Ethiopia Zare (ረቡዕ ግንቦት 20 ቀን 2000 ዓ.ም. May 28, 2008)፦ ዛሬ ማምሻውን በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ አራት ሰዓት ተኩል ገደማ በስድስት ኪሎ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሲጮሁ ማምሸታቸውን ከአዲስ አበባ የደረሰን ዘገባ ጠቆመ።

 

ግንቦት 9 ቀን ወለጋ የተካሄደውን ጭፍጨፋ ተንተርሶ በተለይ የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች “ወላጆቻችንና ወገኖቻችን እየሞቱ እኛ እንዴት እንማራለን” በሚል አንዳንድ ጥያቄዎች እንዳሏቸው ለዩኒቨርሲቲው ባለሥልጣናት አመልክተው ነበር።

 

ዛሬ ቀን ላይ የዩኒቨርሲቲው ባለሥልጣናት ከተማሪዎቹ ጋር የተወያዩ ሲሆን፣ “እናንተ ትምህርታችሁን ቀጥሉ፤ ችግሩ አሁን ረግቧል። ጉዳዩ እየተጣራ ስለሆነ የሚመለከተው አካል ጉዳዩን አጣርቶ ተገቢውን ምላሽ ይሰጣችኋል፣ …” በሚል ተማሪዎቹን ለማረጋጋት ሞክረው ነበር።

 

ማምሻውን በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ አራት ሰዓት ተኩል ጀምሮ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች በግቢው አጥር ላይ ተንጠልጥለው ከፍተኛ ጩኸት ሲያሰሙ እንደነበር ለማወቅ ችለናል። ጩኸቱ ለጥቂት ሰዓታት ያህል እንዳልተቋረጠ ታውቋል። በመጨረሻም በምን ምክንያት እንደሆነ ባይታወቅም ጩኸቱ መብረዱን አረጋግጠናል።

 

ወደ ዩኒቨርሲቲው ግቢ የፖሊስ እና የፌዴራል ኃይሎች መግባት አለመግባታቸውን ግን ለማረጋገጥ አልቻልንም።

 

በተያያዘ ዜና፤ መብራት በፈረቃ መሆን ከጀመረ ጥቂት ሣምንታትን ያስቆጠረ መሆኑ ይታወቃል። ዛሬ ማምሻውን በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ በአብዛኛው መብራት እንዳልነበረ ለማወቅ ችለናል። በመብራት ኃይል የመብራት ማከፋፈል የጊዜ ሠሌዳ መሰረት ዛሬ መብራት በማይቋረጥባቸው አካባቢዎች ሁሉ ማምሻውን ከምሽቱ አራት ሰዓት ተኩል ጀምሮ እስከ እኩለ ሌሊት (ስድስት ሰዓት) ድረስ መብራት ተቋርጦ ነበር። በስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲም በተመሳሳይ ሰዓት መብራት ጠፍቶ ነበር።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