ኮሚቴው ሪፖርት እንዳመለከተው

- በስድስት ሴቶች ላይ ፆታዊ ትንኮሳ ፈፅመዋል፣

- በርካታ ገንዘብ ተመዝብሯል፣

- ከ50 በላይ የቅርብ ቤተሰቦቻቸውን ቀጥረዋል

ልዩ ሪፖርታዥ

Ethiopia Zare (ዓርብ መጋቢት 19 ቀን 2000 ዓ.ም. March 28,2008) ሪፖርተራችን ከአዲስ አበባ የላከልንን እና እንቢልታ ጋዜጣ በዛሬው ዕለት ዓርብ መጋቢት 19 ቀን 2000 ዓ.ም. (ማርች 28 ቀን 2008 እ.ኤ.አ.) ዕትሙ ይዞት የወጣውን ልዩ ሪፖርታዥ ይዘን ቀርበናል።

 

 

በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትና የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በፍርድ ቤቶች አስተዳደር ዳይሬክተሩ በአቶ ዳኛቸው ካሣ ምክንያት በደል ደርሶብናል የሚሉ ሠራተኞች አቤት በማለታቸው የተቋቋመው ኮሚቴ፤ በፍርድ ቤቶች በርካታ ገንዘብ መመዝበሩን፣ ወደ 50 የሚጠጉ የዳይሬክተሩ የቅርብ ዘመዶች ያለአግባብ ሥራ መቀጠራቸውን፤ በፍርድ ቤቱ ሴት ሠራተኞች ላይ ፆታዊ ትንኮሳ መፈጸሙን የሚጠቁም ሪፖርት ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ለአቶ ከማል በድሪ ከአንድ ወር በፊት አቀረበ። ፕሬዚዳንቱ በሪፖርቱ ላይ ይፋዊ መልስ አለመስጠታቸውን ምንጮቻችን ጠቁመው፤ ነገር ግን በሪፖርቱ ላይ በተደረገው ማጣራት 95 በመቶ አቶ ዳኛቸውን ነፃ ሊያወጣ የሚችል ሪፖርት መዘጋጀቱ ታውቃል።


 

ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ምንጮች ለእንቢልታ ጋዜጣ እንደገለፁት፤ ለህብረተሰቡ የፍትህ መስጫ አካላት በሆኑት ሦስቱ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ውስጥ እየተፈፀመ ያለው አስተዳደራዊ በደል ተጣርቶ መፍትሄ መገኘት አለበት የሚል ሃሳብ ቀርቦ በዳኞች ስብሰባ ላይ መወሰኑን ገልጸዋል። በዚህ ስብሰባ ላይም የፍርድ ቤቶችን አስተዳደራዊ ሥራ የሚሰራበት የጠቅላይ ፍርድ ቤት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ዳኛቸው ካሳ፣ በሠራተኞች ላይ አለአግባብ በደል ይፈፅማሉ፣ ፍርድ ቤቶቹን የግለሰብ ድርጅት እስኪመስሉ ድረስ እንደፈለጉ ሰዎች ይቀጥራሉ፣ በሴት ሠራተኞች ላይ የተለያዩ ጫናዎችን በመፍጠር የመድፈር ሙከራ ይፈጽማሉ፣ ይህንን ተግባራቸውን ደግሞ የፍርድ ቤቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት በዝምታ እያለፉት እንደሆነ የሚገልፁ ክሶች መቅረባቸውን ምንጮችን ጠቁመዋል። 

 

 

