• ሁለቱ ብቻ መልስ እንዲሰጡ ታዝዘዋል
  • ክሱ የዳኝነት ነፃነትን ከማቀጨጭ ያለፈ ፋይዳ የለውም ተባለ

Ethiopia Zare (እሁድ ሚያዝያ 19 ቀን 2000 ዓ.ም. April 27, 2008)፦ ፍትህ ሚኒስቴር ኅዳር 17 ቀን 2000 ዓ.ም. የሙያ ግድፈት ፈጽመዋል ያላቸው ዳኞች በዲሲፕሊን እንዲጠየቁ ለዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ያቀረበውን ክስ ጉባዔው በሚያዝያ 9 ቀን 2000 ዓ.ም. በሰጠው ውሳኔ ውድቅ ማድረጉን እንዳስታወቀ ተዘገበ። ሃያ ገፆችን የያዘው የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ክሱን እና ምላሹን በዝርዝር ያብራራ ሲሆን፣ ፍትህ ሚኒስቴር ያቀረበውን አቤቱታም አስፍሯል።

 

ፍትህ ሚኒስቴር ያቀረበው ክስ ይዘት፤ የአዲስ አበባ ከተማ ከሚያስተዳድራቸው ቤቶች የሚነሳው ክርክር የማስተናገድ ሥልጣን የተሰጠው ለፌዴራል ፍ/ቤቶች ሳይሆን ለከተማ ነክ ፍርድ ቤቶች በመሆኑ ዳኞች የሥልጣን ገደባቸውን አልፈዋል፣

 

የዳኞቹ ውሳኔ የፍትሐ-ብሔር ሕግ ቁጥር 1195 የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት ነኝ የሚል ሰው የምስክር ወረቀት የሚያስገድደውን ድንጋጌ የጣሰ ነው፣

 

ከዐዋጅ ውጪ የተወሰዱ ቤቶችን በሚመለከት ሥልጣኑ የተሰጠው ለፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ እንጂ ለፍርድ ቤቶች ባለመሆኑ የዳኞቹ ውሳኔ ግድፈት ያለበት ነው፣

 

ዳኞቹ በሥር ፍርድ ቤት ያልተነሣ ክርክር ለውሳኔአቸው መነሻ ማድረጋቸው፣ የፍትሐ ብሔር ሥነ-ሥርዓት ሕ.ቁ. 329ን የሚጥስ ነው፣

 

የቀረበው ክስ ከዐዋጅ ውጭ የተወሰዱ ቤቶች ይመለሱልኝ የሚል ሆኖ ሳለ ዳኞቹ የምርጫ ቤት እንዲመለስ በተጠየቀ አስመስለው መወሰን አግባብ አይደለም የሚል ነው።

 

የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ በውሳኔው ላይ ክሶቹንና የክሶቹን ምላሽ በዝርዝር ያቀረበ ሲሆን በማጠቃለያው እንዳሰፈረው፤

 

የፍትህ ሚኒስቴር ባቀረባቸው ሁለት ቅሬታዎች ዳኞቹ የሚሰጡት መልስና አስተያየት ተመልክቶ ጉባዔው ወደፊት ውሳኔውን ያሳውቃል፣

 

በቀሪዎቹ ጉዳዮች ፍትህ ሚኒስቴር ያቀረባቸውን ቅሬታዎች ጉባዔው ዳኞቹን በዲሲፕሊን የሚያስጠይቁ ሆነው አላገኛቸውም።

 

ለቅሬታው መነሻ የሆነው የፍትሐ-ብሔር ሕግ ቁጥር 1195 በዳኞቹ በአግባቡ የተተረጎመ በመሆኑ፣ ይልቁንም የተሳሳተ ትርጉም የተሰጠው በፍትህ ሚኒስቴር በመሆኑ፣ በቀረበው ጉዳይ ዳኞች የሥልጣናቸውን ገደብ ተላልፈው በፕራይቬይታይዜሽን ሥልጣን ሥር የሚካተት ጉዳይ እና በአዲስ አበባ ከተማ ነክ ፍ/ቤት ሥልጣን ስር የሚወድቁ ጉዳዮችን ማየታቸው ባለመረጋገጡ፣ ይልቁንም የፍትህ ሚኒስቴር የፕራይቬታይዜሽን ዐዋጅ አግባብነት በሌለው ጉዳይ በመጥቀሱ፣

