Beqa! Sweden, Stockholm April 08, 2011በስዊድን የኢትዮጵያውያን የሰልፍ ውሎ

Ethiopia Zare (ቅዳሜ ሚያዝያ 1 ቀን 2003 ዓ.ም April 9, 2011)፦ ትናንት ዓርብ መጋቢት 30 ቀን 2003 ዓ.ም. ትንሽ ትንሽ፣ ብን ብን ከሚለው ዝናብ በስተቀር ይሄን ያህል ብርድ አልነበረም። የስዊድን ክረምት (ዊንተር) ከመቼውም በበለጠ ሁኔታ እንኳን ለስደተኛው ለዜጋውም አልገፋ ብሎ በረዶው በአንዳንድ ከተሞች ከመሬቱ አልላቀቅ ብሎ ሙጭጭ ያለበት ዓመት ነው - የአውሮጳውያኑ 2011። የአየሩ ፀባይ አፈር ሲሉት ውሃ እንደሆነ የሚያውቀው ኢትዮጵያዊ ግን የክረምት ልብሱን አልወጠም። በሻርፕ ተጠቅሏል፤ ኮፍያውንም አልጣለም።

ከፓርላማው ፊት ለፊት የሚገኘው ሚንትስ ቶርየት አደባባይ ከወትሮው የተለየ የሰልፈኛ ድምፅ እየተሰማበት ነው። ”በቃ! የግፍ አገዛዝ በቃ! ገዬ! በስ! አኖሌ! ገዲስ! …” የሚል።

 

Beqa! Sweden, Stockholm April 08, 2011

 

ሰልፈኛው በድምፁ ብቻ አላባራም፤ መደቡ ጥቁር ሆኖ በነጭ ቀለም ”በቃ!” የሚል ጽሑፍ ያለበት መፈክር በእጁ ይዟል፤ ካኒተራም ለብሷል፤ ”በቃ!” የሚል ኮፍያ አጥልቋል። የኢትዮጵያን ባንዲራና ልዩ ልዩ መፈክሮች ይዟል። በሌላ ፊት በድምፅ ማጉልያ የሚተላለፈው ቀስቃሽ ግጥምና ሙዚቃ እየተሰማ ነው። ይህ የሆነው ዓርብ መጋቢት 30 ቀን 2003 ዓ.ም. (አፕሪል 8 ቀን 2011 እ.ኤ.አ.) ከቀኑ ስምንት ሰዓት (14፡00 ሰዓት) ጀምሮ ነበር።

እስከ ዘጠኝ ሰዓት (15፡00 ሰዓት) ድረስ በዚሁ ሁኔታ ከቀጠለ በኋላ፤ ክላስ ኑርድማርክ መናገሪያውን ጨበጡ። ኑርድማርክ የሶሻል ዲሞክራት ፓርቲ ተወካይ ሆነው በሰልፉ ላይ የተገኙ ሲሆን፤ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ እንድትፈታ ከፓርቲያቸው ጋር በመሆን የደከሙ ፖለቲከኛ ናቸው።

 

Beqa! Sweden, Stockholm April 08, 2011

 

በንግግራቸውም እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2006 ወይዘሪት ብርቱካንን ከማሪታና ከካሪና ሄግ ጋር በመሆን እንዳገኟት ገልጸው፤ ለዲሞክራሲና ለፍትህ መገኘት የቆመች ጠንካራ ሴት እንደነበረች አስታውሰዋል።

”... የአቶ መለስ አስተዳደር ወደር ከማይገኝለት የአገዛዝ ግድፈቱ እንዲታረም ብዙ ብንጥርም፤ እስካሁን ሰው ማሰቃየቱን አላቆመም። ይህንንም በማድረግ የሥልጣን ዕድሜውን እየገፋ ነው። ሆኖም እኛን ከመታገል የሚገታን ምንም ነገር አይኖርም። ይልቁንም በአሁን ሰዓት እዚህ ኤምባሲና አምባሣደር ቢኖረው ኖሮ ”በቃ!” የሚል መልዕክት ባስተላለፍንለት ነበር። ...” ብለዋል።

 

Beqa! Sweden, Stockholm April 08, 2011

 

