ምርጫው ሲጠናቀቅ ሩዝ ኪሎው ከ6 ወደ 12 ብር ገባ

Ethiopia Zare (እሁድ ሚያዝያ 12 ቀን 2000 ዓ.ም. April 20, 2008)፦ ዛሬ ማምሻውን አዲስ አበባ ደውለን ባገኘነው መረጃ መሠረት ኢህአዴግ “አረጋግቼዋለሁ” ያለው የምግብ ሸቀጣ ሸቀጦች ዋጋ ከ15 % እስከ 100 % (በእጥፍ) ማደጉን ለመረዳት ችለናል።

 

የኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ ዘጋቢ ወደ አዲስ አበባ ደውሎ ማምሻውን ገበያ ወጥተው የነበሩ ሰዎችን አነጋግሮ ባገኘው መረጃ መሰረት ዛሬ እስከ ከሰዓት ረፋዱ ላይ 6 ብር ይሸጥ የነበረው አንድ ኪሎ ሩዝ ምሽት ላይ 12 ብር መሸጥ እንደተጀመረ ታውቋል። በዚህ ስሌት ሩዝ 100 % (በእጥፍ) የዋጋ ጭማሪ እንደተደረገበት ያሳያል።

 

የኑሮ ውድነቱ እያሻቀበ በመጣበት ወቅት አንድ ሊትር ዘይት 26 ብር ድረስ ገብቶ የነበረ ሲሆን፣ ኢህአዴግ ገበያውን አረጋጋለሁ ብሎ ቁጥጥር ጀምሮ በነበረበት ጊዜ ሊትሩ 17 ብር ገብቶ እንደነበር ዘጋቢያችን ያነጋገራቸው የከተማው ነዋሪዎች ገልፀዋል። በዛሬው ምሽት ላይ ግን በሊትር 2 ብር ከሃምሳ ሣንቲም መጨመሩን እነዚሁ ነዋሪዎች ገልጠዋል። በዘይት ላይ የተደረገው የዋጋ ጭማሪ 15 በመቶ ነው።

 

ስኳር ቀን ኪሎው 7 ብር ከ50 ሣንቲም ሲሰጭ ውሎ ካረፈደ በኋላ 10 ብር መግባቱን እነዚሁ የመዲናዋ ነዋሪዎች ለሪፖርተራችን ገልጠዋል። የስኳር ዋጋ ጭማሪ በመቶኛ ሲሰላ 33.3 % ይሆናል።

 

“ለዋጋ ቁጥጥርና መረጋጋት” በሚል ኢህአዴግ ባለሱቆች በተለይ የሚሸጧቸውን ምግብ ነክ ሸቀጦች ስምና ዋጋ ዝርዝር በሱቆቻቸው መስኮት ወይን ፊት ለፊትና ሁሉም ሰው ሊያቸው በሚችልበት ስፍራ እንዲለጥፉ መመሪያ አውጥቶ ነበር። በዚህ መሰረት ሱቆች ይህንን ግዴታ ሲፈጽሙ ይሰተዋላሉ። ዛሬ ማምሻውን በከተማዋ ያሉ በርካታ ሱቆች የዋጋ ዝርዝሮቻቸውን እየቀየሩ ሲለጥፉ ማስተዋላቸውን ኢትዮጵያ ዛሬ ያነጋገራቸው የከተማው ነዋሪዎች ገልጠዋል።

 

ዘጋቢያችን በስልክ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ምርጫው በተጠናቀቀ ማምሻውን እንዲህ ያለ የዋጋ ንረት መታየቱ እንዳስገረማቸው ገልጠው፤ ኢህአዴግ አደረግሁት ያለውን የዋጋ ቁጥጥርና ማረጋጋት ለምርጫው ፕሮፓጋንዳ ሊጠቀምበት አስቦ ከነበረ ሞኝነትና “ጨፍኑና ላሞኛችሁ” አይነት ጨዋታ ነው የሚሆነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

 

ባለፈው ሣምንት እሁድ ሚያዝያ 5 ቀን 2000 ዓ.ም. በሀገር አቀፍ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማሟያ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተደረገ ሲሆን፤ በዛሬው ዕለት ደግሞ በአዲስ አበባና በአንዳንድ ክልሎች የክፍለ ከተማ አስተዳደርና የቀበሌ አስተዳደር ምርጫ መደረጉ ይታወቃል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!