(ውይይቱን በድምፅ አቅርበነዋል)

'በሞኖፖል የተያዘውን የኢትዮጵያ ሚድያ ከውጭ ሃገር ሆኖ መስበር ይቻላል'  ዶ/ር ብርሃኑ

Dr. Berhanu, Vancouver public meeting 080510

Ethiopia Zare (እሁድ ግንቦት 3 ቀን 2000 ዓ.ም. May 11, 2008)፦ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ትናንት ቅዳሜ ግንቦት 3 ቀን 2000 ዓ.ም. ከቫንኩቨር ነዋሪዎች ጋር ያካሄዱት ውይይት የተሳካና ግልጽ ውይይት አካሄዱ። ውይይቱ የተጀመረው በቀድሞ የአዲስ አበባ የኒቨርሲቲ ተማሪዎች ፕሬዝዳንት የነበረው ተማሪ ተክለሚካኤል አበበ የዶ/ሩን የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የመምህርነት ተግባርና ከዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ጋር የነበራቸውን ቅርርብ፣ በማስተማርና በመማር ሂደት ላይ ያላቸውን ችሎታ በማውሳትና ምስክርነት በመስጠት ነበር።

 

ዶ/ር ብርሃኑ የውይይት መክፈቻ ጽሁፍ ለማዘጋጀት ወደ ቫንኩቨር የመጡት በድንገት ስለሆነና ሙሉ ዝግጅታቸው ለሲያትሉ ስብሰባ ስለነበር ውይይቱን የጀመሩት በማስታወሻ የያዙዋቸውን ነጥቦች በማንሳት ነበር።በውይይቱን የጀመሩት የሚከተሉትን ነጥቦች በማብራራት ነበር። 

 

ምርጫ 97ን በሚመለከት እና ጠቅላላ የኢህአዴግ አገዛዝን የጭካኔ የመጨረሻ እርምጃ የተወሰደባቸውን ሁኔታዎች ካስረዱ በኋላ፤ የወያኔ አገዛዝ ለሕጋዊ የሠላማዊ ሂደት ምንም አይነት ዝግጅት ካለመኖሩም በላይ ማናቸውንም ምርጫም ሆነ የዲሞክራሲ እንቅስቃሴ በሕጋዊ መንገድ ማከናወን የማይታሰብ መሆኑን፣ በሀገሪቱ ምንም አይነት የዲሞክራሲ ተቋማት ሊኖሩ እንዳይችሉ መንገዱን የዘጋ መሆኑን፣ አገዛዙ የሚያካሂደውን እርምጃዎች በማስረዳት ነበር ውይይቱን የጀመሩት።

 

ከዚያም በመቀጠል የአቶ መለስ መንግሥት ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚያካሂደው ትንኮሳ ምክንያቱንና አፈጻጸሙን በሚመለከት ያላቸውን ዕይታ ተንትነው ካስረዱ በኋላ፤ በሀገር ውስጥ በተለይ በኦጋዴን ህዝብ ላይ የሚፈጸመውን ጭፍጨፋና እንግልት በሚመለከት ያላቸውን አተያይ አብራርተዋል።

 

አያይዘውም በሞኖፖል የተያዘውን የኢትዮጵያ ሚድያ ከውጭ ሀገር ሆኖ ለመስበር በተለይ በቴሌቪዥን ረገድ ያለምንም ችግር ሀገር ቤት ለማሰራጨት ባላቸው መረጃ መሰረት 250 ሺህ ዶላር በዓመት በቂ መሆኑን ካስረዱ በኋላ፤ አንድ ሺህ ሰው አንድ ሺህ ዶላር ቢያዋጣ የመገናኛ ብዙኀኑን ውጤት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚቻል አጽንኦት ያስቀመጡት ሃሳብ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ መሆኑን ለማወቅ ችለናል።

 

በማከልም በወያኔ አስተዳደራዊ መዋቅር ውስጥ በተለይ በወታደሩ አካባቢ ያለውን ደካማነት አስረድተዋል። ጦሩ በራሱ የማይተማመንና በዲሲፕሊን ያልታነጸ መሆኑንና በታሪካችን ያልነበሩ አስነዋሪ ተግባሮችን የሚፈጽም መሆኑን፤ በተለይ በሶማሊያና በኦጋዴን የፈጸማቸውን አስገድዶ መድፈርን ጨምሮ የሚካሄደውን አስነዋሪ ሂደቶች አስረድተዋል።

 

ዶ/ር ብርሃኑ ንግግራቸውን ከጨረሱ በኋላ የጥያቄና መልስ ውይይት የተካሄደ ሲሆን፣ በጥያቄና መልሱ ላይ የተለያዩ ጉዳዮች ተዳስሰው በቂ ምላሽ በመስጠት ጠያቂዎቻቸውን ያረኩ መሆኑን ለመረዳት ችለናል።

 

በውይይቱ ላይ የኦነግ የኦጋዴንና የቅንጅት ደጋፊዎችን ጨምሮ ሌሎች የቫንኩቨር ነዋሪዎችም ተገኝተዋል። (ውይይቱን በድምፅ ለማዳመጥ ከፈለጉ በሁለት ክፍሎች ያገኙዋቸዋል። የሚፈልጉትን ማጫወቻው ቁልፍ play button ላይ ይጫኑ!)

ክፍል አንድ


ክፍል ሁለት

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!