• ሪፖርቱ ለዳኞች ቀረበ
  • ከሥራ ታግደው እንዲጣራ ተጠየቀ
  • ዳይሬክተሩ መልቀቂያ አስገብተዋል
  • ሪፖርቱን ተከትሎ ጠ/ፍርድ ቤት እርምጃ መውሰድ ጀመረ

Ethiopia Zare (ዓርብ ሚያዝያ 10 ቀን 2000 ዓ.ም. April 18, 2008)፦ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ዳኛቸው ካሳ በሠራተኞች ላይ ፈጽመውታል የተባለውን በደል እንዲያጣራ የተቋቋመው ኮሚቴ ሪፖርቱን ለሦስቱም ፍርድ ቤት ዳኞች አቀረበ። በአስቸኳይ ሕጋዊ ርምጃ እንዲወሰድ ዳኞች የጠየቁ ሲሆን፣ አስተዳደር ዳይሬክተሩ የሥራ መልቀቂያ ማስገባታቸው ታውቋል።

 

ፍርድ ቤቱ ሪፖርቱን መሠረት አድርጎ እርምጃ መውሰድ የጀመረ ሲሆን፣ "የወሲብ ትንኮሳን ባለመቀበላችን አላስፈላጊ ምደባ ተደርጎብናል" ያሉ ወደ ቦታቸው እንዲመለሱ፣ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ብቻ ይፈጸም የነበረው ቅጥር ቀርቶ ሦስቱም ፍርድ ቤቶች ቅጥርን ራሳቸው እንዲያከናውኑና፣ እድገትን በተመለከተ የሚቀርቡ ቅሬታዎችን የሚያጣራ ኮሚቴ እንዲቋቋም ተወስኗል።

 

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የከፍተኛ፣ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አስተዳደር ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ዳኛቸው ካሳ በሦስቱም ፍርድ ቤቶች ሠራተኞች የቀረበባቸውን ቅሬታ እንዲያጣራ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና የአስተዳደር ጉዳዮች ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ፣ የፌዴራል ፍርድ ቤት ዳኞች አቶ አማረ አሞኘ፣ አቶ መድኅን ኪሮስ እና ወይዘሮ ዘነበች ክብርቴ የተባሉ አራት አባላት ያሉት ኮሚቴ መቋቋሙ ይታወሳል።

 

ይህ ኮሚቴ ሠርቶ ያዘጋጀውን ሪፖርት ለዳኞች አስተዳደር ጉባዔና ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቅርበው ውጤቱ ሲጠበቅ የነበረ ሲሆን፣ ባለፈው ሣምንት ዓርብ ከ120 በላይ የፍርድ ቤት ዳኞች ተጠርተው ሪፖርቱ ተሰምቷል።

 

በጠቅላይ ፍርድ ቤት ዓርብ ሚያዚያ 3 ቀን 2000 ዓ.ም ሪፖርቱን ለማሰማት የተጠሩት ዳኞች ምናልባትም ከ95 በመቶ በላይ የሚሆኑት የሁሉም ፍርድ ቤት ዳኞች ተገኝተዋል።

 

የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ከማል በድሪ ስብሰባውን የመሩ ሲሆን ምክትል ፕሬዝዳንቱ አቶ መንበረ ፀሐይ ታደሰ አብረዋቸው ተቀምጠዋል። ጉዳዩን እንዲያጣራ ከተቋቋመው ኮሚቴም አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴና አቶ መድኅን ኪሮስ ሪፖርቱን አቅርበዋል።

 

ከቀኑ 8 ሰዓት ከ15 ደቂቃ ሲሆን ሪፖርቱ በአቶ መድኅን ኪሮስ መነበብ ጀመረ። በመካከል የሻይ ዕረፍት ከተደረገም በኋላ ስብሰባው ቀጥሎ ከቀኑ 11 ሰዓት ከ30 ደቂቃ ሲል ተጠናቀቀ።

 

የሪፖርቱ አጠቃላይ ይዘት የፍርድ ቤቶቹ አስተዳደር ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ዳኛቸው ካሣ በስድስት ሴቶች ላይ ጾታዊ ትንኮሳ ፈጽመዋል፣ በርካታ ገንዘብ ተመንዝሯል፣ ከ50 በላይ የቅርብ ቤተሰቦቻቸውን ቀጥረዋል፣ በመሥሪያ ቤቱ ንብረትና መኪኖች ለግል መኖሪያ ቤት ግንባታ አውለዋል የሚል ነበር። ሪፖርቱ ከቀረበ በኋላ ዳኞች በሪፖርቱ ላይ ያላቸውን አስተያየት እንዲሰጡ ተጠየቁ።

