“የአቶ መለስን ጤንነት እንድንጠራጠረው ከማድረጉ ውጪ የተለየ ነገር የለውም” ዶ/ር ነጋሶ

“ስለወ/ት ብርቱካንም በግልጽ እንዳንናገር በይፋ ሲያስጠነቅቁንም ነበር” አቶ አንዷለም አራጌ

Ethiopia Zare (ሰኞ መጋቢት 13 ቀን 2002 ዓ.ም. March 22, 2010)፦ እሁድ መጋቢት 12 ቀን 2002 ዓ.ም. መድረክ ኃይሌ ገብረሥላሴ ጎዳና በሚገኘው የውሃ ልማት መ/ቤት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ከህዝብ ጋር ተወያይቷል። ሁለት ወር የቀረውን የ2002 ምርጫ በተመለከተ መድረክ ህዝቡን በመዲናይቱ ሲጠራ የዕለተ እሁዱ ለአራተኛ ጊዜ ነው።

 

ከዚህ በፊት በጉለሌ፣ በአዲስ ከተማ (መርካቶ) እና በቄራ ተመሳሳይ ውይይቶችን ከከተማው ነዋሪዎች ጋር አካሂዷል። በመጋቢት 12ቱ ህዝባዊ ውይይት ቁጥራቸው ከ2 ሺህ የሚበልጥ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች መገኘታቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ከተሰብሳቢዎቹ ከተነሱት የወደብ ባለቤትነት፣ ስለምርጫው ፍትሐዊነትና ከምርጫው በኋላ ጠ/ሚኒስትር መለስ “ሕጋዊ እርምጃ እንወስዳለን …” ስለማለታቸው፤ ስለኑሮ ውድነቱ እና መድረክ ስለሚኖረው አማራጭ ጥያቄዎች የመድረኩ አመራሮች ምላሽ ሰጥተዋል።

 

እንደዚሁም “ኢትዮጵያን ለማስተዳደር ብቃት የላችሁም ስለመባሉ ምን አስተያየት አላችሁ?” የሚል ጥያቄ ተሰብሳቢዎቹ አቅርበዋል። በዕለቱ መድረክን ወክለው በውሃ ልማት አዳራሽ የተገኙት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ ዶ/ር ኃይሉ አርኣያ፣ ኢንጂንየር ግዛቸው ሽፈራው፣ አቶ አስራት ጣሴ እና አቶ አንዱዓለም አራጌ፤ ከተሰብሳቢው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ለተሰነዘሩላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።

 

የአቶ መለስ ዜናዊን ቅድመ ዛቻ በተመለከተ ምላሽ የሰጡት የተከበሩ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ “በምርጫ ዋዜማ … ‘በምርጫ ማግስት ወደ ፍርድ እናቀርባቸዋልን፣ ክስ የምንመሰርትበትን መረጃዎች ከወዲሁ እየሰበሰብን ነው …’ ብሎ መናገሩ አዲስ ነገር አይደለም። ከዚህ ቀደም የህወሓት ኢህአዲግ ልሳን በሆኑ የሕትመት ውጤቶች ብዙ ተጽፏል። በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎችም በተደጋጋሚ ሲነገር የነበረ ነው። ያም ሆኖ በጠ/ሚኒስትር መለስ አንደበት ለዚያውም ጣታቸውን ወደ እኛ እየቀሰሩ ‘ከምርጫው በኋላ ሕጋዊ እርምጃ ልንወስድባቸው እንችላለን’ መባሉ የአቶ መለስን ጤንነት እንድንጠራጠረው ከማድረጉ ውጪ የተለየ ነገር የለውም። እንዲህም ሆኖ ዛቻው በሠላማዊ መንገድ ከምናደርገው የትግል እንቅስቃሴ እንድናፈገፍግ የሚያደርገን ሊሆን አይገባም። ህዝቡን ይዘን፣ ወገናችንን ከአጠገባችን አሰልፈን በፅናት ከታገልን እናሸንፋለን” ብለዋል።

 