በስብሰባው ላይ በተደረሰ መግባባት የተጠቀሱት ድርጊቶች ተፈፅመው እንደሆነና እንዳልሆነ የሚያጣራ ኮሚቴ እንዲቋቋም ውሳኔ መስጠቱንና የኮሚቴው ሥልጣንና ተግባርም አቶ ዳኛቸው ካሳ ድርጊቱን ፈጽመዋል᐀ ወይስ አልፈፀሙም᐀ የሚለውን ብቻ አጣርቶ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ለአቶ ከማል በድሪ እንዲያቀርብ ኃላፊነት ይሰጠዋል። ኮሚቴው አምስት አባላት እንዲኖሩት ተደርጎ የተመረጠ ሲሆን፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሰቢ አቶ አስመላሽ ወ/ስላሴ፤ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ም/ፕሬዚዳንት አቶ አዲል አህመድ፤ አቶ አማረ ሙሄ፣ አቶ መድህን ኪሮስ እና ወ/ሮ ዘነበች ክብቴ የተባሉ ሦስት ዳኞችና በአጠቃላይ አምስት አባላት ያሉበት ኮሚቴ ይቋቋማል። 

 

 

የቅንጅት አመራሮች፣ ጋዜጠኞችና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት አባሎችና ሌሎች ተከሳሾች ክስን በመሃል ዳኛነት ተሰይመው ለሁለት ዓመታት ሲያስችሉ የነበሩት የከፍተኛው ፍርድ ቤት ም/ፕሬዚዳንት አቶ አዲል አህመድ የሥራ ጫና እንዳለባቸው በመግለጽ ገና ከጅምሩ ከኮሚቴው ራሳቸውን ማግለላቸውን ምንጮቻችን ጠቁመዋል። 

 

 

ቀሪው በአራት ሰዎች የተዋቀረው ኮሚቴ፤ ከተቋቋመበት ቀን ጀምሮ ሦስት ወራትን ከፈጀ በኋላ የካቲት 7 ቀን 2000 ዓ.ም. ያጠናቀቀውን ሪፖርት ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት ማቅረቡ ታውቋል። ነገር ግን ፕሬዚዳንቱ ሪፖርቱን ይፋ ያደርጋሉ፤ ስብሰባ ይጠራሉ፣ እርምጃ እንዲወሰድ ይወስናሉ አሊያም ሪፖርቱን ውድቅ ያደርጋሉ ተብሎ ቢጠበቅም ከአንድ ወር ለሚበልጥ ጊዜ ዝምታን መምረጣቸው ታውቋል። አራት አባላት ባሉት በዚህ ኮሚቴ የተጠናውና ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና ለፌዴራል ፍርድ ቤት ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ የቀረበው ይህ ሪፖርት፤ ኮሚቴው ለምን እና እንዴት እንደተቋቋመ፣ ምን ምን ጉዳዮችን እንዳጣራ፣ ማን ማንን እንዳነጋገረ በድምጽ ቀድቶ በወረቀት ከተገለበጠ ንግግር ጭምር ካተተ በኋላ የደረሰበትን በዝርዝር አስፍሯል። ምንጮቻችን እንደጠቆሙት፣ ኮሚቴው ሪፖርቱን ለማቅረብ በመረጃነት እና በማስረጃነት የተጠቀመባቸውን ግለሰቦች ቃል በድምፅ የተቀዳውን እንዳለ በማስገልበጥ፤ የግለሰቦችን ስም በዝርዝር በመጥቀስ አስፍሯል። ኮሚቴው የደረሰበትን ድምዳሜ፣ የገጠሙትን ችግሮችና የመፍትሄ ሃሳብ በመጠቆም በስፋት አብራርቷል።

 

 

በተደረገው ማጣራትም ከሰበሰበው መረጃ ኮሚቴው ደረስኩበት ያለው፤ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የአስተዳደር ዳይሬክተሩ አቶ ዳኛቸው ካሳ፣ ምስክርነታቸው በአካል ቀርበው በሰጡ የሰጡት ቃል ነው በሚል የተጠቀሰው ስድስት ሴቶች ላይ የወሲብ ትንኮሳ ፈፅመዋል። በሪፖርቱ ላይ ሴት ሠራተኞች የምስክርነት ቃልም፣ ቢሮ ውስጥ አስገድደው ስመውናል፤ በጉንተላ ያለ ፍላጐታችን ለመዳራት ሞክረዋል፤ የወሲብ ጥያቄዬን ካልተቀበላችሁ በሚል በደል ፈጽመውብናል የሚሉ እንደሚገኙበት ሪፖርቱ ጠቅሷል። 

