አምስቱ ክፉኛ ቆስለዋል

Ethiopia Zare (ረቡዕ መጋቢት ቀን 2004 ዓ.ም. March 14, 2012)፦ ከትናንት በስቲያ ሰኞ መጋቢት 3 ቀን 2004 ዓ.ም. ከቀኑ 10 ሰዓት አካባቢ ከጎደሬ ወደ ጋምቤላ በሚጓዝ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ላይ ተሳፍው የነበሩ 25 ወንዶች ተማሪዎችና ወጣቶች ካርሚ በምትባል ስፍራ ላይ በጥይት ተደብድበው 20ዎቹ ሲሞቱ 5ቱ ደግሞ ክፉኛ ቆስለዋል።

 

 

የህዝብ ማመላለሻው ጋላይ ተሳፍረው የነበሩት 35 ሰዎች ሲሆኑ፣ ወንጀሉን የፈፀሙት ወገኖች መኪናው ጋምቤላ ከተማ ሊደርስ ሃያ ኪሎ ሜትር ሲቀረው አስቁመውት ተሳፋሪዎቹን ካስወረዱ በኋላ ወንዶቹን በአንድ ወገን ሴቶቹን በሌላ ወገን ለይተዋቸው ሲያበቁ፤ ወንዶቹን በጥይት ደብድበዋቸዋል። በጥይት ከተመቱት ከ25ቱ ወጣት ወንድ ተማሪዎች ውስጥ 17ቱ ወዲያውኑ ሕይታቸው ስታልፍ፤ ቀሪዎቹን ወደ ጋምቤላ ሆስፒታል ሲወሰዱ ሦስቱ ሕይወታቸው ማለፉ ታውቋል። ቀሪዎቹ አምስቱ ደግሞ ክፉኛ የቆሰሉ በመሆኑ በሞትና በመኖር መሃል እንዳሉ ታውቋል።

 

ሃያ አምስቱ ወጣቶች የጋምቤላ ግብርና ኮሌጅ ተማሪዎች እንደሆኑ የተጠቆመ ሲሆን፣ ቀሪዎቹን ሴት ተሳፋሪዎች ደግሞ አፍነው ይዘዋቸው ከሄዱ በኋላ መልሰው እንደለቀቋቸው ለመረዳት ችለናል።

 

ይህንን የአስራ ሰባት ንፁሃን ዜጎችን ሕይወት ያጠፋውንና ዘጠኙን ያቆሰለውን እጅግ ዘግናኝ ድርጊት የፈፀሙት ወንጀለኞች እስካሁን ድረስ በቁጥጥር ያልዋሉ ሲሆን፣ የጋምቤላ ክልል ባለሥልጣናት ጉዳዩን የፈፀሙት ሽፍቶች መሆናቸውን ገልጸዋል። አያይዘውም የክልሉ ፖሊስና የመከላከያ ሠራዊት ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በመሆን ሽፍቶቹን እያደነ እንዳለ ተናግረዋል።

 

የአዲሲቱ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) የሃያ ንፁሃንን ሕይወት ያጠፋውንና አምስቱን ሰዎችን ያቆሰውን ጥቃት ክፉኛ የሚያወግዝና የሚታገል ከመሆኑም በላይ ወንጀለኞቹን ለፍርድ እንዲቀርቡና ከድራማው በስተጀርባ ያሉትን ክፍሎች ለማጋለጥ ከፍትህ ወዳጆችና ከህዝብ ጋር አብሮ እንደሚሰራ ገልጿል። እጅግ አሳዛኝ፣ አስደንጋጭ፣ ጭካኔ የተመላበት ግድያ ተፈጽሟል፤ ቤተሰቦች ልጆቻቸውንና አጋሮቻቸውን ያጡበት፣ አገር ልጆቿን የተነጠቀችበት አሰቃቂና ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ነው በማለት አኢጋን ጥቃቱን ኮንኖታል።

 

እንደ አኢጋን ገለጻ ከሆነ ድርጊቱ የተፈፀመው በአካባቢው ካለው ከመከላከያ ሠራዊት የመከማቻ ካምፕ ቅርብ ርቀት ላይ መሆኑና አደጋውን ተከትሎ እየወጡ ያሉት መረጃዎች ከወንጀሉ በስተጀርባ የማን እጅ እንዳለበት የሚያመላክቱ መሆናቸው ኀዘኑን ድርብ እንደሚያደርገውና ለወደፊቱም ስጋት ውስጥ እንዲወድቅ እንዳደረገው አስርቷል።

 

የአዲሲቱ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) መሪ አቶ ኦባንግ ሜቶ “ወንጀል ክልል የለውም። እንዲህ ያለውን ድርጊት ወያኔ/ኢህአዴግ ያድርገውም፣ የታዘዙ ግለሰቦችም ይሁኑ፣ ሽፍቶችም ይሁኑ በገንዘብ የተገዙ ቅጥረኞችም ይሁን፤ እኛ ከእውነት ጋር ስለምንቆም፣ ስለፍትህ ስለምንጨነቅ፣ ከወንጀሉ በስተጀርባ ያሉት ሊደበቁ አይችሉም፤ ሕግ ፊት ይቀርባሉ” በማለት የተሰማቸውን ጥልቅ ኀዘን ገልፀው፤ ለሟች ቤተሰቦችና ኀዘኑ ለጎዳቸው ሁሉ መጽናናትን ተመኝተዋል።

 

በዚህ አጋጣሚ የኢትዮጵያ ዛሬ ዝግጅት ክፍል ሕይወታቸውን ላጡት ተማሪዎች ወላጆችና ቤተሰቦች ልባዊ መጽናናት ይመኛል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!