ዶ/ር ኃይሉ አርኣያ በበኩላቸው የዶ/ር ነጋሶን አባባል የሚያጠናክር ሃሳብ ሰንዝረዋል። ኢንጂንየር ግዛቸው ሽፈራው ደግሞ “ህዝቡ ስለነፃነቱ መክፈል የሚገባውን ሥርዓት እና ጨዋነት የተመላበትን የሠላማዊ ትግል መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆን አለበት። ገዥው ፓርቲ ፈርተንና ተሸማቀን ከነፃነት፣ ከፍትህ ጥያቄያችን እንድንታቀብ የሚያስተጋባውን የዛቻ ጩኸት ችላ ማለት እንዳለብን ተገንዝበናል። ስለዚህም ህዝቡ ለራሱም ሆነ ለመጪው ትውልድ የነፃነትና የፍትህ ጥያቄ ስኬት ሲል ከጎናችን መሰለፍ ይኖርበታል” ሲሉ ድምፃቸውን አሰምተዋል።

 

የኢትዮጵያን የባህር-በር ባለቤትነት ጉዳይ በተመለከተ ጥልቅና አሳማኝ ምላሽ የሰጠት አቶ አስራት ጣሴ በበኩላቸው፤ “እርግጠኛ ነኝ የእኛ ሠላማዊ ትግል በህዝቡ ከታገዘ ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት ለመሆኗ ቅንጣት አልጠራጠርም። እኛ የታሪክና ዓለም አቀፍ የሕግ ድጋፍ አለን። ኢትዮጵያዊ መንግሥት በሀገሪቱ በቆመ ጊዜ በዲፕሎማሲያዊ መንገድና በሕግ አግባብ የአሰብ ወደብ ባለቤትነታችን ይረጋገጣል” ብለዋል። ዶ/ር ነጋሶም “ኤርትራ ኢትዮጵያን በወረረች ጊዜ ወረራውን ለመቀልበስ ባካሄድነው የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ ወቅት የኢህአዲግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በአብዛኛው፤ የኢትዮጵያ ሠራዊት አሰብን ይዞ ቀጣይ የዲፕሎማሲያዊ ሂደቶች ግፊት እንዲደረግባቸው ወሳኝ ጥያቄ ያቀረበ ቢሆንም፤ ሁለት የወሳኝነት ሚና የነበራቸው የኢህአዲግ ባለሥልጣናት የብዙኀኑን ድምፅ በተንበርካኪነት ቀልብሰውታል። ይህም አሰብ ከኢትዮጵያ ህዝብ ተነጥቆ ለሻዕቢያ በስጦታ ወይም በውሰት ለመሰጠቱ እርግጠኛ ላልተሆነበት እንቆቅልሽ በኢህአዲግ በኩል ልዩ ምስጢር መኖሩን የሚያመለክት እንደሆነ ግልጽ ነው” ሲሉ አስተያየታቸውን አስቀምጠዋል።

 

ይህ በእንዲህ እንዳለ በመጋቢት 12ቱ ስብሰባ ትልቅ አጀንዳ ሆኖ የቀረበው የወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ጉዳይ ሲሆን፣ “በብርቱካን ላይ ወደር የሌለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጽሟል። ሌላው ቀርቶ የኢህአዲግ ባለሥልጣኖች ወ/ሪት ብርቱካንን እንደወንጀል የተቆጠረባትን ንግግር ህዝቡ እንዲያደምጠው አልፈለጉም። በቴሌቪዥን እና በራዲዮ በምናደርገው ምርጫውን የተመለከተ የክርክር ሃሳብ ላይም ይሄን የመሰለውን ዓብይ ነጥብ ቆርጠው አውጥተውታል። የካድሬነት ሚና ያላቸው የመንግሥቱ ጋዜጠኞችም “እንደዚህ ብትናገሩ በሕግ ያስቀጣችኋል …” በማለት ስለወ/ት ብርቱካንም ሆነ ስለኢህአዲግ ሕገ-ወጥ ድርጊት በግልጽ እንዳንናገር በይፋ ሲያስጠነቅቁንም ነበር። ...” ብለዋል፤ በዕለቱ በወ/ሪት ብርቱካን ጉዳይ እጅግ በጣም ሲብሰለሰሉ የነበሩት አቶ አንዷለም አራጌ።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!