 

 

የሠራተኛ ቅጥርንም በሚመለከት የፍርድ ቤቱ አቅም ከሚፈቅደው በላይና በትክክለኛና ሕጉን በተከተለ መንገድ መመዘኛዎችን ያላሟሉ ግለሰቦችን የፍርድ ቤት ሠራተኞች አድርገው በመቅጠር ፍርድ ቤቶቹን በገዛ ፍቃዳቸው ሲያስተዳድሩ ነበር ይላል ሪፖርቱ። ለዚህም ሪፖርቱ እያንዳንዱን ስም እና የዝምድናውን ደረጃ በመዘርዘር እንደ ማስረጃነት ያቀረበው፤ ከወንድማቸው ጀምሮ የቅርብ ዘመዶቻቸው የተካተቱበት 20 ግለሰቦች በፍርድ ቤቱ ቋሚ ሠራተኛነት ተቀጥረዋል፣ 13 በመኖሪያ ቤት የሚገኙ ጎረቤቶቻቸውን ቀጥረዋል፣ ቀደም ሲል ይሰሩበት ከነበረው "አዲስ ጋዝ" ከተባለ ድርጅት 17 ሠራተኞች የቀጠሩ መሆኑንና ከዚህም ውስጥ 12 የሚሆኑት የሂሳብ ሠራተኞች እንደሆኑ በሪፖርቱ ተጠቅሷል። 

 

 

የሚቀጠሩት ሠራተኞች በዕድሜያቸው ያልበሰሉ፤ በትምህርት ደረጃቸው ያልዳበሩና "ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ" ከሚባል ከአንድ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋም በርከት ብለው የተቀጠሩ መሆናቸውን ሪፖርቱ መዳሰሱን ምንጫችን ጠቁመዋል። ኮሚቴው የማጣራት ሂደቱን ሲያከናውን "ገጠመኝ" ያላቸውን ችግሮች በሪፖርቱ ላይ በዝርዝር የጠቀሰ ሲሆን፤ ከነዚህም መካከል በዳኞች ስብሰባና ሁሉም አካል በተገኘበት ታምኖበት የተቋቋመው (የእነሱ ማለት ነው) ኮሚቴ እያለ እንዲጣራ ኮሚቴ በተቋቋመበት የአስተዳደር ዳይሬክተሩ አማካኝነት የስነ-ምግባር መኮንኖች የሚመሩት ሌላ ኮሚቴ መቋቋሙን ነው። 

 

 

በሥነ ምግባር መኮንኖች የሚመራው ይህ ኮሚቴም ፈጠረብን ያሉትን ችግር በሪፖርቱ ሲያስቀምጡ፤ ማስረጃ ለመሰብሰብ የሚያነጋግሩአቸውን የፍርድ ቤቱን ሠራተኞች ስብሰባ ጠርተው ባነጋገሩ ማግስት፣ ያኛው ኮሚቴም ስብሰባ በመጥራት ጉዳዩ የሚመለከተው ይኼኛው ኮሚቴ ስለሆነ ለኛ ንገሩን በሚል ሠራተኛው ግራ እንዲጋባ በማድረግ በሠራተኞቹ ላይ ውዥንብር መፍጠራቸው ተጠቁሞአል። የደረሰባቸውን በደል ለማስረዳት ወደ ኮሚቴው የሚቀርቡ ሠራተኞች እንዲፈሩና እንዲሸማቀቁ እድል መፈጠሩን ጠቅሶ፤ የማጣራት ሂደቱ መሰራት የነበረበት የአስተዳደር ዳይሬክተሩ ከሥራ ታግደው ወይም እረፍት እንዲወጡ ተደርጎ መሆን ሲገባው ባሉበት መደረጉ እክል መፍጠሩን ሪፖርቱ ጠቅሷል። 

 

 

