W/ro Aregash Adane, ወ/ሮ አረጋሽ አዳነን ‘አድዋ ለአረጋሽ፣ አረጋሽ ለአድዋ’ የስብሰባው መሪ መፈክር

Ethiopia Zare (ቅዳሜ መጋቢት 18 ቀን 2002 ዓ.ም. March 27, 2010)፦ በመጪው ምርጫ በትግራይ ክልል ውስጥ በአድዋ ከተማ የአቶ መለስ ዜናዊ ተፎካካሪ ሆነው የሚቀርቡት ወ/ሮ አረጋሽ አዳነን ለማበረታታትና በምርጫው እንዲያሸንፉ ለማገዝ በቫንኩቨር (ካናዳ) ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አዘጋጆቹ ለኢትዮጵያ ዛሬ ገለጹ።

 

የዓረና ትግራይ ለዲሞክራሲያዊና ለሉዓላዊነት ፓርቲ አባልና ስምንት የፖለቲካ ፓርቲዎችን ያቀፈው መድረክ እጩ የሆኑት ወ/ሮ አረጋሽ አዳነ በአድዋ አቶ መለስን ለመፎካከር እንደሚቀርቡ ሲነገር ቆይቷል። ወ/ሮ አረጋሽ እና አቶ መለስ በአድዋ ከተማ ተወልደው ያደጉና በተለያዩ ጊዜያት ህወሓትን የተቀላቀሉ ከመሆናቸውም በላይ በ17 ዓመቱ የትጥቅ ትግል በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች የሠሩ መሆናቸው ይታወቃል።

 

ወ/ሮ አረጋሽ አዳነ ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በኋላ በህወሓት ኢህአዲግ ውስጥ በተፈጠረ አለመግባባት አሸንፎ በወጣው የአቶ መለስ ቡድን ተወግዘው ከተገለሉ ወዲህ ከአጋሮቻቸው ጋር በመሆን ዓረና ትግራይን መስርተው በንቃት የሚሳተፉ ፖለቲከኛ መሆናቸው ይታወቃል።

 

ወ/ሮ አረጋሽን በግል በማገዝና ከጎናቸው መሆናቸውን ለመግለጽ በቫንኮቨር የሚገኙ ነዋሪዎችን ለስብሰባ የጠሩት አዘጋጆች ሰብሳቢ ወጣት ተክለሚካኤል አበበ፤ “አሁን ባለው ሁኔታ በኢትዮጵያ ውስጥ ፍትሃዊ ምርጫ ይደረጋል ብለን ባንጠብቅም፤ እንደ ወይዘሮ አረጋሽ ያሉትን ሴቶች መርዳት ዳዊት በጎልያድ ላይ የተቀዳጀውን ድል ሊያሳየን ይችላል። በተጨማሪም በህወሓት ክፉ ሥራ በትግራይ ተወላጆችና በሌሎች ኢትዮጵያዊያን መካከል የተፈጠረውን ውጥረትና መጠራጠር ያረግባል” ሲል የዝግጅቱን ዓላማ ገልጿል። ወጣት ተክለሚካኤል “ኢህአዲግን በሠላማዊ ትግል ማሸነፍ ይቻላል ከተባለ የህወሓት በትግራይ ውስጥ መሸነፍ ወሳኝ ስለሆነ እንደነ ወ/ር አረጋሽ እና አቶ አስገደ ገ/ሥላሴን የመሰሉ እጩዎችን እንዲያሸንፉ አቅም መገንባት አስፈላጊ ነው” በማለት አስተያየቱን ደምድሟል።

 

በፓርላማ 38 ወንበሮችን ከያዘው የትግራይ ክልል፤ ከአድዋ የምርጫ አካባቢ አንድ ተወዳዳሪ ብቻ የሚያልፍ ሲሆን፣ ወ/ሮ አረጋሽ አዳነ ምርጫው ነፃና ፍትሃዊ ከሆነ ማሸነፋቸው እንደማይቀርና የአቶ መለስን የወደፊት አምስት ዓመት የመግዛት ዓላማ ከወዲሁ እንደሚቀጩት ዝተዋል። ወ/ሮ አረጋሽ ያለጡረታና ባሳዛኝ መልኩ በትግል አጋሮቻቸው ከሥልጣን ተወግደው በድህነት በሚኖሩበት ሁኔታ ውስጥም ሃሳባቸውን በድፍረት በመግለጽ የሚታወቁ ሴት ሲሆኑ፤ ለጦር መሣሪያ መግዣ ውሏል በተባለው የእርዳታ ገንዘብ ላይ ቁጥሩ የተጋነነ ቢሆንም ድርጊቱ መፈጸሙን ማመናቸው ይታወቃል።

 

በዚሁ በሚቀጥለው እሁድ መጋቢት 26 ቀን 2002 ዓ.ም. (አፕሪል 4 ቀን 2010 እ.ኤ.አ.) ከሰዓት በኋላ በቫንኩቨር ከተማ በሚደረገው የገንዘብ ማሰባሰቢያ ሥነሥርዓት ሞዛይክ በሚባለው የመሰብሰቢያ አዳራሽ እንደሚሆን ለማወቅ ተችሏል። በሲያትልና አካባቢው የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ይሄንኑ ሃሳብ በመደገፍ የበኩላቸውን ገንዘብ የማሰባሰብ ዘመቻ መጀመራቸውንም ለማወቅ ችለናል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!