ስያሜው ግንቦት ሰባት ተብሏል

በቅርቡ ራዲዮና ድረ-ገጻቸው ይፋ ይሆናል

Ethiopia Zare (ዓርብ ግንቦት 1 ቀን 2000 ዓ.ም. May 09, 2008)፦ በቅርቡ ከቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲም ሆነ አሁን እንደአዲስ ከተቋቋመው አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ራሳቸውን ያገለሉት ዶ/ር ብርሃኑ ነጋና አጋሮቻቸው ግንቦት ሰባት ንቅናቄ በሚል ስያሜ አዲስ የፖለቲካ ድርጅት አቋቁመው በመጭው ሳምንት ግንቦት 6 ቀን 2000 ዓ.ም. ለህዝብ ይፋ ሊያደርጉ መሆኑን ታማኝ ምንጮቻችን ገለጹ።

 

ግንቦት ስድስት ቀን የሚሰጠው ይፋ መግለጫ በአሜሪካን አገር በሚገኘው በኢትዮጵያ የቴሌቭዥን ኔትወርክ (ETN) ጣቢያ ሲሆን፣ የተለያዩ ሚዲያዎችን በመጥራት በሚደረገው ጋዜጣዊ መግለጫ ዶ/ር ብርሃኑን ጨምሮ የድርጅቱ መስራቾች እንደሚገኙ ተጠቁሟል። በፕሮግራሙ ላይ የአሜሪካ ድምጽ፣ የጀርመን ሬዲዮ፣ የፓልቶክ ክፍሎች፣ ዌብ ሳይቶችና ሌሎች የተለያዩ ሚዲያዎች መጋበዛቸውን ለማወቅ ችለናል።

 

የግንቦት 7 ንቅናቄ መመሥረትን በማስመልከት በሚዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፤ የግንቦት 7 ንቅናቄ አካል የሆኑ የድረ-ገፅ፣ የሬዲዮ እና የቴሌቪዥን ጣቢያዎቻቸውን ይፋ እንደሚያደርጉ ምንጮቻችን ገልጸዋል፡፡ድርጅቱን፣ ራዲዮ ጣቢያውና የድረ-ገጹም ስያሜ ከታሪካዊው ግንቦት 7 ቀን ጋር ተያያዥነት እንዳለው የጠቆሙት ምንጮቻችን ሙሉ ስያሜውን ግንቦት 6 ቀን በሚሰጡት መግለጫ ይፋ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

 

እነ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ በመግለጫቸው ላይ በዝርዝር ያቀርቡታል ከተባለው ከንቅናቄው የፖለቲካ ግቦች መካከል ነው በማለት ምንጮች የጠቆሙት የመንግሥትን ሥልጣን ለመያዝ ሳይሆን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ያገባኛል የሚሉ ሁሉም ኃይሎች ጋር በመተባበር በሕዝብ ፍላጎትና ውሳኔ የሚገዛ ሰላማዊ፣ ሕጋዊና ዴሞክራሲያዊ የሆነ የፖለቲካ ሥልጣን አያያዝ ሂደት በኢትዮጵያ ለማስጀመር መሆኑን ይገልጻል።

 

በመጪው ረቡዕ ግንቦት 6 በይፋ መመሥረቱን የሚያስታውቀው የግንቦት 7 ንቅናቄን የትግል ስልትና መርሆዎች አስመልክቶ ምንጮቻችን እንደጠቆሙት፤ ንቅናቄው ቀኖናዊ በሆነ መንገድ የሚከተለው የትግል ስልት አለመኖሩን ጠቁመው፣ የትግል ስልቱ የኢትዮጵያን ተጨባጭና የተለየ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ሁለገብ የሆነ የትግል ሥልት በተግባር ላይ በማዋል የኢትዮጵያ ሕዝብ በምርጫ 97 የተጎናጸፈውን የሞራል የበላይነት እንዲከበር ለማድረግ ቆርጠው መነሳታቸውን በጽሁፍ ማስፈራቸው ታውቋል።

 