እንደውም ይላል ሪፖርቱ፣ አቶ ዳኛቸው በፍርድ ቤት ሠራተኞች በቀረቡባቸው በርካታ ክሶች ምክንያት ኮሚቴው በማጣራት ላይ እያለ ታግደው ወይም እረፍት ወጥተው መከናወን ሲገባው የፍርድ ቤቶቹን ኃላፊዎች በመወከል ወደ ሕንድና ፈረንሳይ አገር ለስብሰባ እንዲሄዱ መደረጉን ይጠቅሳል። ይህ ደግሞ እሳቸው ከበስተኋላቸው የተማመኑት ነገር ቢኖር ነው በሚል ሠራተኛው በሚሰጠው ምስክርነት መተማመን እንዳያድርበት ተደርጓል ይላል። ኮሚቴው ገንዘብን በሚመለከት፤ በሪፖርቱ የጠቀሰው በአቶ ዳኛቸው ምክንያት ከፍርድ ቤቱ ይህን ያህል ገንዘብ ተመዝብሯል ወይም ምንም አልተመዘበረም ለማለት ኮሚቴው የኦዲተር ኤክስፐርት /ባለሙያ/ የሌለው መሆኑን በመግለፅ ነገር ግን ከጄኔራል ኦዲተር የቀረበው ሪፖርት እንደሚያስረዳው በርካታ ገንዘብ መመዝበሩን ሪፖርቱ አመልክቷል። 

 

 

በሪፖርቱ መደምደሚያም፣ በፍርድ ቤቶቹ አስተዳደር ዳይሬክተር አማካኝነት እስካሁን አላግባብ የተሰሩትን ጉዳዮች በማጣራት፤ አስፈላጊው ርምጃ ተወስዶ ማስተካከያ እንዲደረግ በመጠቆም ሪፖርቱን አጠናቋል፡ ኮሚቴው ዝርዝሩን ሳይገልፅ ሪፖርቱን ማጠናቀቁን ብቻ ለሠራተኛው በመግለፅ የካቲት 7 ቀን ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና ለዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ያስረከበ መሆኑን የጠቆሙት ምንጮች ሪፖርቱ ለመቅረብ አንድ ወይም ሁለት ቀናት ሲቀሩት አቶ ዳኛቸው የሦስት ዓመት የተጠራቀመ እረፍታቸውን እንዲወስዱ ተደርገው የፍርድ ቤቱን ግቢ ለቀዋል ብለዋል። 

 

 

የፌዴራል ጠቅላይ ከፍተኛና የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ሁለት አይነት አስተዳደሮች ያሏቸው ሲሆን፣ አንደኛው ዳኞችን የሚያስተዳድረው "የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ" እና የፍርድ ቤቶችን አስተዳደር ሥራ አጠቃሎ የሚሰራው "የፍርድ ቤቶች አስተዳደር ዳይሬክተር" ነው። በሌላ በኩል ከፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያገኘነው መረጃ እንደሚጠቁመው ሪፖርቱ የቀረበለት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ከማል በድሪና ምክትል ፕሬዝዳንቱ አቶ መንበረፀሐይ ታደሰ በሪፖርቱ ላይ በስም የተጠቀሱትን ግለሰቦች በማስጠራት ባደረጉት ማጣራት 95 በመቶ አቶ ዳኛቸውን ነፃ ሊያወጣ የሚችል ሪፖርት ከ15 እና 20 ቀናት በኋላ ይፋ ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ምንጮች ጠቁመዋል። 

 

 

በጉዳዩ ላይ አስተዳደር ዳይሬክተሩን በስልክ ለማነጋገር እንደሞከርነው፤ በመጀመሪያ ሪፖርቱን እንድንሰጣቸውና አይተው መልስ እንዲሰጡን ላቀረቡልን ጥያቄ ፈቃደኛ አለመሆናችንን የገለጽን ሲሆን፣ ሪፖርቱን በሚመለከት የሚያውቁት ነገር እንደሌለና አሁን በፍቃድ ላይ እንደሚገኙ ገልጸው የእረፍት ጊዜያቸውን መጋቢት 30 ቀን ጨርሰው ወደ ሥራ እንደሚመለሱ ከገለጹ በኋላ ኮሚቴው አቀረበው በተባለው ሪፖርት ብቻ ተይዞ ስማቸው በጋዜጣ ቢነሳ ጉዳዩን በቀላሉ እንደማያዩት በመግለጽ ማስፈራሪያ ሰንዝረዋል። 

