“የኢህአዲግ ደጋፊዎች ሳይቀሩ “ብርቱካን ትፈታ” ብለው መጮህ አለባቸው” አቶ ስየ አብርሃ

Ethiopia Zare (ሰኞ መጋቢት 20 ቀን 2002 ዓ.ም. March 29, 2010)፦ መጋቢት 18 እና 19 ቀን በ4 የተለያዩ ሥፍራዎች የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ጥምረት የሆነው መድረክ፤ በአዲስ አበባ ከተማ ህዝባዊ ስብሰባ አካሂዷል።

 

በስብሰባዎቹም የወረዳ 23፣ 1 እና 9፣ 11፣ 12 እና 13 የመድረክ ዕጩዎች ተዋውቀዋል። እንደ ወረዳዎቹ ቅደም ተከተል የተዋወቁት ዕጩዎች ዶ/ር ኃይሉ አርኣያ፣ አቶ አንዱዓለም አራጌ፣ አቶ ሽመልስ ሀብቴ እና አቶ ባህታ ታደሠ ናቸው። በወረዳ 23፤ ወረዳ 1 እና 9 በቀበሌ የመሰብሰቢያ አዳራሾች፣ በዳግማዊ ምኒልክና በመነን ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ውስጥ ነው ስብሰባዎቹ የተካሄዱት። አንደኛው ስብሰባ ቅዳሜ መጋቢት 18 ቀን በዳግማዊ ምኒልክ ት/ቤት ሲካሄድ የተቀሩት ዕሁድ መጋቢት 19 ቀን ከቀትር በኋላ ከቀኑ 8፡15 ሰዓት ላይ ተጀምረው 11፡30 ሰዓት ላይ ነው የተጠናቀቁት።

 

በወረዳ 23ቱ ስብሰባ ዶ/ር ኃይሉ አርኣያ፣ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ አቶ ስየ አብርሃ እና አቶ ንጉሤ ነውጤ ተገኝተዋል። በወረዳ 1 እና 9 ስብሰባውን የመሩት የመድረክ ወጣቶች ሲሆኑ፤ የመነኑን ደግሞ ኢንጂንየር ግዛቸው ሽፈራው፣ አቶ ተመስገን ዘውዴ፣ አቶ ብሩ በርመጂ እና ወ/ሮ ላቀች ደጋፉ ናቸው።

 

በምኒልክ ት/ቤት አዳራሽ ስብሰባ የተገኙት አቶ ስየ አብርሃ “የብርቱካን ጥያቄ የአንድነትና የመድረክ ጥያቄ ብቻ አይደለም። የእሷ ጥያቄ የማንም ኢትዮጵያዊ ነው። በብርቱካን ላይ በደል ተፈጽሟል ትፈታ ብለን ስንል፤ በማንኛውም ሰው ላይ በደል አይፈጸም! በፖለቲካ ምክንያት የታሰሩት ሁሉ ይፈቱ! ማለታችን ነው። ይህ የእኛ ጥያቄ የመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ መሆን አለበት። የኢህአዲግ ደጋፊዎች ሳይቀሩ “ብርቱካን ትፈታ!” ብለው መጮህ አለባቸው። ብርቱካን በኢትዮጵያ የነፃነት መገፈፍ ተምሣሌት በመሆኗ ሁሉም በምርጫው የሚሳተፍ ዜጋ የምርጫ ካርዱን እሷን በማሰብ ወደ ምርጫ ኮሮጆው ይጨምር” ብለዋል።

 

የብርቱካን ጤንነት ስጋት በማስከተሉ ሁኔታውን ለማጣራትና ብርቱካንን ለመጠየቅ እስር ቤት ድረስ ቢሄዱም መጠየቅ እንደማይችሉ መከልከላቸውንና ይህም ኢህአዲግ ለራሱ ሕገ-መንግሥት የማይገዛ መሆኑን ያረጋገጠበት መሆኑን የገለጹት ደግሞ ዶ/ር ነጋሶ ናቸው።

 

በዚህ ህዝባዊ ውይይት ላይ ብርቱካንን ከአሜሪካዊቷ “ሮዛ ፖርክስ” ጋር አመሳስለው፤ “እሷ ልትታሰር ቀርቶ ሊያስወቅሳት የሚገባት ንግግር አላደረገችም። እንዲት ወጣት ሴት የነፃነት ታጋይን አስሮ፤ ህዝብና ሀገር አስተዳድራለሁ ማለት እጅግ የከፋ ቂም በቀለኝነት ነው። ለሁሉም ለኢህአዲግ የሚኖረው አማራጭ ብርቱካንን ፈቶ ለሠላማዊ ትግሉ እጅ መስጠት ነው” ያሉት ወ/ሮ ላቀች ደገፉ በአዲስ ከተማ የወረዳ 5 መርካቶ አካባቢ፤ በመድረክ የፓርላማ ዕጩ ተወዳዳሪ ናቸው።

 

የመድረክ አመራሮችም በየአዳራሹ በተደጋጋሚ የሚቀርብላቸውንና፡- “ሀገር መምራት አትችሉም ይባላል፤ ትችላላችሁ ወይ?፣ ኢትዮጵያ ወደብ አያስፈልጋትም ለሚለው የኢህአዲግ ሰዎች አቋም የእናንተ መልስ ምንድን ነው?፣ ለሥራ አጡ ወጣት የቀረጻችሁት ዕቅድ አለ ወይ?፣ በአቶ ስየ አብርሃ እና በዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ላይ ያላችሁ ዕምነት የቱን ያህል ነው?፣ እነዚህ ሰዎች በኢትዮጵያ ታሪካዊ አንድነት ላይ የፀና አቋም አላቸው ወይ? እናንተ ከዚህ አስከፊ ሥርዓት ህዝቡን ለማላቀቅ ብቃቱና ልባዊ ወኔ አላችሁን?፣ በወደብ ጉዳይ ከኤርትራ ጋር ሊፈጠር የሚችለውን ቅራኔ የምትፈቱበት ፖለቲካዊ አማራጭ የትኛው ነው? …” የሚሉትንና ሎችም በርካታ ጥያቄዎችን መልስ ሰጥተውባቸዋል።

