በማትያስ ከተማ

Ginbot 7 Rally  - Stockholm, Sweden

Ethiopia Zare (ኀሙስ ግንቦት 7 ቀን 2000 ዓ.ም. May 15, 2008)፦ ግንቦት ሰባት ቀን 1997 ዓ.ም. የተደረገውን የዲሞክራሲ ትግል ለማስታወስና በወቅቱ የተሰዉትን ሰማዕታት ለመዘከር በዛሬው ዕለት ግንቦት 7 ቀን 2000 ዓ.ም. (ሜይ 15 ቀን 2008) ሊደረግ ታቅዶ የነበረው ሰልፍ በስዊድን ዋና ከተማ በስቶክሆልም ተደረገ። በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን አዘጋጆቹ ለኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ ገለጡ።

 

ሰልፉን ያስተባበረው የቅንጅት ለአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ድጋፍ ማኅበር ሲሆን፣ በሰልፉም ላይ በግምት ከሰባ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ተገኝተዋል። ሰልፈኛው በተገናኘበት በሰርገልስ ቶርየት (ፕላታን) ቀደም ሲል ቅንጅትን በመወከል ፓርላማ ገብተው የነበሩትና የቀድሞው የቅንጅት የላዕላይ ምክር ቤት አባል የነበሩት ዶ/ር ሙሉዓለም ታረቀኝ ንግግር አድርገዋል። ዶ/ር ሙሉዓለም በዚሁ ንግግራቸው ላይ በፓርላማ ቆይታቸው ወቅት የታዘቡትን ለተሰብሳቢው ገልፀዋል።

 

በመቀጠልም ሰልፈኛው ልዩ ልዩ መፈክሮችን እንደያዘ የተቃውሞ ድምጹን እያሰማ ሚንት ቶርየት ወደተባለው ቦታ የእግር ጉዞ አድርጓል። በተባለው ቦታ በስዊድን የሁለት ፓርቲዎች ተወካዮች ተገኝተዋል። እነርሱም የስዊድን የቬንስተር ፓርቲ (የስዊድን የግራ ፓርቲ) የውጪ ጉዳይ ተወካይ ሃንስ ሊንድ እንዲሁም የፎልክ ፓርቲ የውጪ ጉዳይ ክፍል ኃላፊ ብርጊታ ኡልሶን ሲሆኑ፣ ሁለቱም በየተራ ንግግር አድርገዋል።

 

ሃንስ ሊንድ በመለስ ዜናዊ የሚመራው መንግሥት አምባገነንና ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ደንታ-ቢስ እንደሆነ ሊረዱ መቻላቸውን ገልጸዋል። ብርጊታ ኡልሶን ደግሞ ይሄው መንግሥት ዲሞክራሲን ከቀን ወደቀን ከማጎልበት ይልቅ ይበልጥ እያጠፋው እንደሄደ ተናግረዋል።

 

ሌላው ተናጋሪ የድጋፍ ማህበሩ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ታምራት አዳሙ ነበሩ። እሳቸውም በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ ህዝብ ለአንድነቱና ለመብቱ ካደረጋቸው ትግሎች ሁሉ ግንቦት ሰባት በእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ እንደሐውልት ተቀርጾ የተቀመጠ ቀን ነው ብለዋል።

 

 

Ginbot 7 Rally - Stockholm, Sweden

 

አቶ ታምራት አክለውም ”... ምንም እንኳን ያ ድል በጦረኛው መንግሥት የጭካኔ ጥይት ቢከሽፍም ካሁን በኋላ በማይረባ ጭቅጭቅ ጊዜ ማጥፋታችንን ትተን በአንድነት ትግሉን እንደገና ማፋፋም ይገባናል። ወቅቱም አሁን ነው ...” ሲሉ አሳስበዋል።

 

ስለሰልፉ ሁኔታ የጠየኳቸው የድጋፍ ማኅበሩ ፀሐፊ አቶ ስሜነህ ታምራት በበኩላቸው በውጭ የሚገኘው ኢትዮጵያዊ ለዲሞክራሲ ለፍትህና ለአንድነት ከሚታገለው ያገር ቤት ነዋሪ ጋር ያለውን የትግል አንድነት ያስመሰከረበትና ለወደፊቱም በማንኛውም አቅጣጫ ድጋፉን እንደማያቋርጥ የገለጸበት ሰልፍ ነበር ብለዋል።

 

በመጨረሻም ሰልፈኛው ሀገራዊ መዝሙር በማሰማት በ16 (ከሰዓት በኋላ 10) ሰዓት አካባቢ ሰልፉን አጠናቅቆ ተበትኗል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!