Obang Metho አቶ ኦባንግ ሜቶ Ethiopia Zare (መጋቢት 7 ቀን 2004 ዓ.ም. March 16, 2012)፦ የአገራችን ግማሽ ህዝብ የሚሆኑትን ሴት እህቶቻችን ያልተሳተፉበት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ምስረታ ስኬቱ ያማረ እንደማይሆን፣ ቢሆንም ራሱን ለጥፋት እንደሚያጋልጥ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ ተናገሩ።

 

 

አቶ ኦባንግ ይህን የተናገሩት ባለፈው ከየካቲት ሠላሳ እስከ መጋቢት ሦስት ቀን በዋሽንግተን ዲሲ በተካሄደው የኢትዮጵያ ሴቶች ዓለም አቀፍ ጉባዔ ላይ “የሴቶችን መብት በማስከበር ለሥልጣን ማጎናጸፍ” በሚል ርዕስ ባደረጉት ንግግር መሆኑን አኢጋን ለኢትዮጵያ ዛሬ ከላከው መግለጫ ለመረዳት ችለናል።

 

በዚህ የኢትዮጵያ ሴቶች ዓለም አቀፍ ጉባዔ ላይ አስራ ስድስት የተለያዩ ድርጅቶች መሳተፋቸውም ታውቋል።

 

አቶ ኦባንግ በዚህ ባደረጉት ንግግር ላይ ለዛሬው ለእሳቸው የሰብዓዊ መብት ተሟጋችነት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያደረጉላቸው አያታቸው መሆናቸውን በመጥቀስ፤ ለሴት እህቶችና እናቶች አስፈላጊው ክብርና ዋጋ ሊሰጥ እንደሚገባ አሳስበዋል። አቶ ኦባንግ “የሴቶች እህቶቻችን ያላሳፈረ የነፃነት፣ የሠላምና የብልጽግና ባቡር ከታሰበለት የነፃነት ጣቢያ መድረስ አይችልም” በማለት ተናግረዋል። በመሆኑም አብሮነት እጅግ አስፈላጊ እና ወሳኝ መሆኑን በመጥቀስ “አብረን ለመሥራት ዝግጁ ነን!” ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

 

“አገራችን ሁሉም ዓይነት ሴቶች ያስፈልጓታል። አምላክ ለዚህ የተቀደሰ ተግባር የጠራው የተማሩትንና የተሻሉትን ብቻ አይደለም። ሁሉንም እንጂ! ስለዚህም በኦሞ ሸለቆ ከንፈሮቿ ላይ ሸክላ ከምታንጠለጥለው ውብ ጀምሮ በአዲስ አበባ ከንፈሮቿን ቀይ ቀለም እስከተቀባችው ቆንጆ፤ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ባዶ እግሯን ከተዋበችው ጀምሮ በዋንዳቢቲ እስካጌጠችው የኦሮሞ ኮረዳ፤ በኦጋዴን በሒጃብ ካሸበረቀችው ኢትዮጵያዊት ጀምሮ ባማረ ጥለት እስከተዋበችው የአማራ ቆንጆ፤ ግማሽ አካሏ እርቃን ከሆነው የአፋር ድንቅ ጀምሮ በሹርባዋ እስከተዋበችው የትግራይ ሴት … ሁሉም ዓይነት ሴቶች ኢትዮጵያችን ያስፈልጓታል።” ሲሉ አቶ ኦባንግ ተናግረዋል።

 

በማያያዝም በጉባዔው ላይ ለተሳተፉት ኢትዮጵያውያን ሴቶች “እነዚህ ሴቶች እናንተ ናችሁ፤ እናንተም እነዚያ ሴቶች ናችሁ። እናንተ እዚህ የተሰበሰባችሁ አገር ቤት ያሉት ሴቶች ሁሉ ተወካዮች ናችሁ። አገር ቤት ያሉት ኢትዮጵያውያን ሴቶች መብት እስካልተከበረ ድረስ የእናንተ በምዕራባውያን አገራት መብታችሁ መከበሩ ብቻ በቂ አይሆንም።” በማለት ጠንካራ መልዕክት አስተላልፈዋል።

 

የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ “ሁላችንም ነፃ ካልወጣን ማንም ነፃ ሊሆን አይችልም” የሚለውን ዋንኛ ዓላማው አድርጎ የሚንቀሳቀሰው ለዚህ እንደሆነ አቶ ኦባንግ ተናግረዋል። … (የአቶ ኦባንግን ሙሉ ንግግር አስነብበኝ!)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