 

አቶ ተመስገን ዘውዴ፤ “እኛ የምዕራባውያን ተላላኪዎች አይደለንም። ሶማሊያ ጦር አላዘመትንም። አውሮፓና አሜሪካ ሄደን ከእንግሊዝ፣ ከፈረንሣይ፣ ከዩናይትድ ስቴት ባለሥልጣኖች ጋር በልዩ የፍቅር ስሜት … ፎቶ አልተነሳንም፣ ፊልም አልተቀረጽንም። ይሄን ያደረጉት አቶ መለስ ናቸው። የፍቅሩን ዜና ያሠራጩትም የመንግሥት ሚዲያዎች ናቸው። ስለዚህ አሁን ምዕራባውያን በአቶ መለስና በሚዲያቸው ስለሚወገዙበት ሁኔታ … ምስጢሩ ያለው በእነሱ ዘንድ ነው። በእኛ በኩል ለኢትዮጵያ ህዝብ ሰብዓዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብት መከበር፣ የፍትህ ጥማት እርካታ፣ … በሠላማዊ መንገድ እየታገልን ነው። ህዝብን እያስፈራሩና እያሸማቀቁ መግዛት ይቁም በማለት ላይ ነን …” በማለት ምዕራባውያን ከአቶ መለስ አገዛዝ ጋር እየሻከረ የመጣውን ግንኙነታቸውን አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል።

 

ኢንጂንየር ግዛቸው ሽፈራው በበኩላቸው ደግሞ፤ “ከክቡር አባዱላ ገመዳ፣ አዲሱ ለገሠ፣ ደመቀ መኮንን፣ ተሾመ ቶጋ፣ ... ወዘተ የበለጡ፤ የትምህርትና የሥራ ልምድ ማስረጃቸው በተጨባጭ ሊቀርብ የሚችል ምሁራንና ሀገር መርተው የሚያውቁ ሰዎችን በመድረክ ስር አሰባስበናል። ስለዚህ የመድረክ ሰዎች ሀገር መምራት አይችሉም የሚለውን አንቀበለውም” ብለዋል።

 

ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፤ “ለኢትዮጵያ ዳር ድንበር፣ ሉዓላዊነት፣ ለህዝቡ ነፃነትና አንድነት … ለነዚህ ሁሉ ክብር በጋራ እንቆማለን” ያሉ ሲሆን፤ አቶ ስዬ ደግሞ - “የባሕር በሩ ጉዳይ በዲፕሎማሲያዊና በዓለም አቀፍ የሕግ አግባብ የሚፈታ ነው። 80 ሚሊዮን ህዝብ የባሕር በር ተዘግቶበት ሊቀመጥ አይችልም። ኤርትራውያንም ከኢትዮጵያ ህዝብ ተነጥለው ሊኖሩ የሚችሉበት ሁኔታ ስለሌለና የሕልውናቸውም ጉዳይ ከኢትዮጵያ ጋር ፍፁም የተቆራኘ በመሆኑ፤ የወደብ ጉዳይ ከእኛ ወገን ብቻም ሳይሆን ከእነሱም በኩል ለፍቅር እና ለሁለቱ ሀገራት ዘላቂ ወንድማማችነት ሲባል ግፊት የሚደረግበት ነው …” በማለት ለባሕር በሩ ጥያቄ መልስ ይሆናል ያሉትን ሃሳብ ሰንዝረዋል።

 

ሰሞኑን ቪዛ መከልከላቸው የተሰማው አቶ አንዷላም አራጌ በበኩላቸው፤ “ብርቱካንን በማሰር አገዛዙ ከሽንፈት፣ በታሪክ ፊት ከመዋረድና የትውልድ ማፈሪያ ከመሆን አይድንም” ካሉ በኋላ፤ “የኢትዮጵያ ህዝብ ለነፃነቱ ከመታገል አንድ ኢንች ወደኋላ ማፈግፈግ የለበትም” በማለት ህዝቡ ለነፃነቱ ይታገል ዘንድ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

 

የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ጉዳይ ሰፊውን አጀንዳ በያዘበት የመድረክ ህዝባዊ ስብሰባዎች፤ 14ኛ ወሯን ጨርሳ 15ኛ የእስር ወራቷን የጀመረቸው ወ/ት ብርቱካን “በዕንቅልፍ ማጣት ሕመም እንደምትስቃይ መጋቢት 12 ቀን 2002 ዓ.ም. ለወላጅ እናቷ ነግራለች። በአሁኑ ወቅት የመርፌ ሕክምና እየተሰጣት ይገኛል። ያም ሆኖ የጤንነቷ ሁኔታ የሚያሳስበን በመሆኑ ህዝቡ በፆምና በፀሎት ተማጽኖ እንዲያስባት …” ብለዋል፤ የመድረክ ሰዎች ዕሁድ መጋቢት 19 ቀን 2002 ዓ.ም. በመነን ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ከቀትር በኋላ ባስተላለፉት ጥሪ ከሰኞ መጋቢት 20 ቀን 2002 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ ይሆን ዘንድ የጠየቁ ሲሆን፤ 15ኛ ሻማ በማብራት የብርቱካን እስር ታስቧል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