Helen Berhe, አርቲስት ሔለን በርሔ

  • የብአዴን ዝግጅት ላይም ተመሳሳይ ችግር ገጥሟት ነበር
  • ነዋይ ደበበም አልተሳካለትም

Ethiopia Zare (ማክሰኞ ታህሳስ ቀን 2003 ዓ.ም. January 4, 2010)፦ ባሳለፍነው አርብ የፈረንጆቹን አዲስ ዓመት ምክንያት በማድረግ አዲስ አበባ በሚገኘው ሸራተን አዲስ ሆቴል በተዘጋጀው የሙዚቃ ኮንሰርት ላይ በቅርቡ በአዲሱ የሙዚቃ አልበሟ ተደማጭነትን ያገኘችው አርቲስት ሔለን በርሔ እና አርቲስት ነዋይ ደበበ ተመልካቹን አሸማቀቁ።

 

በየዓመቱ የሚከበረውን የፈረንጆቹን የገና በዓል እና አዲስ ዓመት በማስመልከት ታዋቂ ዓለም አቀፍ አቀንቃኞችን ወደ አገር ውስጥ በማስገባት በሸራተን ሆቴል ዝግጅት እንዲቀርብ የሚያደርጉት ሼክ መሐመድ አል አሙዲን በዘንድሮው የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ታዋቂው የሙዚቃ አቀንቃኝ አር ኬሊ ተገኝቶ እንዲዘፍን አድርገዋል። በዚህ መድረክ ላይም፤ አርቲስት ነዋይ ደበበ፣ አርቲስት ሔለን በርሔ፣ አርቲስት እዮብ መኮንን እና ከስዊድን የመጣች ትግሬኛ ዘፈን ተጫዋች አርቲስት ረሻን ገብሬ ይዘፍናሉ የሚል ማስታወቂያ መነገር የጀመረው ከዝግጅቱ እጅግ አስቀድሞ ነበር።

 

አርብ ታህሣሥ 22 ቀን 2003 ዓ.ም. ማምሻውን የተጀመረው ዝግጅት በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን በቀጥታ ሥርጭት መተላለፍ የጀመረ ሲሆን፤ ”ታስፈልገኛለህ” በሚለው አዲሱ አልበሟ በቅርቡ እውቅናን ያገኘችው አርቲስት ሔለን በርሔ የሙዚቃ ሥራዎቿን ስታቀርብ፤ ተመልካቹ ”ማነው እንዲህ ዘፈኗን ያበላሸባት?” በሚል እርስ በርሱ መጠያየቅ የጀመረ ሲሆን፤ ዘፈኑን እያቀረበችው ያለችው እራሷ መሆኗ ሲታወቅ ”ሔለን በርሔ በኮምፒዩተር ሸውዳናለች” በሚል ተመልካቹ ሲናደድባት ተደምጧል።

 

አርቲስቷ በሙዚቃ አልበሟ ላይ ከተካተቱት ዘፈኖች አንዱንም በሚገባ መዝፈን ካለመቻሏም በላይ ከሦስት ዓመት በፊት ለቃው በነበረው ”ኡዛዛ አሌና” በተሰኘው ዘፈኗ በተለያዩ ዐረብ አገራት መድረኮች ላይ የመጫወት ልምድ እንዳገኘች ቀደም ሲል በሰጠቻቸው ቃለምልልሶች ብትገልጽም፤ በዚህ ሥራዋ ግን አንድም ቀን መድረክ ላይ ሠርታ የምታውቅ በማይመስል ሁኔታ የተጋነነው ስሟ በተሳሳተ ችሎታ ላይ የተመረኮዘ መሆኑን በራሷ ላይ አስመስክራለች።

 

ምንጮች እንደሚጠቁምትም፤ ከወራት በፊት በባህርዳር በተካሄደው የብአዴን 30ኛ ዓመት በዓልን በማስመልከት ሁለት የሙዚቃ ዝግጅቶች ተደርገው የነበረ ሲሆን፤ አርቲስቷ በወቅቱ ኢግዚብሽኑ ላይ ለተዘጋጀው መድረክ ለመዝፈን ተስማምታ ከአዲስ አበባ መንቀሳቀሷን ምንጮች ጠቁመው፤ ፓርቲው ባዘጋጀው መድረክ ላይም ለመዝፈን ከፍተኛ ፍላጎት በማሳየቷ በክልሉ ፖሊስ ባንድ ታጅባ እንድትዘፍን መደረጉ ታውቋል። ምንጮች እንደሚሉት በወቅቱ ተሯሩጣ ትዝፈን እንጂ በካሴቷ ላይ ያለውን ድምጿን ማምጣት እንዳልቻለች ጠቁመዋል። በወቅቱ ከባንዶቹ ጋር መጣጣም አለመቻሏ ችግር እንደፈጠረባት ተናግራ ነበር።