 

"ኮሚቴው ምን ሥልጣን አለው? የትኛው መመሪያ ነው ዳኞች በአስተዳደሩ ሥራ ጣልቃ እንዲገቡ የሚፈቅደው? ብዙ ባለጉዳይ በምናስተናግድበት ሰዓት እዚህ ሥራ ፈትተን መቀመጣችን አሳፋሪ ነው" በማለት የአንድ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ሴት ዳኛ አስተያየት ሰጥተዋል።

 

አንድ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ወንድ ዳኛ በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት፣ "ሪፖርቱ በአሉባልታ ላይ የተመሠረተ፣ በማስረጃ ያልተደገፈ መደምደሚያ የሌለው ተራ አሉባልታ ነው። ዳኛ ሆነንም በእንደነዚህ ዓይነት መንገድ የምንሠራ ከሆነ ያሳፍራል" ብለዋል።

 

"ሪፖርቱ ማጠቃለያ የሌለውና የአስተዳደር ዳይሬክተሩን ሃሳብ ያላካተተ በመሆኑ ሪፖርቱን የተጓደለ ያደርገዋል" ያሉት ደግሞ አንድ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኛ ናቸው።

 

ሌሎች ዳኞች በሰጡት አስተያየት ደግሞ በዲሲፕሊን ክስ እርምጃ ይወሰድ፣ በመደበኛ ወንጀል ይከሰስ፣ ጉዳዩ ለፀረ-ሙስና ኮሚሽን ይመራ፣ ጉዳዩ እልባት እስኪያገኝ ከሥራ ይታገድ፣ ማጣራት እየተደረገ ለምን ወደ ሕንድና ፈረንሳይ እንዲሄድ ተደረገ? ሪፖርቱ በጊዜ መታወቁ የመሥሪያ ቤቱን ገጽታ ከመጥፋት አድኖታል፣ ከዚህ የባሰ ጉዳት ሳይደርስ ርምጃ ሊወሰድ ይገባል የሚሉ አስተያየቶች ተሰንዝረዋል።

 

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ከማል በድሪ ለተነሱት ጥያቄዎች ማጠቃለያ ሲሰጡ፣ አቶ ዳኛቸው ወደ ውጭ አገር እንዲሄዱ የተደረገው ከሌሎች የፍርድ ቤቱ አስተዳደሮች ጋር መሆኑን፣ ደግሞ አንድ ሰው ተጠርጣሪ ነው ማለት ወንጀለኛ ነው ማለት ባለመሆኑ እንደ ማንኛውም የአስተዳደር ሠራተኛ መላካቸውን፣ ከሥራ ይታገዱ ለሚለው ደግሞ አቶ ዳኛቸው ቀድመው መልቀቂያ ያስገቡ መሆናቸውን ጠቅሰው በአጠቃላይ የቀረበውን ሪፖርት የበላይ አመራሩ አይቶና ገምግሞ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚደርስበትን እንደሚያስታውቅ ገልጸው ስብሰባው ተበትኗል።

 

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምንጮቻችን እንደጠቆሙት፣ ከሪፖርቱ መቅረብ በኋላ የፍርድ ቤቱ የበላይ ኃላፊዎች ተወያይተው አዳዲስ ውሳኔዎችን ያስተላለፉ ሲሆን፤ ሪፖርቱን መሠረት አድርጎ እርምጃ መወሰድ መጀመሩ ታውቋል።

 

"የቀረበልንን የወሲብ ትንኮሳ ባለመቀበላችን ከሥራ እንድንዛወር ተደርገናል" ያሉ ሠራተኞች ቀደም ሲል በነበሩበት ሥራ እንዲመለሱ የታዘዘ ከመሆኑም በላይ ቀደም ሲል በጠቅላይ ፍርድ ቤት ብቻ ይፈጸም የነበረው ቅጥር በሦስቱም ፍርድ ቤቶች እንዲሆን፣ ዕድገትን በሚመለከት የሚቀርቡ የቅሬታ ጥያቄዎችን የሚያጣራ ኮሚቴ ይመቻች መባሉን ምንጮቻችን ጠቁመዋል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!