ ብሎም ለነፃነቱ ሲል መስዋዕትነት መክፈል እንደሚኖርበት” የመድረኩ አመራሮች ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።

 

ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በመድረኩ የካቲት 28 ቀን 2002 ዓ.ም. ህዝባዊ ስብሰባይህን መሰሉን ማሳሰቢያ ከሰጡት ሰዎች መካከል ፕ/ር በየነ ጴጥሮስና አቶ ተመስገን ዘውዴ ዋንኛዎቹ ሲሆኑ፤ የስብሰባው ታዳሚ የሆነው ህዝብም ማሳሰቢያውን በከፍተኛ የጭብጨባ ድምፅ ድጋፍ ሰጥቶታል። ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ አቶ ስየ አብርሃ በተገኙበት በዚሁ ስብሰባ ላይ ዶ/ር ኃይሉ አርኣያ “የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በርካታ ፊልሞችን ለመረጃ እየወሰደ ቁንጽል የሆነውን ብቻ ለህዝቡ ዓይን ያቀርባል” በማለት ተቋሙን ከተቹ በኋላ፤ “ያለፉት 18 የኢህአዲግ አገዛዝ ዓመታት የኢትዮጵን ህዝብ ልብ ያጎሹ ናቸው። አሁን በመደለያ የእነ አቶ መለስ ደጋፊ ሊያደርጉት ቢሞከርም፤ ህዝቡ በገንዘብና በጥቅማ ጥቅም ልቡን አይሸጥም” ሲሉ ተሰምተዋል።

 

“ነፃነታችን በእጃችን” የሚል መርኅ የነበረው የመድረክ ህዝባዊ ስብሰባ በታዳሚው የአዲስ አበባ ነዋሪ በኩል ደስታና የመነቃቃት ስሜትን የፈጠረ እንደነበር ለመረዳት ተችሏል። መድረክ በተከታታይ በአዲስ አበባ የተለያዩ ክፍሎችና በሀገሪቱ ዋና ዋና ቦታዎች በመዘዋወር ተደጋጋሚ ህዝባዊ ስብሰባዎችን እንደሚያካሂድ ለመረዳት ተችሏል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!