 

አርቲስቷ በዚህ በሸራተኑ መድረክ ላይ እንድትዘፍን የተጋበዘችውም የመድረክ ላይ ችሎታዋ ተመዝኖ ሳይሆን ገና አልበሟን ከማውጣቷ በፍላጎቷ ለብአዴን ዝግጅት ያሳየችው ቁርጠኝነት ተመዝኖ እና ከሼኩ ጋር ባጋጣሚ በነበራት የሁለት ቀን ቅርበት (ምንጮች ቅርበቱ ምን እንደነበር አልገለጹም) ሳይሆን እንደማይቀር ምንጮች ጠቁመዋል።

 

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አዳዲስ የሙዚቃ አልበም የሚያወጡ አርቲስቶች ድምጽ ሳይኖራቸው በኮምፒዩተር በመታገዝ አልበማቸውን ካወጡ በኋላ መድረክ ላይ ሲወጡ ህዝቡን ከማዝናናት ይልቅ በማናደድ እና በማሸማቀቅ ዝግጅታቸውን ይደመድማሉ።

 

በዚህ መድረክ ላይ በተመሳሳይ ዝግጅቱን አቅርቦ የነበረው አርቲስት ነዋይ ደበበ ድምጹን አውጥቶ ለመዝፈን እና ትክክለኛውን ዜማ ለማምጣት የተቸገረ ሲሆን፤ ”ይቅርታ ነርቨስ ስለሆንኩ ነው። ለድምጼ መበላሸት ይቅርታ እጠይቃለሁ” በማለት የድምጹን መበላሸት አምኖ እዛው መድረክ ላይ ይቅርታ ጠይቋል። አያይዞም ለዛ መድረክ ያበቁትን ሼህ መሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲንን አመስግኗል። አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች እንደ ነዋይ ያሉ ታዋቂ አርቲስቶች ሥራቸውን እንዲያቀርቡ የሚጋበዙት በችሎታቸው ሆኖ እያለ እንዲህ ያለ ምስጋና ማቅረቡ ተገቢ እንዳልነበር ገልጸዋል። ከኢትዮጵያውያኑ አርቲስቶች በኋላ ዝግጅቱን ያቀረበው አርኬሊ የኛን ዘፋኞቹ አሳጥቷቸዋል። ተመልካቹ የህብረተሰብ ክፍል መድረክ ላይ ከነበሩት አርቲስቶች ይልቅ ”አበባየሆሽ” የተሰኘው የቴዲ አፍሮ ዘፈን በዲጄ ሲለቀቅ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨፈረ ደስታውን ሲገልጽ ታይቷል።

 

በአሁኑ ወቅት አዲስ አልበም የሚያወጡትም ሆነ የቀድሞዎቹ አንዳንድ አርቲስቶች ሼኩ በሚያዘጋጁት ማንኛውም ዝግጅት ላይ ተከፈላቸውም አልተከፈላቸውም ችሎታቸውን እና የሞያውን ክብር ሳይጠብቁ የሚሳተፉ ሲሆን፤ የገዢው ፓርቲ በሚያዘጋጀው ዝግጅት ላይ ተጋብዘው እና ሳይጋበዙ መዝፈናቸው እየተለመደ መምጣቱን ኢትዮጵያ የሚገኙ ምንጮቻችን ጠቁመዋል። አርቲስት እዮብ መኮንን ባልታወቀ ምክንያት ሳይዘፍን ቀርቷል።

 

የጽሑፉ አዘጋጅ አስተያየት

የጥበብ ሥራ ከፖለቲካ የራቀ ሊሆን ከመገባቱም በላይ ታዋቂዎቹም ገና ከመሬት ከፍ የሚሉትም አርቲስቶች የገዢው ፓርቲ ዝግጅቶች ማድመቂያ በመሆን እውቅና የሚሰጡት ከሆነ፤ በአሁኑ ሰዓት ካለው ትውልድ የተወሰነው ፐርሰንት እነሱን መከተሉ አይቀሬ ነው። ስለዚህም እንዲህ ያሉት አርቲስቶች ህዝቡን በድምጻቸው መሸወዳቸው ሳያንስ በገንዘቡ እንዲተባበራቸው ማድረጉ ተገቢ አይደለም እና ከወዲሁ ሊታረሙ ይገባል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!