Ethiopia Zare (ማክሰኞ ሰኔ 29 ቀን 2002 ዓ.ም. July 06, 2010)፦ በጥቂት ሀገር ወዳዶች የጋራ ጥረትና ስብስብ ተቋቁሞ በኢትዮጵያና በሌሎች የዓለም ክፍሎች መሠራጨት የጀመረውን የኢትዮጵያ ሳይተላይት ቴሌቪዥን ጣቢያ ለመርዳት በስዊድን መዲና ስቶክሆልም ከተማ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ።

 

በዚህ ሰኔ 19 ቀን 2002 ዓ.ም. (ጁን 26 ቀን 2010 እ.ኤ.አ.) በስቶክሆልም ከተማ ረፋዱን በተደረገው ዝግጅት ላይ ብዛት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ተገኝተው የዝግጅቱ ተካፋይ ሲሆኑ፤ መግቢያ ዋጋውን ጨምሮ በተዘጋጀው ምግብ፣ በጨረታ እና በሎተሪ ዕጣ በርካታ ገንዘብ ሊሰበሰብ እንደቻለ ታውቋል።

 

ከዚህም በተጨማሪ ከተሳታፊዎቹ መካከል ኢሳትን በቋሚነት ለመርዳት የተነሳሱ ሰዎች ስማቸውንና በየወሩ የሚሰጡትን የገንዘብ ልክ ማሳወቃቸውን የገንዘብ አሰባሳቢው ኮሚቴ በተለይ ለኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ ገለጸ።

 

የእርዳታ አሰባሳቢው ኮሚቴ ሰብሳቢ ተስፋዬ ፍሰሃ፣ ዝግጅቱ ምን ያህል የተሳካ እንደሆነ ለተጠየቁት ሲመልሱ፤ ዝግጅቱ በአጭር ጊዜ ብዙ ጥሪና ቅስቀሳ ሳይጠይቅ እንደተከናወነ ገልጸው፣ የመጣው የሰው ብዛትም ሆነ የተዋጣው ገንዘብ ከተጠበቀው በላይ እንደሆነ አሳውቀዋል። ይህም ሁኔታ የሚያስገነዝበው የኢትዮጵያ ህዝብ ምን ያህል የመረጃ እጥረት እንዳለበት የውጪው ማኅበረሰብ መረዳቱን ሲሆን፤ ለወደፊትም ተስፋ ሰጪ መልክ እንደታየበት ገልጸዋል።

 

በዝግጅቱ መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ ሰብሳቢው ባደረጉት ንግግር በሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ርብርብ የኢሳት ቴሌቪዥን እንደተቋቋመና በአይነቱም የመጀመሪያ እንደሆነ ገልፀው፤ የመረጃ ነፃነትን በኢትዮጵያ አስተማማኝ ለማድረግ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሀገራዊ ግዴታው በመሆኑ በቀጣይነት መርዳት እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል።

 

በኢትዮጵያና በሌላው የሠለጠነው ዓለም ያለውን የመገናኛ ብዙኀን (ሚዲያ) አጠቃቀምን አስመልክተውም ሲናገሩ፤ በአንድ ያደገ ሀገር ብቃት ያለው ህዝብን የሚያገለግል ሚዲያ አለ፤ ህዝብም የመረጃ ነፃነት እንዳለው ያውቃል ይህንንም የሚያስፈጽም መንግሥት አለ። በመሆኑም መንግሥት ህዝብና ሚዲያ በመቀናጀት ብቃት ያለው መረጃ ለህዝብ ያደርሳሉ። እኛ ግን ለዚህ ባለመታደላችን መንግሥት ለራሱ ፕሮፖጋንዳ ብቻ የሚጠቀምበት በመሆኑ ህዝብ ያጣውን የመረጃ ነፃነት ለመቀናጀት የኢሳት በአሁን ሰዓት መወለድ ወደር የማይገኝለት አማራጭ መሆኑን ገልጸዋል።

 

አቶ አህመድ አሊ በስዊድን የኢትዮጵያ ራዲዮ ሥርጭት ኃላፊ በበኩላቸው፤ ለአንድ ሀገር ህዝብ የመረጃ አገልግሎት ያለውን ጠቀሜታ፣ በፖለቲካው በኩል የሚጫወተውን ሚና እና በኢትዮጵያ ያለውን የሚዲያ አፈና ተጨባጭ ሁኔታ ሰፋ አድርገው ተንትነዋል።

 

በስዊድን የአንድነት ፓርቲ የድጋፍ ማኅበር ፀሐፊ የሆኑት አቶ መላኩ ወልደአምላክ በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ያለበትን የመረጃ ጥማት አስረድተው፤ ኢሳት ወቅታዊ ሆኖ የመረጃ እጥረትን ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት መነሳቱን በማድነቅ በአስተማማኝ ሁኔታ ግቡን ሊመታ እንደሚችል ያላቸውንም እምነት ገልጸዋል።

 

በመቀጠልም የኢትዮጵያ ሳይተላት ሥርጭት ጣቢያ የቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት ፕሮፌሠር አለማየሁ ገ/ማርያም በኤሊክትሮኒክስ መገናኛ ቀርበው፣ የኢሳትን አጀማመር በማብራራት ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ሥርጭቱን እውን ለማድረግ የከፈሉት መስዋዕትነት ቀላል እንዳልሆነ ገልጸዋል። ኢሳት በመረጃ አቅርቦት በኩል ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚጫወተው ሚና ከፍ ያለ እንደሆነ በማረጋገጥ፤ በስዊድንና በተለያዩ የዓለም ክፍል ያሉ ኢትዮጵያውያን ድጋፋቸው በጅምር ብቻ ሳያበቃ በቀጣይነት መርዳት እንደሚገባቸው ጥሪ አቅርበዋል። ከዚህም ሌላ ከተሰብሳቢዎች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል።

 

ከፕ/ር አለማየሁ በመቀጠል ሌላው ተናጋሪ የነበሩት በስዊድን የግንቦት ሰባት ንቅናቄ ተወካይ የሆኑት አቶ ቸኮል ጌታሁን፤ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ያለውን የፖለቲካ አመለካከት እንዳለ ይዞ ከኢሳት ጎን በመቆም የኢትዮጵያዊነት ድርሻውን መወጣት እንደሚገባው በማሳሰብ፣ ኢሳት የመረጃ ነፃነት መፍትሔን ይዞ የመጣ መሆኑን ገልጸዋል።

 

ከተናጋሪዎቹ በተጨማሪም ኢሳትን ለማጠናከር በአንድነት መሥራት አማራጭ የሌለው መሆኑን የሚገልጹ ቀስቃሽ ግጥሞች በሁለት ገጣሚዎች ቀርበው፣ ተሰብሳቢው ቀሪውን ጊዜ በዕለቱ የሚተላለፈውን የዓለም የኳስ ግጥሚያ በአንድነት ተመልክቷል። በመጨረሻም የዝግጅቱ አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ ተስፋዬ ፍሰሃ፣ ዝግጅቱን እውን ለማድረግ የደከሙትንና በቦታው በመገኘት እርዳታ ያደረጉትን ጭምር አመስግነው ፕሮግራሙ ከምሽቱ 5፡00 ሰዓት (23፡00) ተጠናቅቋል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!