 

 

ቀረበ የተባለውን ሪፖርት በሚመለከት አስተያየታቸውን እንዲሰጡን የጠየቅናቸው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ በላይ ለገሠ ለእንቢልታ ጋዜጣ እንደገለጹት፤ አቶ ዳኛቸው ካሳ ከሦስት ዓመት በላይ የተጠራቀመ እረፍት ላይ መሆናቸውን ጠቁመው ቀረበ ስለተባለው ሪፖርት ምንም የሚያውቁት ነገር እንደሌለ አስረድተዋል። በጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ጉዳዩን በሚመለከት መልስ እንዲሰጠን ጠይቀን የቀረበውን ሪፖርት በሚመለከት የደረሰበት መደምደሚያም ሆነ ሪፖርቱ ይፋ አለመሆኑ ተገልጾ በጥቂት ቀናት ውስጥ ለመሥሪያ ቤቶቹ ሠራተኞች ይፋ ሲሆን ለሕዝብም ይፋ እንደሚሆን የተገለጸልን ሲሆን፣ እስከዛው ግን በጉዳዩ ላይ ምንም ዓይነት አስተያየት መስጠት እንደማይቻል ተገልጾልናል። 

 

 

ከፍተኛው ፍርድ ቤት ለተወሰኑት ክልሎች በውክልና ከሰጣቸው ፍርድ ቤቶች ውጪ ያሉትን የፌዴራል ጠቅላይ፤ የፌዴራል ከፍተኛና የፌዴራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤቶች ድሬዳዋና አዲስ አበባ የሚያስችሉትን ችሎት ጨምሮ አስተዳደራዊ ጉዳይ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ስር ነው። የዳኞችን የደመወዝ መጠን መወሰን እና ከዳኞች ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያለው የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ሲሆን፤ ደሞዝ ከመክፈል ጀምሮ ያለውን አስተዳደራዊና በከፍተኛና በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ያሉ የፍርድ ቤት ኃላፊዎች (court manager) ጨምሮ ፍርድ ቤቶቹን በበላይነት ይቆጣጠራል ይመራል። የአስተዳደር ዳይሬክተሩ የአቶ ዳኛቸው ተጠሪነትም ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ለአቶ ከማል በድሪና ለም/ፕሬዚዳንቱ ለአቶ መንበረ ፀሐይ ነው። በጠቅላይ ፍርድ ቤት ያሉ ምንጮች እንደጠቀሱት፣ አቶ ከማል በድሪና አቶ መንበረ ፀሐይ ሪፖርቱ ከደረሳቸው በኃላ ሠራተኞችን ተራ በተራ እየጠሩ ማነጋገር መጀመራቸውን ገልጸው፤ አቶ መንበረ ፀሐይ ለኮሜሳ ሥራ ወደ ዛምቢያ ሉሳካ ለ15 ቀናት ለሚሆን ጊዜ እንደሚቆዩ ታውቋል። 

 

 

በኢትዮጵያ ውስጥ ወደ 2 ሺ 400 የሚጠጉ ዳኞች ሲኖሩ፤ ከነዚህ ውስጥ በፌዴራሉ ጠቅላይ፣ ከፍተኛና የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የሚገኙ ዳኞች ቁጥር አዲስ ከተሾሙት ጋር ወደ 150 አካባቢ ነው። በሦስቱም የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አስተዳደር ሥር የሚገኙ ሠራተኞች ደግሞ ወደ 1 ሺ 500 አካባቢ እንደሆኑ ይገመታል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!