• ሁለቱም የተለያየ ትዕዛዝ ለችሎት ልከዋል
  • ፍርድ ቤቱ ሃሳባቸሁን በአንድ አጠቃላችሁ ስጡኝ ብሏል

Ethiopia Zare (ዓርብ ሚያዝያ 17 ቀን 2000 ዓ.ም. April 25, 2008)፦ የኢ.ፌ..ዲ.ሪ የፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ አሰፋ ከሲቶ እና ሚኒስትር ዴኤታው ዶ/ር ሐሺም ተውፊቅ የግለሰቦችን ጉዳይ በያዘ አንድ መዝገብ ላይ «ክስ ሳይቋረጥ ይቀጥል» በሚል የተለያየ ደብዳቤ ለፍርድ ቤት በመፃፍ ተወዛገቡ፡፡ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የወንጀል መምሪያም በዚሁ መዝገብና በአንድ ዓይነት ጉዳይ ሁለት የተለያዩ ውሳኔዎችን ሰጥቷል፡፡

 

ቅርብ የሆኑ የፍትህ ሚኒስቴር ምንጮቻችን፣ ጉዳዩን በማስረጃ አስደግፈው ለዝግጅት ክፍላችን እንዳስረዱት፤ አቶ በቀለ ገብሬ፣ አቶ ማርቆስ አንሼቦ፣ አቶ ፀደቀ ማርቆስ አንሼቦ እና አቶ ተገኝ ጴጥሮስ የተባሉ ግለሰቦች፣ አቶ አለሙ ለእመንጎ በተባሉ ግለሰብ ላይ በግብረ አበርነት በደል ፈጽመዋል ተብሎ ሚያዚያ 26 ቀን 1997 ዓ.ም ክስ ይቀርብባቸዋል፡፡

 

ክሱን ለፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያቀረበው በፍትህ ሚኒስቴር የአዲስ አበባ አስተዳደር ተጠሪ ጽ/ቤት ሲሆን፣ተከሳሾቹ ክስ ተመሥርቶባቸው እና የክስ መቃወሚያ አቅርበው ለብይን ከተቀጠረ በኋላ አድራሻቸው በደቡብ ሕዝቦች ካጣ ዞን ቃጫ ቢራ ወረዳ ሺንቪቶ ከተማ የሆኑት አቶ ማርቆስ አንሼቦና አቶ ፀደቀ ማርቆስ አንሼቦ የተባሉት ሁለት ተከሳሾች «ክሱ ሊነሣልን ይገባል» በማለት ለፍትህ ሚኒስቴር ያመለክታሉ፡፡

 

ጉዳዩን የተመለከተው የፍትህ ሚኒስቴር የወንጀል ጉዳይ መምሪያ በየካቲት 17 ቀን 1998 ዓ.ም በቁጥር 07/43 አተ 04/98 በተፃፈ ደብዳቤ ክሱ እንዲቀጥል ያዛል፡፡

 

የክስ ሂደቱ ቀጥሎ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ለመስማት ከተቀጠረ በኋላ በወቅቱ በመምሪያው ኃላፊ ተፈርሞ የተሰጠውን ውሳኔ በኤክስፐርትነት የሠሩት እና ክሱ ይቀጥል ብለው የወሰኑት ግለሰብ ተከሳሾቹ ክሱ ይነሳልን የሚለውን ጥያቄ በድጋሚ ሲያቀርቡ የመምሪያ ኃላፊ ሆነው ነበር፡፡

 

ቀደም ሲል ኤክስፐርት ሆነው ክሱ እንዲቀጥል አስተያየት የሰጡት የመምሪያ ኃላፊ በድጋሚ በጥር 16 ቀን 2000 ዓ.ም በቁጥር 07/291 አ01/99 በተፃፈ ደብዳቤ ተቃራኒ ውሳኔና ትዕዛዝ ሰጥተው በየካቲት 11 ቀን 2000 ዓ.ም በነበረው ችሎት የሁለቱም ክስ ይነሳል፡፡

 

የግል ተበዳይ አቶ ዓለሙ ለእመንጎ በየካቲት 19 ቀን 2000 ዓ.ም ይህንኑ ጠቅሰው ለፍትህ ሚኒስቴር ያመለክታሉ፡፡

 

መጋቢት 23 ቀን 2000 ዓ.ም በቁጥር 02/563/አመ07/2000 በፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታው ዶ/ር ሐሺም ተውፊቅ ተፈርሞ የወጣ ደብዳቤ እንደገና ለፍርድ ቤቱ ይላካል፡፡

 

የደብዳቤው ይዘትም፤ ቀደም ሲል ከመምሪያው የተሰጠውን ውሳኔ የሚሽር ሌላ ተቃራኒ ውሳኔ በድጋሚ ከወንጀል ጉዳይ መምሪያ መሰጠቱ አዎንታዊና ሕጋዊ አሠራር የተከተለ ሆኖ አለመገኘቱን በመጥቀስ፤ ከፍትህ ሚኒስቴር ወንጀል ጉዳዮች መምሪያ የሁለቱ ተከሳሾች ክስ እንዲቋረጥ የተሰጠው ውሳኔ ተሽሮ ክሱ እንዲቀጥል በፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታው ዶ/ር ሐሽም ተውፊቅ በመጋቢት 23 ቀን 2000 ዓ.ም ጉዳዩን ለሚያየው ችሎት ደብዳቤ ይፅፋሉ፡፡

 

በማግስቱ መጋቢት 24 ቀን 2000 ዓ.ም በፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር ስምና ፊርማ ለችሎቱ በተፃፈ ደብዳቤ ደግሞ ሁለቱ ተከሳሾች ክሱ እንዲነሳላቸው፣ የወንጀል ጉዳዮች መምሪያ መርምሮ ያቀረበውን ውሳኔ ሚኒስቴር ዴኤታው መሻራቸውን አስታውሰው፤ የክርክር ጉዳዩ ሚኒስትር ዴኤታው ውሣኔውን የሚሽሩበት አሠራር ስለማይኖር፣ ከወንጀል ጉዳዮች መምሪያ ክሱ እንዲነሳ የተፃፈው ደብዳቤ የፀና እንዲሆን አስታውቀዋል፡፡ፍርድ ቤቱ የሚኒስትሩ የአቶ አሰፋ ከሲቶ ትዕዝዝ ሲደርሰው ከአንድ ሚኒስትር መሥሪያ ቤት የተለያዩ ትዕዛዞች መቅረቡ ለአሠራር እና ለትዕዛዝ ያስቸገረ ስለሆነ የተጠቃለለ ሃሳባቸውን አንድ ላይ እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቶ ተጠቃልሎ የሚቀርበውን አስተያየት ለመመልከት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል ሲል በየሳምንቱ የሚታተመው እምቢልታ ጋዜጣ ዝርዝሩ በዛሬ እትሙ ይዞ ወጥቷል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!