በተጨማሪም በቅርብ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሞክሮ የነበረውን ሠላማዊ የትግል ሥልት ጠንካራና ደካማ ጎኖችን በመገምገም መስተካከል ያለበትን አስተካክሎ እንደ አስፈላጊነቱ በሥራ እንደሚያውል ይገልፃል። ንቅናቄው ከዚህ ጋር በተያያዘ፤ ሠላማዊ ትግል ሲባል በሥልጣን ላይ ያሉት ገዢዎች ሠላማዊ ነው ብለው እንዳሻቸው የሚደነግጉት ነው ባሉት አፋኝ ሕግ የሚገዛ እንደማይሆን ማስፈራቸውን ምንጮቻችን የገለጹ ሲሆን፣ በአንፃሩ ሕገወጥ የሆኑ ሕጎችን፣ ደንቦችን፣ መመሪያዎችን በቂ ዝግጅት በተደረገበት የሕዝባዊ ሠላማዊ እንቢተኝነት በመጣስ የሚከናወን መሆኑን ይጠቁማል።

 

ታማኝ ምንጮቻችን ንቅናቄው ከሌሎች መሰል የፖለቲካ ኃይላት ጋር ለሚያደርገው ትብብር የሚገለገልባቸው መሠረታዊ እሴቶችን በተመለከተ እንደገለጹት፣ የግንቦት 7 ንቅናቄ በቅድሚያ ማናቸውም በአገሪቱ ፖለቲካ ያገባኛል የሚሉ ኃይሎች፣ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥታዊ አገዛዝ ጨምሮ የኢትዮጵያ ሕዝብ በዜግነት እንጂ በተገዢነት መኖርን የማይቀበል መሆኑን ተረድተው፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ በዜግነቱም የሚገቡትን መብቶች ተከብረውለት ለመጀመሪያ ጊዜ ለሚፈጠረው የሕዝብ ምስፍናን ላረጋገጠ መንግሥታዊ ሥርዓት ሁሉም በጋራ እንዲሠራ የሚጠይቅ መሆኑን ያመለክታል።

 

ከዚሁ በመቀጠል ንቅናቄው የፖለቲካ ኃይሎች ትብብር ዋና ዓላማ ሥልጣን ያለውን መንግሥት ወደ ድርድር እንዲመጣ ወይም ከሥልጣን እንዲወርድ ብቻ ሳይሆን በቦታው ዲሞክራሲያዊ መንግሥታዊ አስተዳደር በኢትዮጵያ ለመተካት እስከሆነ ድረስ፣ የፖለቲካ ኃይሎች ትብብር አባላት በሙሉ በጋራ የሚስማሙባቸውን የማይጣሱና የማይገሰጹ የትብብሩ የፖለቲካ እሴቶች በቅድሚያ መቀመጥ እንዳለባቸው በመግለጫቸው ለማተት መዘጋጀታቸው ታውቋል።

 

እነዚህ የፖለቲካ እሴቶች የኢትዮጵያን ሉዓላዊ አንድነት መቀበል፣ የፖለቲካ ሥልጣን፣ በአገር አቀፍ ይሁን ከዚያ በታች በሚገኙ አስተዳደራዊ አሐዶች ውስጥ የሚያዘው ዜጎች በእኩልነት በሚሰጡት የአንድ ሰው አንድ ድምፅ ሥርዓት መሆኑን ማመን፣ የትብብሩ የትግል ዓላማ ሥልጣን ለመያዝ ሳይሆን ሥልጣን በሕዝብ ፈቃድ የሚያዝበትን ነፃና ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ ለማመቻቸት መሆኑን የተጠቆመ ሲሆን፤ በንቅናቄው የተጠቀሱትን መሠረታዊ እሴቶች ከተቀበሉ ማናቸውም ዓይነት ተመሳሳይ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ፖሊሲዎች ካሏቸው፣ የራሳቸውም የሆኑ አደረጃጀቶችን የሚጠቀሙና የትግል ሥልት የሚከተሉ የፖለቲካና ፖለቲካዊ ካልሆኑ ቡድኖች ጋር በትብብር ለመሥራት ፈቃደኛ መሆኑን የምንጮቻችን ዘገባ ያስረዳል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!