 

የማስረዳት ሸክም ያለው በከሳሽ ወገን በመሆኑና ዳኞቹ ኪራይ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት ያቀረበው ክስ በማስረጃ አልተደገፈም ብለው ቢያምኑ ክሱን ውድቅ ማድረጋቸው ሥነ ሥርዓቱን የተከተለ መሆኑ፣ ይልቁንም የከሰሰ ወገን የማስረዳት ሸክሙን ባይወጣም ተከሳሽ ባለቤት መሆኑን ማስረዳት ነበረበት የሚለው የፍትህ ሚኒስቴር ቅሬታ የሥነ ሥርዓት ሕጎችን መሠረተ ሃሳብ ያልተከተለ መሆኑ በመረጋገጡ፣

 

ፍትህ ሚኒስቴር በኪራይ ቤቶች በኩል ቀርቧል ያለው የኪራይ ውል፣ ከክሱ ጋር ለፍርድ ቤቱ አለመቅረቡ ብቻ ሳይሆን፣ በማስረጃ ዝርዝርም ላይ አለመጠቀሱ፣

 

የከተማ ልማት ሚኒስቴር ቤት ለግለሰቦች ተመልሷል በማለት የሚሰጠው ሰነድ ተቀባይነት ተቃራኒ ማስረጃ እስካልቀረበ ድረስ ተቀባይነት ያለው በመሆኑ፣ ይልቁንም የፍትህ ሚኒስቴር አካሄድ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሚሰጧቸውን ውሳኔዎች ተቀባይነት እንዳይኖራቸው የሚያደርግ በመሆኑ ትክክል አለመሆኑ፣ ሚኒስትሩ ቀርበው ማስረዳታቸው ትክክል መሆኑን፣

 

በቃል ለማስረዳት የቀረቡና የቤቶች ኤጀንሲ የፍትህ ሚኒስቴር ተወካዮች፣ ፍ/ቤቶች በሰጡት ውሳኔ ከመንግሥት እጅ የወጣ ቤት የለም በማለት ማስረዳታቸው፣ ይህም የፍ/ቤቶች ውስጣዊ ስህተት የማረም ሥርዓት በመጠቀም ችግሮችን ማስተካከል የተቻለ መሆኑን ስለሚያሳይ፣

 

የዳኞች ተጠያቂነት መርህ ተቀባይነት ያለው ቢሆንም የሕግ ትርጉም ልዩነት በመኖሩ ብቻ ዳኞቹን በዲሲፕሊን ተጠያቂ ማድረግ ሕገ መንግሥቱም ሆነ ሌሎች ሕጎች የሚፈቅዱ ባለመሆኑ፣

 

ከሕግ አተረጓጎም ልዩነት በተጨማሪ ፍትህ ሚኒስቴር የሥነ ምግባር ችግር ወይም ሌላ ግድፈት መኖሩን የማያሳይ ከጥቅም፣ የግል ስሜት ወይም ሌላ የሥነ ምግባር ጉድለት መኖሩን የሚያሳይ ተጨማሪ ማስረጃ ባለማቅረቡ፣

 

የሕግ ትርጉም ያስጠይቃል እንኳ ቢባል፣ ፍትህ ሚኒስቴር ለሕጉ አንቀጾች የሚሰጠው ትርጉም ወጥነት የሌለው በመሆኑ፣ ይልቁንም ለአንድ የሕግ አንቀጽ ተቃራኒ ትርጉም የተሰጠበት በመሆኑ፣

 

አንዳንዶቹ ጉዳዮች በይግባኝ ወይም በሰበር ቀርበው በሂደት ላይ መሆናቸው በመረጋገጡ፣ በአንዳንዶቹ ደግሞ ከላይ እንደተገለፀው የስር ፍ/ቤት ውሳኔ የተሻረ በመሆኑ፣

 

በመጨረሻም ጉባዔው የቀረበውን ቅሬታ መነሻ በማድረግ በፍትህ ሚኒስቴር ማመልከቻ ስማቸው የተዘረዘረውን ዳኞች በዲሲፕሊን ጥፋት ተጠያቂ ሊሆኑ አይገባም ብሎ አስፍሯል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!