• የፍርድ ቤቱ ግቢ ጨናንቆ ነበር
  • ሦስት መኪና ተጨማሪ የፖሊስ ኃይል ተጠራ

 

Ethiopia Zare (ሰኞ ሚያዝያ 13 ቀን 2000 ዓ.ም. April 21, 2008)፦ ዛሬ ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ላይ የከፍተኛው ፍርድ ቤት በፍርድ ቤት ታሪክ ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ መልኩ በህዝብ ተጨናንቆ እንደነበር በችሎቱ አካባቢ የተገኙ የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገለጹ።

 

Teddy Afro

የቴዲ አፍሮን ችሎት ሂደት ለመከታተል ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ጀምሮ የጎረፈው ህዝብ ብዛት ከአሁን በፊት በፕሮፌሰር አስራት፣ በፕሮፌሰር መስፍንና በቅንጅት መሪዎች የችሎት ሂደት ላይ ከታየው የህዝብ ብዛት በእጅጉ ይልቅ እንደነበር በሁሉም የፍርድ ሂደቶች ላይ ተገኝተው የነበሩ ታዛቢዎች ገልፀዋል።

 

ችሎቱን አጨናንቆት የነበረው ህዝብ ከችሎቱ እንዲወጣ ከተደረገ በኋላ ነበር ጥቂት ሰዎች የፍርድ ቤቱ ሠራተኞችና ጠበቆች ብቻ እንዲገቡ ቢደረግም የህዝቡ ብዛትና ሁኔታ አስቸጋሪ ከመሆኑ የተነሳ ተጨማሪ ሦስት መኪና መሉ የፓሊስ ኃያል ተጠርቶ ህዝቡን ከአካባቢው በማራቅ ነበር ችሎቱ የተጀመረው።

 

ለአጭር ሰዓት የተሰየመው ችሎት የቴዲ አፍሮ ጠበቃ ያቀረበው የክስ መቃወሚያ "አንቀጹ ይቀየርልኝ"፣ "ክሱ ተብራርቶ አልቀረበም" እንዲሁም "ያለመንጃ ፍቃድ የሚለውም ተብራርቶ አልተገለጸም" ሲሉ ለችሎቱ አሰምተዋል።

 

ዳኛ አቶ ልዑል ገብረማሪያም ክሱን አሻሽሎ ለማቅረብ የአስር ቀን የጊዜ ገደብ ይበቃሃል ወይ? በማለት ለዓቃቤ ሕግ ጥያቄ ቢያቀርቡም፤ "ክሱን አሻሽዬ ለማቅረብ ሦስት ቀን ይበቃኛል" ሲል ዓቃቤ ሕግ በመመለሱ ለመጭው ረቡዕ ሚያዝያ 15 ቀን 2000 ዓ.ም. የተቀጠረ መሆኑን ለማወቃ ችለናል።

 

በተጨማሪም የዋስትና መብቱን በሚመለከት ጠበቃው ያነሱትን ጥያቄም የተሻሻለውን የክስ አንቀጽ ሳናይ ዋስትና መስጠትም ሆነ መከልከል አንችልም በማለት ዳኛው ችሎቱን በመዝጋት መነሳታቸውን ምንጮቻችን ገልጸዋል።

 

ችሎቱ ከተዘጋ በኋላ ቴዲ አፍሮ ከችሎቱ ውጭ ይጠብቀው ለነበረው ህዝብ እጁን ሲያውለበልብ፤ ከችሎቱ ውጭ ይጠባበቀው የነበረው ህዝብ በጩኸት ግቢውን ያናጋው ከመሆኑም በላይ ቴዲን የጫነውን የእስረኛ መኪና ከግቢው አናስወጣም እዚሁ ግደሉን በማለት ወጣት ሴቶችንና ወንዶች የቴዲ ደጋፊዎች ባነሱት ከፍተኛ ተቃውሞ መኪናው ወደግቢ ተመልሶ እንዲገባ ተገድዷል። በዚህም ምክንያት ተጨማሪ የፌዴራል ፖሊስ ተጠርቶና ሁለት ወደኋላና ወደፊት መትረየስ በደገኑ የፌደራል መኪኖች ታጅቦ ወደ ቃሊቲ የተጓዘ መሆኑን እነኝሁ ታማኝ ምንጮች አረጋግጠዋል።

 

በወቅቱ የፌዴራሉ የፖሊስ ሃይል እጅግ ብዙ እንደነበርና ከህዝቡ ልክ ለማድረግ ጥረት ተደርጎ የነበረ ከመሆኑም በላይ ብዙ ጊዜ እስረኞች በሜክስኮ በኩል አቋርጠው ወደእስርቤቱ የሚሄዱ ቢሆንም በቁጣ የነደደው ህዝብ ለማሳለፍ ካለመቻሉ የተነሳ መንገዶችን በመዝጋት ቴድሮስ ካሳሁንን የጫነው መኪና በጦር ኃይሎች በኩል ለመሄድ እንደተገደደ ታውቋል።

 

ህዝቡም ችሎቱ ተጀምሮ እስኪያልቅ አበባየሆሽ የሚለውን የቴዲን ዘፈንና አንመካም በጉልበታችን ሚለውን ዜማ በማንጎራጎር እንደተበተነ ምንጮቻችን አረጋግጠዋል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!