አሁን ስላለው ሁኔታም ሲገልጹ፤ ለአቶ መለስ ብቻ ሳይሆን በምዕራብ አፍሪካና በመካከለኛው ምስራቅ የተነሳው የለውጥ ንፋስ የዲሞክራሲ ችግር ያለባቸውን ሁሉ ይዞአቸው እንደሚሄድ ሁኔታው ያሳያል በማለት በአውሮጳ በፀደይ ወራት የሚነሳው አለርጂ የሚያጠቃቸው ሰዎች ከሚታይባቸው ሁኔታ ጋር በማመሳሰል ተናግረዋል።

በመጨረሻም ”የወ/ት ብርቱካን እና የሌሎች ታጋዮች ድካም በከንቱ መቅረት አይገባውም፤ አቶ መለስ እንደሌሎቹ ከሰሜን አፍሪካ ዲክታተሮች ጥግ እንዲይዝ እናደርጋለን፤ በኢትዮጵያውያን ከሙሉ ነፃነት በቀር የሚያረካን አይኖርም፤ በመሆኑም በቃ! ... በቃ! ...” ሲሉ ንግግራቸውን ቋጭተዋል።

”ጀግና የሚፈልግ ሀገር ያልታደለ ነው” በማለት ንግግራቸውን የከፈቱት አቶ አህመድ ዓሊ መነሻቸውን ሲያብራሩ፤ ”... ሁሉም ያቅሙን ካደረገና ለተነሳበት ዓላማ በቆራጥነት ከቆመ ጀግና ባልተፈለገ ነበር። በመሆኑም እናንተ የአቶ መለስ መንግሥት የሚያደርገውን የግፍ አገዛዝ በመቃወም ”በቃ!” በማለት በመውጣታችሁ ጀግኖች ያሰኛችኋል” በማለት ሰልፈኛውን አመስግነዋል። አቶ አህመድ ዓሊ የሰልፉ አስተባባሪ ሲሆኑ፤ ለረጅም ዓመታት ከስቶክሆልም የሚተላለፈውን የኢትዮጵያ ድምፅ ራዲዮ የመሩ ናቸው።

Beqa! Sweden, Stockholm April 08, 2011

የሰልፉን ዝግጅት በመምራትና ሰልፉን በማስተባበር የቆዩት ወ/ሮ መቅደስ ወርቁ በበኩላቸው፤ ”... የዛሬው ሰልፍ ዓላማ የአቶ መለስ መንግሥት የሚያደርገውን ግፍ ለማጋለጥ ለመጨረሻ ጊዜ ’በቃን!’ ማለታችንን ለማሳወቅ፤ ለኢትዮጵያ ህዝብም የትግል አጋር መሆናችንን ለመግለጽና ለታፈኑት ወገኖቻችንን ድምፅ ለመሆን ጭምር ነው” ብለዋል።

አያይዘውም ወጣቱ በዚህ የኢንፎርሜሽን ዘመን በመጠቀም ለዲሞክራሲና ለነፃነት በሚደረገው ትግል ላይ ይበልጥ በመደራጅት፤ የወያኔ የግፍ አገዛዝን ”በቃ!” ብሎ መነሳት ይጠበቅበታል ብለዋል።

ገበሬው መሬቱን እየተነጠቀ እንዳለ፤ ሴቶች እህቶቻችን በዘመናዊ ባርነት በዐረብ ሀገራት እየተሸጡ መሆናቸውን፤ የሀገሪቱ ብሔራዊ ሀብት በገፍ እየተበዘበዘ እንዳለና ግልጽነት በሌለው መልክ ለም መሬታችን ለባዕዳን ዜጎች እየተቸበቸበ መሆኑን የገለጹት ወ/ሮ መቅደስ፤ ይህ ሁሉ ከእንግዲህ እንዲቆም በአንድነት ”በቃ!” ብለን መነሳት እንደሚኖርብን አሳስበዋል።

Beqa! Sweden, Stockholm April 08, 2011

በመጨረሻም ሰልፈኛው በቃ! ጋዬ! በስ! አኖኒ! ጊዲስ! … በማለት በተለያዩ የሀገራችን ቋንቋዎች የብሶት ድምፁን አሰምቶ፤ ሰልፉ ማምሻውን አስር ሰዓት ተኩል ላይ (16፡30 ሰዓት) ተበትኗል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!